ሩስያን ደግፋችሁ ከጎኗ ለቆማችሁ!?
አንዱ ዓለም ተፈራ
በዩክሬን ላይ እየተደረገ ያለውን ወረራ በሚመለከት ይህ ሶስተኛ ጽሑፌ ነው። ዛሬም በዩክሬን የፑትን ወረራ እየተካሄደ ነው። አሁንም ዩክሬናዊያን ባገራቸው እየተጨፈጨፉ ነው። ልክ በኢትዮጵያ አማራዎች በገዛ አገራቸውና በገዛ ቤታቸው እየታረዱና እየተባረሩ እንዳሉት ሁሉ፤ ዩክሬናዊያን በገዛ አገራቸው እየታረዱና እየተጨፈጨፉ ናቸው። ተመሳሳይነት ባለው መልክ፤ አረመኔያዊነት በሁለቱም ቦታዎች ያለገደብ ተለቋል። ለእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በአገራችን ያለው አሰቃቂ ሁኔታ ነው ወይንስ ሩሲያ በዩክሬናዊያን ላይ የምታደርገው ዘመቻ የመጀመሪያው ጉዳያችን? ይህ የኢትዮጵያዊያን ለሩሲያ ድጋፍ መነሳትና ለማመን የሚያስቸግር እውነታ፤ በትክክል ከሕዝቡ ፍላጎት የመነጨ ነው? ወይንስ የአገሪቱን የውስጥ ውጥረት ለማደብዘዝና የውጩን ጉዳይ ትክረት ለማግኘት በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የቀመረው ማዘናጊያ? ወይንስ ጥቂት የሩሲያ ቅጥረኞች ለተጣለላቸው ፍርፋሬ ሩሲያን ለማገዝ ያደረጉት ስሌት? ጤነኛ ሰው ይስማ! በዝሆን መንገድ ላይ ባለ ጭቃ ውስጥ ያለች እንቁራሪት፤ የዝሆኑን እግር ዱካ ጭቃ ነካው ብላ ልትጠርግለት ብትነሳ፤ መጨረሻዋ ምን እንደሚሆን መገመቱ አይከብድም። ቀደምቶቻችን ያልበላውን ማከክ፤ በራስ ቆዳ ላይ ቁስል መፍጠር ነው! ብለዋል።
በርግጥ ባገራችን ሥራ ያጣው ወገናችን ብዙ ስለሆነ፤ ሥራ ፍለጋ ሕይወታቸውን ለመሥጠት የተነሱትን፤ ይሁንላችሁ ከማለት በስተቀር ሌላ የምለው ነገር የለም። በሌላ በኩል ግን፤ ለፍትኅና ለነፃነት እንቆረቆራለን ለምንል፤ ባሁኑ ሰዓት በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የሚጠይቀው መስዋዕትነት ይሄ ነው ወይ? አዎ! ሩሲያ የምታደርገው በዩክሬን የፑትን ወረራ፤ የዓለምን የፖለቲካ መድረክ አጥለቅልቆታል። ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ቢዞሩ፤ ይኼው ዜና ብቻ ነው የዜና አውታሮችን ያጣበባቸው። በዚህ መሓል፤ እያንዳንዳችን የምናገኘው መረጃ ሰለባዎች ሆነናል። የመረጃ ምንጮቻችን ደግሞ፤ በምንኖርበት ቦታ፣ በቦታው ባለው የቴክኖሎጂ ምጥቀትና አቅርቦት፣ በየግላችን ባለን አርቆ የማስተዋልና ምንጮችን የመመርመር ፈቃደኝነት ይወሰናል። ማሰሪያው ደግሞ፤ ምን ያህል የቀረበልንን መረጃ የማመዛዘንና ለሌሎች የተለዩ መረጃዎች ቦታ ሠጥቶ ለማነጻጸር ያለን ፍላጎት ይገዛናል? ነው። በተጨማሪ ደግሞ፤ በኑሯችን ላይ የሚኖረን ቅደም ተከተል የማስቀመጥ ችሎታችን ትልቅ ቦታ አለው። እውነት ኢትዮጵያዊያን ዩክሬን ሄደው ለሩስያ ሕይወታቸውን መሥጠቱ ተገቢ ነው? እውነት ይሄ ነው የኢትዮጵያዊያን አጣዳፊ ጉዳይ? ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ ማሾሪያው።
ከአገራችን አጣዳፊ ጥያቄዎች መካከል፤ አምስት ጎልተው የሚታዩ አሉ።
