>

የኔቶና የራሽያ ሥጋቶችና ፍጥጫ ( አሳፍ ሀይሉ)

የኔቶና የራሽያ ሥጋቶችና ፍጥጫ

(በ10 ጥያቄና መልሶች!)
አሳፍ ሀይሉ

አውሮፓውያን ላለፉት ሁለት አሰቃቂ የዓለም ጦርነቶች፣ ምድራቸውን የጦርነት አውድማ አድርገው፣ የደረሰባቸውን እልቂትና የመጣባቸውን ጦስ በሚገባ አይተውታል። ሌላ ጦርነት አውሮፓ ውስጥ እንዲቀሰቀስ አይፈልጉም። አሜሪካ ደግሞ አውሮፓውያኑ ራሺያን ገትረው እንዲይዙላት ትፈልጋለች። በመሐል ሁለቱንም የሚያገናኝ ኔቶ አለ።
ከሶስት ዓመት በፊት የኔቶ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወታደራዊ አዛዥ፣ በአንድ ዓለማቀፍ ጆርናል ላይ፣ እጅግ ወሳኝ የሆኑ 10 ጥያቄዎች ቀርበውለት ነበር። በሙሉ የአዛዥነት ሥልጣኑ ላይ እያለ ነው ጥያቄዎቹ የቀረቡለትና የመለሰው። ያለምንም ፍርሃትና መደባበቅ ይሰጣቸየነበሩ ምላሾች የሚደንቁ ናቸው።
እነዚህ 10 ጥያቄዎችና ምላሾች፣ አሁን በራሺያና አውሮፓውያን መካከል የነገሠውን ሥጋትና ፍጥጫ፣ አስቀድሞ በትክክል ያመላከቱ የመሆናቸው ነገር ስላስደነቀኝ፣ ከዚህ በታች እንዳለ አቅርቤያቸዋለሁ።
ጥያቄ 1፦ አሁን ራሺያ ባላት ወታደራዊ ቁመናና ለአውሮፓ ባላት ስትራቴጂክ የቦታ ቅርበት አንፃር፣ ራሺያ በኔቶ አባል ሀገሮች ላይ ጥቃት ብትሰነዝር፣ ኔቶ ጥቃቱን የመመከት አቅም አለው ወይ?
መልስ፦ የለውም።
ጥያቄ 2፦ ራሺያ ከኒውክሊየር በመለስ ባሉ ወታደራዊ የሚሊቴሪ ቴክኖሎጂዎች በአውሮፓ ሀገሮች ላይ (ለምሳሌ በእንግሊዝ ላይ፣ ወይም በፈረንሳይ፣ አሊያም በጀርመን ላይ) ጥቃት ብትሰነዝር፣ በተናጠል የራሺያን ወታደራዊ ጉልበትና ወረራ መቋቋም የሚችል የአውሮፓ ሀገር አለ?
መልስ፦ የለም።
ጥያቄ 3፦ የአውሮፓ ሀገራት ወይም ኔቶ ራሱ ራሺያን ለመገዳደርና በአውሮፓ ምድር የምታደርጋቸውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመግታት፣ ወይም ፈርጣማ ጉልበት ገንብቶ ራሺያኖቹን አደብ ለማስገዛት ፍላጎቱ ወይም ዝግጁነቱ አላቸው?
መልስ፦ ማናቸውም የላቸውም። የአውሮፓ ሀገራቱ ወታደራዊ አቅማቸውን በማጠናከር ራሺያን ማስበርገግና፣ ዳግመኛ በአውሮፓ ማናቸውንም ዓይነት የቀዝቃዛውን ጦርነት የመሠለ ወታደራዊ ፍጥጫ ማስጀመር አይፈልጉም፣ ማናቸውንም ከራሺያ ጋር ጦርነት የሚቀስቀስ ነገር መስማት አይፈልጉም፣ ባጠቃላይ አውሮፓውያኑ ከሁለት አውዳሚ የዓለም ጦርነቶችና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዳግመኛ አውሮፓን የጦርነት ቀጣና ማድረግ አይፈልጉም።
ጥያቄ 4፦ ታዲያ ኔቶ ወደ ራሺያ ግዛቶች እየቀረበ፣ የቀድሞ የሶቭየት ራሺያ ግዛቶች የነበሩ የምሥራቅ አውርፓና የባልካን ሀገሮችን ለምንድነው በአባልነት እየመለመለ ያለው? ምንድነው ራሺያን ለመክበብ የሚያነሳሳው ምክንያት? ይሄ ራሺያን አያስቆጣም?
