>

የፋኖ ሻለቃ ሩሲያ ይዝመት፡ የአብርሃም ሃኒባልን ታሪክ ይድገም! (መስፍን አረጋ)


የፋኖ ሻለቃ ሩሲያ ይዝመት፡ የአብርሃም ሃኒባልን ታሪክ ይድገም!

መስፍን አረጋ



ያገራትንና ግንኙነት በተመለከተ፣ ‹‹ቋሚ ጥቅም እንጅ ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የለም›› (There are no permanent enemies, and no permanent friends, only permanent interests) የሚል አባባል አለ፡፡  ባለመታደል ግን ይህ አባባል ለኢትዮጵያ አይሠራም፡፡  ኢትዮጵያ መሠረታዊና ዘላለሚዊ የሆነች ጠላች አለቻት፡፡ ይህችም ጠላት ገብጽ፣ ወይም አሜሪቃ፣ ወይም ፈረንሳይ ወይም ጣልያን አይደለችም፡፡  ስኮተትላንድም፣ ሰሜን አይርላንድም፣ ዌልስም አይደለችም፡፡  ይህች የኢትዮጵያ መሠረታዊና ዘላለማዊ ጠላት፣ እንግሊዝ የምትባል መሠሪ አገር ናት፡፡  

ኢትዮጵያን በተመለከተ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በሚከተለው የሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) እሳቤ ላይ ነው፡፡  

“የጦቢያ አያሌ ብሔረሰቦች የነጭ ባርያ የመሆን ምርጫቸውን የነፈጓቸው መሠረታዊ ዓላማቸው በነጭ ተጽእኖ መቃብር ላይ የጥቁርን ልዕልና መገንባት የሆነው የሐበሻ መሪወች ናቸው” (The numerous tribes who inhabit the Ethiopian state are being forcibly kept from European colonialism by Abyssinian rulers whose aim is to act as champions of all black people so as to attack and destroy Western culture) 

የጦቢያ ዐበይት ችግሮች (በተለይም ደግሞ ከጎጠኝነት የሚመነጩ ችግሮች) ክራቸው ቢመዘዝ፣ ሂደው፣ ሂደው ጫፋቸው የሚገኘው፣ የፕሮቻዝካ ፀረጦቢያ እሳቤ የሚተገበርባቸው ዘዴወች እየተዘየዱ ለሁሉም ምዕራባዊ አገሮች ከሚሠራጩበት ከቁጥር አስር ዳውንኒግ መንገድ (Number 10 Downing Street) ነው፡፡ አሜሪቃን ጨምሮ ሁሉም ምዕራባውያን አገሮች የኢትዮጵያ ፖሊሲያቸውን የሚያረቁት፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ጠበብቶች ናቸው በሚባሉት በመሠሪወቹ በእንግሊዞች ምክር መሠረት ነው፡፡  ባሜሪቃና በሌሎች የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውስጥ የኢትዮጵያን ጉዳይ በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአንግሊዝ ዘር ያላቸው ፀረጦቢያወች ወይም ደግሞ በነዚህ ፀረጦቢያወች የተመረዙ ባለስልጣኖች ናቸው፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሳይደግስ አይጣላምና፣ አገራችን ጦቢያ ዘላለማዊ ጠላት ብትኖራትም፣ በዚያው አንጻር ደግሞ ዘላለማዊ ወዳጅ የሆነች፣ በጭንቅ ቀን ሁልጊዜም የምትደርስላት አገር አለቻት፡፡  ይህችም የጦቢያ ዘላለማዊ ወዳጅ ሩሲያ ናት፡፡  ባድዋ ጦርነት ጊዜ የሩሲያ ቄሳር፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ እስታሊን፣ በሶማሌ ወረራ ጊዜ ብሬዥኔቭ፣ የጦቢያ ወዳጅነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡  አሁን ላይ ደግሞ የምዕራባውያኑ ኖቤል ተሸላሚ የሆነው ጎጠኛው ዐብይ አሕመድ በምዕራባውያን እየታገዘ የጦቢያ ምሰሶ በሆኑት በአማራ ሕዝብና በተዋሕዶ ላይ የሚያወርደውን መቅጸፈት የሚቃወመው የፑቲን አስተዳደር ነው፡፡  

