>

ስለ ዘንድሮው 12ኛ ክፍል ውጤት እና በቤንሻንጉል ክልል በእሳት ስለተቃጠሉት ሰዎች ከባልደራስ የተሰጠ መግለጫ

ስለ ዘንድሮው 12ኛ ክፍል ውጤት እና በቤንሻንጉል ክልል በእሳት ስለተቃጠሉት ሰዎች ከባልደራስ የተሰጠ መግለጫ
 
 ስለ ዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና

የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ብዙ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸውን ለብርቱ ጭንቅ ዳርጓቸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ የሚታየው፣ በቅርቡ የአገሪቷ ትምህርት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ገለፃ ፡-
1. በአገራችን የፈተና መሰረቅ ከግለሰብ ይልቅ ተቋማዊ እየሆነ መምጣቱ
2.  “የእኔ ክልል ተማሪዎች ማለፍ አለባቸው” በሚል በተቋም ደረጃ ወረቀቶችን በመስረቅና መልስ በመስጠት  ጭምር ተባባሪ የሆኑ አመራሮች መኖራቸው የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ደግሞ፣ የራስን ክልል ተማሪ እንዲያልፍ ከማድረግ ባሻገርም፡-
1.የሌላ ክልል ተማሪ ወደ ዩኒቨርስቲ እንዳይገባ ከውስጥ ሆኖ አሻጥር እንደተሰራ፣
2. በተቋም ደረጃ የአንድን ክልል ተማሪዎች በብዛት ወደ ዩኒቨርስቲ ለማስገባት የውስጥ አሻጥር እንደተፈፀመ፣
3. በእርማት ላይ መሠረታዊ ችግር እንደተፈፀመ በተግባር የታየ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ይህ ሁኔታ ሳይታረም የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት ሊኖር ስለማይችል፣ በመንግሥት በኩል ፍትሃዊ እርማት ለመስጠት የሚከተሉት የማስተካከያ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡-
የዘንድሮው የፈተና ውጤት በተቋም ደረጃ ስርቆት የተፈፀመበት ስለመሆኑ እና አለመሆኑ በፖሊስ ምርመራ ተደርጎበት እስኪጣራ ድረስ እንዲታገድና እንዲቆይ፣
2..የሰሜኑ ጦርነት በተካሄደባቸው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ ታይተው ለአካባቢው  ተማሪዎች የተለየ ድጋፍ እንዲደግላቸው፣
3. በእርማት ላይ ችግር ያለ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስትር አጣሪ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ጉዳዩን እንዲመረምረው፣
4. በትምህርት ተቋማት ያለው የፖለቲካ እና የብሔር ምደባ እንዲቆም፣
5. በዚህ ጉዳይ ህግን ተላልፈው የሚገኙት ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡
 # በቤንሻንጉል ስለተቃጠሉት የሰው ልጆች
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ስለተፈፀመ ዘግናኝ ድርጊት  ባወጣው ሪፖርት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በተጠርጣሪነት ተይዘው በነፃ የተለቀቁ ስምንት የትግራይ እና ሁለት የጉምዝ ተወላጆች የይለፍ ደብዳቤ ይዘው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በጉዞ ላይ እያሉ፣ በፍተሻ የነበሩ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከተሳፈሩበት አውቶብስ እንዲወርዱ ከተደረጉ በኋላ፣ ከህግ ውጭ ተረሽነው አስክሬናቸው ወደ ጥሻ ተጥሎ እንዲቃጠል መደረጉ ተገልጿል፡፡
በፍተሻው ወቅት ከተረሸኑት ግለሰቦች ላይ አንድ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎች እና አርባ ሺህ ብር ተገኘ መባሉንና፣ ይህም በቅርቡ በአባይ ግድብ ሰራተኞች  እና አጅበዋቸው ይንቀሳቀሱ በነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ከደረሰው ግድያ ጋር እንዲጠረጠሩ ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
ይህ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ የሆነ ህገ ወጥ ድርጊት በዚህ አልበቃ ብሎ፣ በአውቶውብስ ውስጥ ተደብቆ ተገኘ የተባለ ዘጠነኛ የትግራይ ተወላጅ ክፉኛ ከተደበደበ በኋላ፣ ቀደም ሲል እንዲቃጠሉ ከተደረጉት አስክሬኖች ጋር መካከል ተጥሎ፣ በሕይወቱ እያለ እንዲቃጠል መደረጉ ታውቋል፡፡
በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተደረገው ይህ ዓይነት ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት ላለፉት 30 ዓመታት ሲሰበክ ከኖረው የብሔር ጥላቻ ፖለቲካ የመነጨ ነው፡፡ በኦሮሞ/ብልጽግና በሚመራው ገዥው ፓርቲ አሁንም ሙጥኝ ተብሎ የተያዘው የጥላቻ ፖለቲካ እና የቋንቋ ፌደራሊዝም፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የአብሮነትና የአንድነት የዘመናት እሴት ክፉኛ የሸረሸረ ከመሆኑም በላይ፣ ዜጎች በጠራራ ፀሐይ እንደ ከብት በስለት እንዲታረዱ፣ በድንጋይ እንዲወገሩና በእሳት ተለብልበው እንዲሞቱ ምክንያት ሊሆን በቅቷል፡፡ “በቃ!” ሊባል ይገባል፡፡
ይህ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመ ድርጊት ማንም ሰብዓዊነትን የተላበሰ ፍጡር በጽኑ ሊያወግዘው ይገባል፡፡ ባልደራስ በተከናወነው ዘግናኝና ፍፁም ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በእጅጉ ያዘነ መሆኑን እየገለፀ፣ በዚህ ድርጊት ትዕዛዝ በሰጡ አካላት ላይ እና ተሳታፊ በሆኑት ላይ ሁሉ ግልጽ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂዎች ለህግ እንዲቀርቡ በአጽንኦት ይጠይቃል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
መጋቢት 9/2014
  አዲስ አበባ
Filed in: Amharic