መልስ፦ ያስቆጣል። ሀገሮች ግን ነፃ መሆን አለባቸው። የራሳቸውን ውሳኔ መወሰን መቻል አለባቸው። ራሺያ ከራሷ ግዛት አልፋ ሌሎችን በጉልበቷ የምታሸማቅቅበት ሁኔታ በፍፁም ሊኖር አይገባም። ይሄን ለማረጋገጥ ስንል ከወታደራዊ ግንኙነት ውጭ የሆነ ልዩ የአባልነት መሥፈርቶችን አውጥተን ከብዙ ሀገሮች ጋር እየሠራን ነው። የአውሮፓ ህብረት አባል የሆኑም ያልሆኑም ሀገራት አሉ። ጥያቄየሚመጣልን ከሀገሮቹ ከራሳቸው ነው። እንጂ ኔቶ ማንንም አይመለምልም። ከፈለጉ ግን መከልከል የለባቸውም። ራሺያን ያስቆጣል ተብሎ የሚተው ነገር አይደለም ይሄ።
ጥያቄ 5፦ እንዲህ ካላችሁ ታዲያ ወይ ኔቶን ለምን አታጠናክሩም? ምንድነው ችግራችሁ ኔቶን ለማጠናከር?
መልስ፦ ኔቶን በተለያዩ መስኮች ለማጠናከር ብዙ ጥረት ተደርጓል። ችግሩ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ነው። በአውሮፓ ኃያላኑ በኩል ራሺያን መተናኮል የሚመስሉ ድርጊቶች አይፈለጉም። ለምሳሌ ዋናዎቹ ሀገራት ከኢኮኖሚያቸው ለወታደራዊ ፍላጎታቸው የሚመድቡትን ባጀት ካየን ከ1% በታች ነው። የብዙዎቹ ከ2% በታች ነው። ኔቶ ቢያንስ ሀገራቱ 3% እና ከዚያ በላይ ባጀታቸውን ለወታደራዊ ግልጋሎት እንዲመድቡት ይፈልጋል። ስምምነቱም አለ። ግን ማንም ይህን ሀላፊነት መሸከም አይፈልግም። ማንም ዳግመኛ የቀዝቃዛውን ጦርነት ዘመን የመሠለ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድምና ክምችት በአውሮፓ እንዲፈጠር አይፈልግም። በዚህም የተነሳ ኔቶ በሚገባው ልክ አቅሙን ማሳደግ አልቻለም። እውነቱን ለመናገር ኔቶ በአሁኑ ሰዓት ራሺያኖቹን በወታደራዊ አቅምም በቴክኖሎጂም መመከት በሚችል ቁመና ላይ አይደለም። ምንም መደባበቅ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
ጥያቄ 6፦ ብዙዎች ኔቶ ለምን አልፈረሰም? ብለው ይጠይቃሉ። የቀዝቃዛው ጦርነት አክትሟል። ራሺያ ሥርዓቷን ቀይራለች። አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ከኮሙኒስት ቻይና ጋር እየነገዱ ነው፣ ዓለም በኢኮኖሚ ተሳስራለች። ለአውሮፓውያን ኔቶ ምን ያደርግላቸዋል? ወይስ በራሺያ የመወረር፣ በራሺያ የመጠቃት ሥጋቱ አሁንም አለ? ኔቶ ለምን አልፈረሰም?