ሩሲያኖች ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ምንም ሳይጠይቁና ሳያገኙ ነው፡፡  አሜሪቃ በጦቢያ ላይ የገነባችው አንድ ነገር ቢኖር ለስለላ የምትገለገልበትን ቃኘው ጣቢያን (Kagnew Station) ብቻ ነበር፡፡  በንጉስ ኃይለ ሥላሴ በምትደዳደረው ጦቢያ ውስጥ የሚገኘውን ብቸኛውን ነዳጅ ማጣሪያ አሰብ ላይ የገነቡት ግን ኮሚኒስቶቹ ሩሲያኖች ነበሩ፡፡  

መውደድ አይምሯዊ ሳይሆን ልቦናዊ ስለሆነ ምክኒያት አልባ ነው፡፡  የሚወድህ ሰው አረክለትም አላረክለትም ይወድሃል፡፡  ሩሲያም የፑሽኪንን አገር ኢትዮጵያን የምትወዳት ስለምትወዳት ብቻ ነው፡፡  የሩሲያ አምባሳደር ጥርት ያለ አማረኛ የሚናገሩ መሆናቸው ብቻ፣ ሩሲያ ስለ ኢትዮጵያ ስላላት አመለካከት ብዙ ይናገራል፡፡  በሌላ በኩል ግን መኻል አዲሳባ ላይ ብዙ ጋሻ ርስት የያዘው የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ የኤምባሲው ሠራተኞች ኣማረኛ እንዲናገሩ ማበረታታት ይቅርና፣ የእንግሊዘኛ ትምህርት ቤት ከፍቶ ንግዱን እያጧጧፈ፣ የኢትዮጵያን ልጆች አማረኛ መናገርና ዲንጋ መወርወር ያስቀጣል እያለ በማስተማር፣ ከገዛ ሕዝባችን በሚዘርፈው በገዛ ገንዘባችን እገዛ አገራችን ላይ ያዋርደናል፣ ይልቁንም ደግሞ እንዲያዋርደን ፈቅደንለታል፡፡  

ያገራቸን የጦቢያ የጭንቅ ቀን ደራሽ ሩሲያ፣ አሁን ላይ ደግሞ እሷ ራሷ በተወሰነ ደረጃ ጭንቅ ላይ ትገኛለች፡፡  ምዕራባውያን ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው እሷ ላይ በመረባረብ ህልውናዋን ክፉኛ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡  ስለዚህም፣ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይባል ማናቸውም አይነት እገዛ ያስፈልጋታል፡፡ የኢትዮጵያን ወዳጅ ሩሲያን በተቻለው አቅሙ ቢያግዛት የሚወደው ደግሞ ኢትዮጵያን የሚወደው የአማራ ሕዝብ ነው፡  የአማራ ሕዝብ ደግሞ ባሁኑ ጊዜ እሱ ራሱ ጭንቅ ላይ በመሆኑ፣ ሩሲያን እምብዛም ማገዝ ባይችልም፣ ያለውን እስከወረወረ ድረስ ፈሪ አይባልም፡፡   

በተለይም ደግሞ አንድ ሻለቃ ወይም ከዚያ በላይ የአማራ ፋኖ ወደ ሩሲያ ቢዘምትና አስፈላጊው ሥልጠናና መሣርያ ተሰጥቶት ዩክሬን ላይ ቢሰማራ፣ አፍሪቃን ዳግም ቅኝ መግዛት አለብን ብሎ የፎከረው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) በወዶ ዘማችነት ሽፋን የሚያሰማራቸውን የእንግሊዝ ወታደሮች እየገረፈ ልክ በማስገባት ለሩሲያ ከፍተኛ ውለታ ሊውልላት ይችላል፡፡  ይህ ውለታ ደግሞ የጦቢያንና የሩሲያን ወዳጅነት በደም ያስተሳስረዋል፡፡  ፋኖ ደግሞ ከሩሲያውያን የሚቀስመውን የመሣርያ አጠቃቀምና ወታደራዊ ጥበብ በመጠቀም፣ የአማራ (ስለሆነም የጦቢያ) ጠላት የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በቀላሉ አክስሞ የአማራን (ስለሆነም የጦቢያን) ቀጣይነት ማረጋገጥ ይችላል፡፡  የፋኖ ሩሲያ መዝመት፣ ጥቅሙ ለሩሲያ ብቻ ሳይሆን ራሱ ፋኖ ለቆመበት ዓላማም ጭምር ነው፡፡  