የመጀመሪያው፤ የአንድ አገር አንድ ሕዝብነት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያዊ የሚባል ደብዝዞ፤ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጋምቤላ፣ እና የመሳሰሉት የትውልድ መግለጫዎች፤ የፖለቲካ ልብስ ተጠልቆላቸው፤ የማንነታችን መገለጫዎች ሆነዋል። ሰንደቅ ዓላማ ተፈጥሮላቸው፤ የየራሳቸው መንግሥት ሆነዋል። ይሄን ነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃኝ ብሎ፤ የዚህን የፖለቲካ መስመር ፈጣሪና አራማጅ የሆነውን የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ከሥልጣን ያባረረው። ነገር ግን፤ የጠገበው ጅብ ሄዶ የራበው ጅብ በቦታው ተተክቶ፣ ያው ሰለባ አለልኝ! ብሎ፣ ልጋጥና አጥንት ላስቀር! ነግሦ፣ አሁንም ያው ክፍፍል፤ አሁንም ኢትዮጵያን ለመበታተን፤ አማራውን እናጥፋው! በቦታው ነግሧል።
ሁለተኛው፤ የመብትና ኃላፊነት ጉዳይ ነው። መንግሥት የበላይ፤ ሕዝቡ የበታች የሆነባት ኢትዮጵያ፣ መንግሥት ባለመብት፤ ሕዝቡ ደግሞ ተገዢ ነው። ትናንት ትግሬ መሆን ከወርቃማ ዘር መብቀል፤ ሌሎች ውዳቂዎች የሆኑበት እውነታ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኦሮሞ መሆን የበላይነት፤ ሌሎች ደጎም የበታች የሆኑባት ኢትዮጵያ ነው ያለችን። መንግሥት የአገሪቱ ሳይሆን የአንድ ክፍል አገልጋይ በሆነባት ኢትዮጵያ፣ መብት ማለት ለሩሲያ ሄዶ መሞት ነው! ብሎ የሚያምን ካለ፤ ይህ ግለሰብ አገሩን አያውቅም! አገሩን አይወድም! ለአገሩና ለወገኑ ብቻ ሳይሆን፤ ለራሱም የማይሆን ነው።
ሶስተኛው፤ ትክክለኛ ሕገ-መንግሥትና የሕግ የበላይነት ጉዳይ ነው። ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት በቦታው ሳይኖር፤ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት የሕልም እንጀራ ናቸው። በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ሕግ ቦታ አልነበረውም። ሕግ ማለት፤ ገዥው የሚፈልገውን ማድረግ ማለት ነበር ። በአሁኗ ኢትዮጵያም ሕግ ቦታ የለውም። አክራሪ ኦሮሞዎች የሚፈልጉትን ማድረግ ነው ሕጉ! በዚህ ሀቅ መረጋጋትና ልማት ቀርቶ፤ “አገር አለ ወይ!” የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው። ዛሬም እንደትላንቱ አማራን መጨፍጨፍና ሰላምተኛ አማራዎች ላይ ጉልበትን መፈተሽ፤ የዕለቱ አጀንዳ ሆኗል። ይሄ በሆነባት ኢትዮጵያ፤ ለሩሲያ ሄዶ መዋጋት መብቴ ነው ለሚል፤ ጤንነቱን ሐኪም ይፈትሸው ከማለት ያለፈ የምለው የለም።
አራተኛው፤ የሕዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚመለከት ጉዳይ ነው። አንቺ ኦሮሞ ሆነሽና በኦሮሞ ክልል ነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የምትሳተፊው፤ አንተ ሶማሊ ሆነህና በሶማሊያ ክልል ነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የምትሳተፈው፤ አማራውም እንዲሁ፣ አፋሩም እንዲሁ፣ ሲዳማውም እንዲሁ፣ ወላይታውም እንዲሁ፣ አዲስ አበቤውም በባሰና በከፋ ሁኔታ፣ ከተባለ፤ የት ላይ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኢትዮጵያዊያን ቦታ! እንደ ኢትዮጵያዊ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን በሌሉበት ቦታ፤ በአገር ፖለቲካ የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ አለ ወይ? በዚህ ሀቅ ለሩሲያ ሄዶ መሰለፍ፤ የፖለቲካ ተሳትፎ ነው! ብሎ የሚያምን ካለ፤ ብዙ የአእምሮ ሐኪሞች ያስፈልጉናል።
አምስተኛው፤ መንግሥት የበላይ ሕዝቡ የመንግሥት አሽከር የሆነበት ጉዳይ ነው። ሕዝቡን የማይወክልና በሕዝቡ የማይመራ መንግሥት ባለበት አገር፤ ፍትኅ፣ ሰላምና ልማት መሳለቂያ የቅንጦት ቃላት ናቸው። መንግሥት የመሬት ባለቤት ሆኖ፤ ሕዝቡ ጢሰኛ መሆኑ፤ ፈጣሪነትንና ታታሪነትን ያቀጭጫል። ከልብ የመሥራት ፍላጎትን ያሸሻል። ታዲያ፤ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት፤ ፍትኅ፣ ሰላምና መረጋጋት ባገር እንዲሰፍን መጠየቅ ነው። ከዚህ አልፎ ሩሲያ ሄጄ ለፑትን አገልጋይ ሆኜ ልሙት ማለት፤ አሁንም የአእምሮ በሺተኝነት ነው።
በኢትዮጵያ አገራችን፤ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፤ የሸኔ ወንበዴዎች፣ አማራዎችን በየሚኖሩበት ቦታና በየቤታችው እያረደ ነው። አማራዎች ራሳቸውን ለመከላከል በፋኖ ተደራጅተው ቢነሱ፤ በፌዴራል መንግሥቱ፣ በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች፣ በኦሮሞ ክልል የብልፅግና ፓርቲ መሪዎችና በኦነግ ሸኔ እየተዘመተባቸው ነው። ይህ ለያንዳንዱ አማራ የሕልውና ቅደም ተከተሉ ዘመቻ፤ የመጀመሪያው የዝርዝር ሰነዱ ሰፋሪ ነው።
ግዙፉ ሩሲያ በትንሿ ዩክሬን ላይ ያደረገው የፑትን ዘመቻና ያደረሰው ጥፋት፤ የፋሽስቱ ሞሶሎኒ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ካደረገው ወረራና ጭፍጨፋ ጋር በብዛት ይመሳሰላል። በዚህ ሰዓት፤ ከሩሲያ ጋር ለመዝመት መነሳት፤ የጣሊያኑ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የፋሽስቱን የጣሊያን ወታደሮች እንዲዘምቱ ከመባረክ፣ የሩሲያ ቤተክርስትያን የሩሲያ ሕዝብ ዩክሬንያዊያንን ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ ከመስበክ ጋር ያሰልፋል። ለአንድ አፍሪካዊ ግለሰብ፤ አፍሪካዊያንን ዝቅተኛ ፍጡር አድርገው የሚመለከቱና እንደዚያም አድርገው የሚያስተናግዱት፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ነጮች ናቸው፤ አሜሪካዊያን፣ አውሮፓዊያን፣ ዩክሬናዊያን፣ ሩሲያዊያን በሙሉ። በዚህ ረገድ ግን፤ ከሁሉም በላይ ሩሲያዊያን ይከፋሉ። ታዲያ ለኒህ ነው ጥብቅና ኢትዮጵያዊያን የሚቆሙት! ሕይወታቸውን የሚሠጡት!
ፑትን አምባገነን መሪ ነው። ይህ መሪ፤ እንኳንስ ለትንሿ አገር የዩክሬንና ሕዝቧ፤ ለራሱ ወታደራዊም ሆነ ሲቪል መሪዎች አክብሮት የለውም። ይልቁንም ንቀት ያለውና አረመኔ ግለሰብ ነው። እንደ ሌሎች አምባገነኖች ሁሉ፤ ፍጹም ታዛዥነትን እና አጎብዳጅነትን ይጠይቃል። ይሄንን በየቦታው የምናየው ነው። እናም ፑትን ለማንም ግድ የሌለውና ራሱን ብቻ ወዳድ መሪ ነው። በኔ እምነት፤ ይሄ ሰው የአሜሪካው ያለፈው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያለልጓም ማለት ነው። ታዲያ ለዚህ ግለሰብ ነው ሕይወታቸውን ለመሥጠት ኢትዮጵያዊያን የሚሰለፉት!
ማንም አማራ፤ ፋኖን ከመቀላቀል ይልቅ ለሩሲያ ሊሰለፍ ከተነሳ፤ ደግሜ እላለሁ፤ አእምሮው መመርመር አለበት! አማራ በየቦታው እየተጨፈጨፈና “አማራ ነን!” ብለው የሚገዙት፤ የፌዴራል መንግሥቱ አጎብዳጅ ሆነው ገባር ሲያደርጉት፤ ለሩሲያ ሄጄ ልሙት ማለት፤ ጤና ማጣት ነው። ባሁን ሰዓት፤ አማራና የአማራ ተወልጅ የሆነ ሁሉ፤ በአንድነት ለአማራው ሕልውና መሰባሰብና መሰለፍ አለበት። አማራው መብቱን የሚያስከብረው ራሱና ራሱ ብቻ ነው። አማራው ፍኖን መጠበቅ መንከባከብና መደገፍ አለበት። የሚችል ይቀላቀል! የማይችል ይደግፍ! የአማራ መዳኛ ፋኖ ብቻ ነው። በውጪ አገር የምንገኝ የአማራ ተቆርቋሪዎች በሙሉ፤ በተናጠል የምናደርገው ዕርዳታ ውስን ውጤት ነው ያለው። በኛ የበጎ አድራጎት የአማራው ሕልውና በቋሚነት አይቀጥልም። አማራው ራሱን ችሎ፣ አልምቶና አፍርቶ ማደር ይችላል። አሁን ውጥረት የበዛበት፤ የሚወክሉት ትክክለኛ የአማራ ተቆርቋሪዎች ሆነ ባለመገኘታቸው ነው። እናም ጥቃት በየቦታው ሲደርስበት፤ እነሱ ስላልቆሙለት ነው።ራሱን እንዲከላከልና ትክክለኛ ተወካዮች ኖረውት ኑሮውን እንዲቀጥል፤ ግዙፍ የሆነ መሰባሰብ አድርገን፤ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጫና መፍጠር አለብን። ባንድ በኩል እኛ ገዝፈን ስንገኝ፤ የምናደርገው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አማራው ራሱን አደረጅቶ ሕልውናውን እንዲጠብቅ፤ ጠቀም ባለ መልኩ መርዳት እንችላለን። ይህና ይህ ብቻ ነው የኛ ኃላፊነት። እንዴት ለሚለው ቀላል መልስ አለኝ። የተደራጁ የአማራ ስብስቦች በአሜሪካ፣ በካናዳና በሌሎችም አገሮች አሉ። እያደረጉ ያለው ጥረት ከፍተኛ ነው። አሁን ግን፤ የአማራውን ሕልውና አስመልክቶ፤ የሁላችንን በር ያንኳካኡአ በመሆኑ፤ በአንድነት መሰባሰቡ አጣዳፊ ግዴታ ነው። እናም በነሱ መካከል አነሳሽነቱ ይወሰድና፤ ተሰብስበው ያሰባስቡን። ካልሆነ ግን፤ እኔን ለማግኘት ለፈለገ፡ eske.meche@yahoo.com