መልስ፦ ልክ ነህ። እንደዚያ የሚሉ ብዙ አካሎች አሉ። ራሺያኖቹም የሚሉት ይሄንኑ ነው። ነገር ግን የኔቶ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ዓላማው ተቀይሯል። ራሺያ ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። በዘርፈብዙ የጋራ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በአባል ሀገራቱ ትብብርና መዋጮ የሚሠራ፣ እና ለአውሮፓም ሆነ ለዓለም ደህንነት መረጋገጥ የቆመ፣ በጋራ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት የሚሠራ ተቋም ነው። ይህን ተቋም ማጠናከር አባል ሀገራቱን ያጠናክራል። የተናጠል ሥራቸውንና ሥጋታቸውን ይቀርፋል። ሁሉም በተናጠል ቢሄዱ ኖሮ ከሚሸከሙት አላስፈላጊ ወታደራዊ ሸክም ይገላግላል አባላቱን። እና ደግሞ አስፈሪነቱም ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ዛሬ ላይ ብዙ ሀገሮች ከብዙ ክፉ ድርጊት የሚቆጠቡት ማድረግ ሳይቻላቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ እንደ ኔቶ ያሉ የትብብር ተቋሞች ምን መዘዝ እንደሚያመጡባቸው ስለሚያውቁ ነው። ስለዚህ የዓለም ሠላም የሚጠበቀው ኔቶን በማጠናከር ነው፣ እንጂ እንዳይጠናከር በመፍራት አይደለም።
ጥያቄ 7፦ ብዙዎች ኔቶ አሜሪካን ለማስደሰት ብቻ የቆመ ጊዜ ያለፈበት ድርጅት ነው ይላሉ፣ አሜሪካ ጉዳይዋን በአውሮፓውያን በኩል ለማስፈፀም በሪሞት ከንትሮል ወዳሻት የምትጠመዝዘው ድርጅት ነው በማለት አስፈላጊነቱን ይተቻሉ። ለአውሮፓ ከአሜሪካ ይልቅ ራሺያ ትቀርበናለችና ከአሜሪካ ይልቅ ከራሺያ ጋር ብንተባበር ይበልጥ ሠላማችንን ማስጠበቅ እንችላለን የሚሉም አሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ወይም የድርጅትዎት የኔቶ አባልሀገራት ዝንባሌና አስተያየት ምንድነው?
መልስ፦ በእርግጥ ኔቶን ከአሜሪካ ጋር አቆራኝተው የሚገልፁት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተሳስተዋል ማለት አይቻልም። ኔቶ ከታሪኩም አንፃር ከአሜሪካ ጋር የተቆራኘ ነው። ከሁለተኛየዓለም ጦርነት ማግሥት ጀምሮ እስካሁንም ድረስ ለኔቶ ትልቁን የኢኮኖሚ መዋጮና የሚሊቴሪ ድርሻ የምታበረክተው አሜሪካ ናት። ስለዚህ በኔቶ መቀጠል ጉዳይ ላይ የአሜሪካኖች ጠንካራ ፍላጎት እንዳለ መካድ አይቻልም። ባላት አስተዋፅዖም ልክ በኔቶ እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ አላት። ይህ ማለት ግን ኔቶ የአሜሪካ አሻንጉሊት ነው ማለት አይደለም። ኔቶ የሚሠራበትና አባል ሀገሮቹ ሁሉ በውሳኔዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት የራሱ የሚመራባቸው ውስጣዊ አሠራሮች አሉት። አሜሪካም ሆነች ሌላ ማንም አንድ ሀገር ተነስቶ ስለፈለገ የሚጠመዝዘው ድርጅት አይደለም ኔቶ። ለምን ኔቶ አልፈረሰም? እንደነገርኩህ አስፈላጊ ስለሆነና ዘርፈብዙ ጥቅሞች ስላሉት ነው። በመላው ዓለም ፈጥኖ ሊደርስ የሚችል የሠላም አስከባሪ ሀይል ነው ኔቶ። የራሺያኖቹና የሌሎችም ሥጋት ይገባናል። ነጠር ግን የኔቶ እንቅስቃሴዎች ሠላማዊና በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይሄንን ድርጅት በቀላሉ መበተን የሚፈልግ ማንም የለም።
ጥያቄ 8፦ ኔቶ ራሺያን የሚገዳደርና በቀላሉ ለአሜሪካ ፍላጎት የማይገዛ ጠንካራ ሀይል ሆኖ እንዲወጣ ምን መደረግ አለበት ይላሉ እርስዎ?