ሰው ሁሉ እኩል ነው (all men are created equal) የሚል የወረቀት ሕገመንግሥት በመጻፋቸው የሚመጻደቁት ጆርጅ ዋሽንግተን (George Washington) እና ቶማስ ጀፈርሰን (Thomas Jefferson) ባሮቻቸውን ጽፈት ለመማር ሞክራችኋል በማለት ጣቶቻቸውን በሚቆርጡበት ዘመን፣  የሩሲያው ቄሣር ታላቁ ጴጥሮስ (Peter the Great) ግን፣ ኦቶማን ቱርኮች በባርነት የሸጡለትን የታላቁን ቀያኔ (poet) የእስክንድር ፑሽኪንን (Alexander Pushking) አያት፣ ኢትዮጵያዊውን አብርሐም ጴጥሮስ ሃኒባል (Abram Petrovich Hannibal) የክርስትና ልጁ (godson) አድርጎ፣ ፈረንሳይ ድረስ ልኮ በመድፈኛነት አስተምሮ በማስመረቅ (royal artillery academy of La Fere) የሩሲያ ቄሣር ጦር (Imperial Russian Army) ዋና ጀነራል (general-in-chief) አድርጎት ነበር፡፡  ፋኖወች ዩክሬን ቢዘምቱ ደግሞ፣ በጀግንነታቸው ሩሲያንም ጦቢያንም አኩርተው፣ የጦቢያን ዘላለማዊ ጠላት እንግሊዝን አሳፍረው፣ ጥቂቶቹ ፋኖወች አያታቸው አብርሐም ሃኒባል ከደረሰበት ከፍተኛ ወታደራዊ ደረጃ የማይደርሱበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡   

የጦቢያ ዘላለማዊ ጠላቶች የሆኑት ምዕራባውያን ለአማራ ሕዝብም ዘላለማዊ ጠላቶች ናቸው፣ ምክኒያቱም አማራና ጦቢያ አንድ አካል አንድ አምሳል እንደሆኑ፣ አማራ ያለ ጦቢያ፣ ጦቢያ ያለ አማራ እንደማትኖር ስለሚያውቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አደረገችልኝ፣ አላደረገችልን ሳይል በኢትዮጵያዊነቷ ብቻ ከነፍሱ በላይ የሚወዳት የአማራ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡  ሌሎቹ ግን በኢትዮጵያ ላይ ሰፍተውና ተንሰራፍተው፣ ሁሉን በጃቸው በደጃቸው አድርገው፣ በጨሳፊ (rocket) ፍጥነት ቢሊየነሮች ሁነውባት እንኳን፣ የጦቢያ ስም ሲጠራ የዘራቸው ያንዘረዝራቸዋል፣ የጦቢያን ባንዲራ ሲመለከቱ ደግሞ ዓይናቸው ደም ይለብሳል፡፡  

የዩክሬን ጦርነት ምዕራባውያን ከሩሲያ ጋር የሚያደርጉት የውክልና ጦርነት (proxy war) እንጅ ከዩክሬን ብሔራዊ ጥቅም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡  የምዕራባውያን ዓላማ ዓለምን ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠሩ እንቅፋት የሆነችባቸውን ሩሲያን ክፉኛ በማሳፈር፣ ከቻሉም ደግሞ ድምጥማጧን በማጥፋት፣ ለሌኛዋ ተገዳዳሪያቸው ለቻይና ማስፈራሪያ ማድረግ ነው፡፡  ከሩሲያ ጋር እየተዋጉ፣ ትኩረታቸው ቻይና ላይ መሆኑ በግልጽ የሚመሰክረው፣ የዩክሬን ጦርነት በዩክሬን ስም ይሁን እንጅ ለዩክሬን ሲባል አለመሆኑን ነው፡፡  

