>
5:13 pm - Sunday April 20, 8138

እጅግ አደገኛ በሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ቃላቶች የታጨቀው የኦሮሚያ ብልጽግና መግለጫ!! (አሳዬ ደርቤ)

የኦሮሚያ ብልጽግና መግለጫ!!

አሳዬ ደርቤ

*…. መግለጫው ተያይዞ ቀርቧል…!!!
 
➔እጅግ አደገኛ በሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ቃላቶች የታጨቀ፤
➔ጽንፈኝነትን በማውገዝ ጀምሮ- ጽንፍ በያዘ ዛቻ የተጠናቀቀ፤
➔በስሜትና በግንፍልተኝነት የተሞላና ከኃላፊነት መንፈስ ሙሉ በሙሉ የራቀ፤
➔በአማራ ክልል የምትገኘውን አውራ ጎዳና ቀበሌን ወደ ኦሮሚያ ክልል የወሰደ፤
➔ቁጣውን ለሕዝብ አከፋፍሎ ‹‹የአማራ ጽንፈኞች ከክልላችን ገብተው የፈጸሙት ጥቃት መላው ሕዝባችንን አስቆጥቷል›› በሚል ድምዳሜ የእርስ በእርስ እልቂት መለኮስን የወደደ፤
➔የአማራ ጽንፈኛ ከሚለው ሃይል በተጨማሪ በአማራ ብልጽግና እና በክልሉ ሚዲያዎች ላይ የቁጣ መዓት ያወረደ፤
➔የኢሰመጉ መግለጫን እና እውነትን በካዴ መልኩ ‹‹የአማራ ጽንፈኞች ከክልሌ ገብተው ጥቃት ፈጽመዋል›› በሚል ክስ ምንጃር ሸንኮራ ገብቶ የአማራ ገበሬዎችን ለመምታት ያቀደ…… እጅግ አደገኛ መግለጫ ነው፡፡
ከሁለት ወር በፊት ከ200 በላይ አማራዎች በወለጋ ሲገደሉ ቁጣውን ቀርቶ ኀዘኑን በወጉ መግለጽ የተሳነው አካል… ዛሬ ላይ ዛቻውን እና የጥፋት እቅዱን ይዞ እንዲመጣ ያስገደደው ምክንያትም… ሰለባ ይሆን ዘንድ የፈረደበት የአማራ ሕዝብ በአገር ሥም ለብልጽግና ወንበር በመታገልና በየስፍራው በመገደል ፈንታ እራሱን መከላከል መጀመሩ ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ጉዳይ የሚገደን ኃይሎች ሁሉ በተረኝነት እና በዘረኝነት መሃከል የሚወዛወዘው ይህ ሥርዓት በተግባሩም ሆነ በንግግሩ ውስጥ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ሁሉ የሮዋንዳን እልቂት የመድገም እቅድ መኖሩን የሚገልጹ ስለሆኑ… ሕዝባችን እንዲጠነቀቅ ከማድረግ ባለፈ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማሳወቅ ግድ ይለናል፡፡
“ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ለማንም ለምንም አይጠቅምም!”-የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ለማንም ለምንም አይጠቅምም” ሲል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ ለማንም ለምንም አይጠቅምም !
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ
ኢትዮጵያ በልጆቿ ውድ መስዋዕትነት የተገነባች ህብረ-ብሔራዊት ሀገር መሆኗ እሙን ነው፡፡ በዘመናት ከውጭና ውስጥ ሲደቀኑባት የነበሩ ፈተናዎችን ድል በመንሳት አንድነቷን ጠብቃ እነሆ ዛሬ ደርሳለች፡፡ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ በፈተና ውስጥ ሆና በመደመር መንገድ ተጉዛ ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ጋር አንገት ላንገት ተናንቃ ትገኛለች፡፡
ባለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎች የተጋላጭነታችን መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በተሟላ ሁኔታ ዘግተን ባለማለፋችን በጦርነትና በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንቆይ አድርጎናል፡፡በጋራ ታሪክና እሴቶቻችን ላይ የጋራ እይታና መግባባት መፍጠር ተስኖን ግራና ቀኝ ስንጓተት እንስተዋላለን፡፡ህብረ-ብሔራዊነትና ብዝሃነትን የውበታችን ምንጭና መድመቅያችን አድረገን እንደ ጸጋ ከማየትይልቅ እንድ ስጋት ማየታችን ዋጋ ሲያስከፍልን ኖሯል፡፡ባጠቃላይ ሀገራዊ መግባባትን አለመፍጠራችን በየዘመናት የቤት ስራ ሆኖብን እዚህ ደርሷል፡፡