መልስ፦ እኔ እንደማስበው የኔቶ አባል ሀገሮች አንድ ቁርጥ ውሳኔ መወሰን አለባቸው። ኔቶ ከስም ባለፈ በእውን እንዲጠናከር፣ ነጥሮ እንዲወጣ፣ ብቁ ተወዳዳሪ ሀይል ሆኖ እንዲወጣላቸው ይፈልጋሉ? ውሳኔው በእጃቸው ነው። በተለይ በኢኮኖሚም በወታደራዊም ረገድ ትልቅ አቅም ባላቸው ሀያላን አባል ሀገሮቹ እጅ ላይ ያለ ውሳነው ይሄ። እንደሚታየኝ ሶስት አማራጮች ናቸው ያሉን። የመጀመሪያው ኔቶን አስፈላጊ አይደለም ብሎ ማፍረስ ነው። ይሄ አማራጭ ግን በፍፁም የሚታሰብ አይደለምና እንተወው። ሁለተኛው ምርጫ የኔቶን አስፈላጊነት ማመንና ኔቶን በሁሉም ስትራቴጂክ መስኮች ጠንካራና ተገዳዳሪ አድርጎ ለማውጣት መወሰን ነው። ይህን ከወሰኑ አባላቱ ሊወስዷቸው የሚገቧቸው ጠንካራ፣ በተግባር የሚገለፁ ውሳኔዎች አሉ። ከእነዚህ ዋነኛው አባል ሀገሮች ለድርጅቱ የሚመድቡትን ዓመታዊ ወጪ ማሳደግ ነው። በኢኮኖሚያቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው። ከሀገራቸው ውሳኔ ሰጪዎች ሥልጣን ላይ የተወሰኑ ነገሮችን ሸርፈው ለኔቶ ማስተላለፍ አለባቸው። ነገር ግን አሜሪካን ጨምሮ ይህን ሲያደርግ የሚታይ ማንም የለም።  አሁን እዚህ በአውሮፓውያኑ ስብሰባ ላይ የተገኘሁትም ለሀገራቱ መሪዎች ይሄንኑ ጥሪ ለማቅረብ ነው። የመጨረሻው አማራጭ ግን ኔቶን አሁን ባለበት ቁመናው አልፈስፍሶ የረባ ሚና እንዳይኖረውና ከአባል ሀገሮቹ በኩል በሚታየው በቸልታ የተነሳ ተገዳዳሪ እንዳይሆን አድርጎ ማስቀረት ነው። ይህ ትልቅ አደጋ አምጥቷል። ትልቅ ስህተት እየሠራን ነው። ድክመታችንን ያወቁ ሌሎች ብዙ ርቀት እየሄዱ ነው። ይህንን ዛሬ ላይ ልብ ማለት ካልቻልን፣ ነገና ከነገ ወዲያ የሚጋረጥብን አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
ጥያቄ 9፦ በአውሮፓ የኒውክሊየር መሣሪያ የሚያማዝዝ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ሥጋት አድሮብዎት ያውቃል በግልዎት?
መልስ፦ በሥጋት ደረጃ እንኳን የኒውክሊየርን ጦርነት ለማስነሳት የሚፈቅድ፣ ማለቴ ሌላውን አጥፍቶ ራሱንም ለማጥፋት የሚፈቅድ አካል በዙሪያችን አለ ወይም ይኖራል የሚል ሥጋት የለብኝም። ነገር ግን የመቻሉንና ያለመቻሉን ሁኔታ ከሆነ እየጠየቅከኝ ያለኸው፣ አዎ፣ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያዎች እስካሉ ድረስ ለጦርነት ሊውሉ የሚችሉበት ዕድል የቱንም ያህል የጠበበ ቢሆን ሁልጊዜም አለ። ይሄን እውነታ ልትሸሸው አትችልም። ልታደርግ የምትችለው ያንን ለመከላከል የሚያስችል የማስፈራራትና ራስን የመከላከል የቴክኖሎጂ አቅም መፍጠር ነው። በአሁኑ ወቅት ኒውክሊየርን ትተህ፣ የራሺያ የጦር ጄቶች ተነስተው ያንዱን ሀገር የአየር ክልል ቢጥሱ በቅፅበት የምናስቆምበት አቅም የለንም ነው የምልህ። ምኞቴ ይህ ዓይነቱ ግልፅ ቸልተኝነት የሚጋብዝብን አደጋዎች እውን እንዳይሆኑ ብቻ ነው። ሌላ ማለት የምችለው ነገር ያለ አይመስለኝም።
ጥያቄ 10፦ ኔቶ ከራሺያ የሚሻልበትን አንድ ነገር ብቻ ይንገሩኝ ብልዎት፣ ያ ኔቶ ብልጫ የወሰደበት ጠንካራ ጎን ምንድነው ይላሉ በእርስዎ የግል አስተያየት?
መልስ፦ ኢኮኖሚ! ኔቶ በአባላቱ ትብብር ሌላ ማንም የዓለም ሀገር መፍጠር የማይችለውን የኢኮኖሚ አቅም ባንድ ሌሊት ፈጥሮ ማደር ይችላል። ይህን ያልደከመ ጎኑን በስትራቴጂካዊ መንገዶች አጎልብቶና አባላቱን አስተባብሮ  መጠቀም ከተቻለ፣ ኔቶ የተነሳለትን ሠላምና ደህንነት በአስተማማኝ መልክ በተግባር ማረጋገጥ የሚችል፣ አመርቂ የትብብር ተቋም ሆኖ ይቀጥላል። ይህንንና ሌሎችም ጠንካራ ጎኖቹን በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ ግን፣ እንኳንስ ለሌላው ዋስትና ሊሰጥ፣ ራሱንም ማዳን አይችልም። እውነቱ ይኸው ነው። አማራጩም ግልፅ ነው።
የመጨረሻ ጥያቄ፦ በመጨረሻ ለኔቶ አባል ሀገራት ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የሚፈልጉት አንድ መልዕክት ካለ ቢነግሩን? ከሌለዎትም ስለነበረን ቆይታና ስለሰጡኝ ቀጥተኛ ምላሾች እጅግ አድርጌ አመሠግንዎታለሁ።
መልስ፦ እኔም አመሠግናለሁ። አንድ መልዕክት ላልከኝ፣ መልዕክቴ ሁሌም አንድ ነው። “ደካማነት ትልቅ ድምአለው፣ ክፉ አድራጊዎችን ከሩቅ ይጣራል! ጠንካራ ሆኖ መገኘት ግን አስተማማኙ የሠላም ዋስትና ማግኛ መንገድ ነው!” ይህ ነው መልዕክቴ። “Weakness arouses evil. And strength is the surest guarantee to peace.”
ይህንኑ ቃል ሰሞኑን በቲቪ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው፣ የትራምፕ ምክትል ከነበሩት ከማይክ ፔንስ አፍ በድጋሚ ሲወጣ ሰማሁት። እና የቀድሞውን የኔቶ ወታደራዊ አዛዥ ቃለመጠይቅ አስታውሶኝ ፃፍኩት።
ለዛሬ አበቃሁ።
መልካም ጊዜ።

Filed in: Amharic