ዩክሬን የተጎዳቸው ያልታደለች የጦር ሜዳ በመሆኗ ነው፡፡  ምናልባትም ደግሞ የኑክሌር አርማጌዶን ልትሆን ትችላለች፡፡  ለዚህ ደግሞ ዩክሬናውያን ከማንም በላይ መውቀስ ያለባቸው ዜሌንስኪ (Zelensky) የሚባለውን የራሳቸውን ቧልተኛ መሪ ነው፡፡  ይህ ሩሲያጠል (russophobic) ግለሰብ፣ የኑክሌር ትራጀዲን ከቲቪ ኮሜዲ መለየት የማይችል፣ በቤቱ ውስጥ ያለው ነጻነት ጎረቤቱን ለማስሸበር ቀርቶ ለመረበሽ መብት እንደማይሰጠው ያልተረዳ፣ ለኪውባ (Cuba) የሠራው ለዩክሬን መሥራት እንዳለበት የማያውቅ ወይም እንዲያውቅ ያልተደረገ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምዕራባውያን እንደ ትልቅ ጀግና እየቆጠሩት፣ ዘረኛው ዊንሰተን ቸርችል (Winston Churchill) በየቦታው እየተዘዋወረ ቱልቱላውን ይነፋ እንደነበረው፣ እሱንም ቱልቱላውን እያስነፉት ከፍተኛ አድናቆት እስከቸሩት ድረስ፣ ዩክሬኖች ጨርሰው ቢያልቁ ግድ የሌለው አረመኔ ነው፡፡

ነገሮችን ሳሰላስላቸው የዩክሬኑ ዜሌንስኪ እና የጦቢያው ዐብይ አሕመድ በተወሰነ ደረጃ ይመሳሰሉብኛል፡፡  በመጀመርያ ደረጃ ሁለቱም አጭበርባሪ ተውነቴኞች ናቸው፡፡  የዜሌንሰኪ ዓላማ ለዩክሬን የቆመ መስሎ ዮክሬኖችን እና ሩሲያኖችን በማጨፋጨፍ ምድሩን ባድማ አድርጎ የስላቮችን አገር የምዕራባውያን የርሻ መሬት (lebensraum) በማድረግ የነ ሂትለርን ምኞት ማሳካት ነው፡፡  የኑክሌር ጦርነት እንዲቀሰቀስ የሚቋምጠውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡  የዐብይ አሕመድ ዓላማ ደግሞ አንዴ ከትግሬ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአማራ ጋር የወገነ እየመሰለ፣ በአማራና በትግሬ መካከል እሳት እየለኮሰና እያቀጣጠለ፣ አማራና ትግሬን እርስ በርስ አጫርሶና አወዳድሞ፣ የአማራና የትግሬን ምድር ባድማ በማድረግ የኦሮሞን አጼጌ (Oromo Empire) በመላው ጦቢያ ላይ መመሥረት ነው፡፡            

ዩክሬኖችን ከሩሲያኖች ጋር እንዲያጨፋጭፍ ዜሌንስኪን በገፍ የሚያስታጥቁት ምዕራባውያን፣ ዘወር ብለው ደግሞ ዩክሬኖች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጸመ በማለት የአዞ እንባ እያለቀሱ፣ የሩሲያ ጦር የበላይ አዛዥ የሆነውን ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ (war criminal) ብለው በይፋ ከሰውታል፡፡  በዚህ እሳቤያቸው መሠረት ትግራይ ላይ ተፈጽመዋል ብለው በሰፊው ለሚያስወሯቸው ወንጀሎች የመጀመርያው ተጠያቂ ማድረግ የነበረባቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆነውን ዐብይ አሕመድን ነበር፡፡  ዐብይ አሕመድ ግን መለስ ዜናዊን የተካ፣ መለስ ዜናዊን በሚያስንቅ ሁኔታ አማራን የሚነክስላቸው ውሻቸው ነው፡፡  በአማራ ሕዝብ ላይ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ስለተፈጸሙት፣ በማስረጃ የተደገፉ፣ ሊካዱ የማይችሉ ጭፍጨፋወች ትንፍሽ ሳይሉ፣ ትግራይ ላይ ተፈጸሙ ስለተባሉ ማስረጃ ስለሌላቸው ወንጀሎች አለመጠን የሚጮኹት፣ ፋኖን በጦር ወንጀለኝነት ፈረጀው በማጥፋት፣ የአማራን ሕዝብ ለወያኔና ለኦነግ ጭራቆች አሳልፎ ለመስጠት ነው፡፡  ስለዚህም ፋኖ ምዕራባውያንን ዩክሬይን ላይ መዋጋት ያለበት፣ ለሩሲያ ሲል ብቻ ሳይሆን፣ ለራሱም ሕልውና ጭምር ነው፡፡

EMAIL: mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic