>

አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ !!! (ብርሀኑ አድማሴ)

አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ !!!
ብርሀኑ አድማሴ

 

“እስከ እለት ሞቴ ቃለ እግዚአብሔርን እየተናገርኩ ባልፍ ደስታዬ ነው….!!!” 
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ዛሬ እሁድ ከዚህ ዓለም ድካም  ማረፋቸውን የኢኦተቤ መገናኛ ብዙሃን  አገልግሎት ስርጭት ድርጅት አሳውቋል።
ብፁዕነታቸው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ለተሚማ አረጋግጠዋል።
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ ጥር 14 ቀን 1972 ዓ.ም. ከተሾሙት ብፁዓን አባቶች አንዱ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፤ እስከ ዕርግና ዘመናቸው ከቆዩበት ደብረ ብርሃን ቀደም ብሎ፣ በአርሲ እና በመቐለ አህጉረ ስብከት ተመድበው ጉልሕ ሐዋርያዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
“እስከ እለት ሞቴ ቃለ እግዚአብሔርን እየተናገርኹ ባልፍ ደስታዬ ነው፤” የሚሉት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ በዕርግና ዕድሜአቸው እንኳ፣ በየወረዳው እየተንቀሳቀሱ ለስብከተ ወንጌል ባሳዩት ትጋት ይታወቃሉ፡፡
በተለይም፣ ባለፉት ዓመታት ቁልፍ የዕቅበተ እምነት ትኩረት በኾነው በፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ ረገድ፣ የኑፋቄው ወኪል ሰባክያንና ዘማርያን ነን ባዮች ሀገረ ስብከቱን እንዳይዳፈሩ፣ በሰጡት ጥብቅ አባታዊ አመራርና ባደረጉት የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ይታወሳሉ፡፡
በራስ አገዝ ልማትም በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ታሪካዊውን የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዐደባባይ ይዞታ በማስከበር፣ እንደ ጻድቃኔ ማርያም እና ሸንኮራ ዮሐንስ ያሉ ታላላቅ አድባራትን በማስተባበር ያሠሩትና የከተማው መገለጫ ለመኾን የበቃው ዘመናዊ ኹለ ገብ ሕንፃ በአብነት ይጠቀስላቸዋል፡፡
ከኹሉም በላይ ደግሞ፣ በጸሎታቸውና በአባትነታቸው፣ በተመደቡባቸው አህጉረ ስብከት አገልጋዮችና ምእመናን የተወደዱ አንጋፋ አባት ነበሩ – አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፡
 
ረቡዕ ማታ ገብተን ሐሙስ ጧት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ ሀገር ቤት የገቡት ሃምሌ ሃያ አምስት ቀን በእለተ ረቡዕ ነበር።
ሐሙስ ጧት አንድ ከዚያ በፊት በመልክ የማላውቃቸው በስም ደጋግሜ የሰማኋቸው አባት ፣ምርኩዝ ይዘው ከትክሻቸው ወረድ ያሉ ወይም የመሬት ስበት የሚታገላቸው አባት ቅዱስ ፓትርያርኩ የት ነው ያሉት አሉን።
ደረጃ መውጣት አቅቷቸዋል። በጧት ከደብረ ብርሃን መምጣቸው ያወኩት ማን እንደሆኑ ከአጣራሁ በኋላ ነበር።
በዚያ ሰዓት ብዞቹ ግራ ተጋብተው መፈራራት ውስጥ ሁነው መጥተው ሰላም ለማለት የተፈራሩበት ሰአት ነው። አንዳንዶች አኩርፈው ልድርድር ልከናቸው ይዘዋቸው መጡ ብለው ለድርድር በወከሏቸው ያኮረፉም ነበሩ።
በግቢው ሁነው አድፍጠው ያየሩን ሁኔታ አይተው መጥተው እንጅ የነሱ ያሉትን ያህል የቀድሞቹ አረጋውያን ጳጳሳት ደግሞ የደስታቸውና የናፍቆታቸው መጠን ድካማቸውን አስረስቷቸው ደረጃውን እንደ ወጣት ሲወጡት ታዝበናል። ከነዚህም አንዱና ያስገረሙን አንጋፋውና አረጋዊዩ አቡነ ኤፍሬም ናቸው።
ምን አልባትም ከዘጠናዎቹ አጋማሽ እድሜ ክልል ሳይሆኑ አይቀሩም።
የሰውነታቸው ድካም ዐይቼ በሌሊት መምጣታቸው ሰምቼ አጥብቄ ተገርሜባቸዋለሁ።የቅዱስነታቸው መምጣት ደስታ ሃይል ሁኗቸው እንጅ በጣም ተዳክመው ነበር።
የዘር ፖለቲካው ሥር ሳይሰድና መንፈሳዊ አባቶችን በግዳጅ ወደ ተወለዱበት አካባቢ መመደብ ሳይጀመር የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ።
እጅግ ተወደውና  ተከብረው መኖሯቸውን፣ሕዝቡ እንደ ቅዱስና የተለየ መናኝ አድርጎ የመለከታቸው እንደነበር ሰምቻለሁ።
ትግራይ በታሪኳ እሳቸውን የመሰለ ተወዳጅ አባት አልነበራትም። በልማት የተመሰገኑት አቡነ ዮሐንስን የመሰሉ ታላላቅ አባቶች ቢመደቡም እንደ አቡነ ኤፍሬም በትግራይ የከበረ አልነበረም ሲሉ የሚያውቁ ነግረውኛል።
የዘር ፖለቲካውን መሬት ለማስነካትና ሁሉ በዘር እንዲያስብ ሲገደድ ወደ ተወለዱበት አካባቢ ደብረ ብርሃን  ሀገረ ስብከት ተቀይረው በደግነትነታቸውና በብህትውናቸው ታውቀው ኑረዋል
የዋህና ቅን ፍጹም የድሮ ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ለብፁእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ የነበራቸው ክብርና ፍቅር  ማታ ገብተን ጧት ሲመጡ አስመስክረዋል።
ደጉ አባት ከብፁእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ጋር እረፍታቸውን አድርገዋል።
አረጋዊያኑና ደጋጎቹ ተከታትለው እየሄዱ ነው።
ጌታ ሆይ ለቤተክርስቲያን ተተኪ አባቶችን ፍጠርልን።
ደጉና የዋሁ አባት አቡነ ኤፍሬም በረከተዎ አትለየን
የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን!
Filed in: Amharic