በመሆኑም  ባላግባቡን ጉዳዮች ላይ መግባባትን ፈጥረን  የችግሮቻችንን ምንጭ ለማድረቅና ሀገረ-መንግስቱን ለማጽናት የተጀመረው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ሀገራዊ ምክክሩ ተሳክቶ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ  ከግጭት አዙሪት ለመላቀቅ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በመደገፍ ላይ እገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ የህብረ-ብሔራዊ አንድነትና የወንድማማችነት ጸር የሆነው ጽንፈኝነት የዜጎች መፈናቀል፤ ሞትና ሰቆቃ መንስኤ በመሆን የሀገራዊ መግባባትና ምክክር ጋሬጣ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከትላንት እስከ ዘሬ በህዝቦች መካካል የኖረው ማህበራዊ መስተጋብር ወንድማማችነት፤ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ለሀገራዊ ሉአላዊነትና ክብር አብሮ መቆም ሆኖ ሳለ፤ የህዝባችንን እሴት የማይመጥኑ ጽንፈኞች በሚፈጥሩት መሳሳብ ቀላል የማይባል ሀገረዊ ጉዳትን በማስከትልና እሴቶቻችንን በመሸርሸር ላይ ይገኛሉ፡፡
የነዚህ ጽንፈኞች መሰረታዊ ዓላማ  የኦሮሞና የአማራን ህዝብ በማጋጨት ሀገርን ማፍረስ ይቻላል ተብሎ በወያኔ የተወጠነውን ሴራ  ማሳካት ነው፡፡ የነኚህን ጽንፈኛ ሀይሎች እኩይ ተግባርን አንድ ቦታ ማስቆም ካልተቻለ በሀገራችን ሌላ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል፡፡
እዚህም እዝያም የሚታየውን ጽንፈኝነት እያባባሰ ያለው አንዱ ምክንያት በባህሪው ላይ ተመሳሳይ እይታና አቋም አለመያዛችን ነው፡፡በዚሁ መሰረት ጽንፈኝነት ከየትም ይምጣ ከየት እሳቤውና ተግባሩ ጸረ-ህዝብ መሆኑን ተገንዝቦ በጋራ  መታጋል ሲገባን ጣት መቀሳሰር ጎልቶ ይታያል፡፡የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ጽንፈኝነት የትም ይብቀል የት ጸረ-ህዝብ መሆኑን በጽኑ አምኖ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሰረት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በሚደርገው ትግል ውድ መሰዋትነት እየከፈለ ይገኛል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚከፈለው መሰዋትነት ጽንፈኝነት ሀገር-አፍራሽ መሆኑን በጽኑ አምነን ሀገርና ህዝብን ለመታደግ እንጂ  በአማራ ስም ለሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎች እድል ለመከፈት አይደለም፡፡
ከዚህ አንጻር የአማራና የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀንደኛ ጠላት የሆኑት በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ  ጽንፈኛ ሀይሎች  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዘልቀው በመግባት በሰላማዊ ዘጎችና ጸጥታ አካላት ላይ የፈጸሙት አጸያፊ ድርጊት የክልሉን ህዝብ ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ይህ ጽንፈኛ ሀይል ስለፈጸመው አጸያፊ ድርጊት  የክልሉን የመንግስት ሚዲያ  ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሲያስተጋቡ፤ ጥላቻን ሲሰብኩና የግጭት ነጋሪት ሲጎስሙ በዝምታ ማየት ተገቢ አለመሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጽኑ ያምናል፡፡ 
ሕብረ-ብሄራዊነትና ወንድማማችነት ጽኑ የኢትዮጵያ አንድነት መሰረት ነው፡፡መከባበር፤ ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም አብሮ መቆም፤ ከልዩነት ይልቅ የጋራ እሴቶቻችንን ማጽናት ዘላቂ መፍትሄ ነው፡፡ ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፡፡ ለማንም ለምንም አይጠቅምም፡፡ ጸረ ህዝብ እሰከ ሆነ ድረስ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ በጋራ ልንታገለው ይገባል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ፊንፊኔ
መጋቢት 26፣ 2014
Filed in: Amharic