>

"ፋኖ ን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ናችሁ " በሚል ከሠራዊት አባልነት የተመለሱ 32 ወታደሮች ታሰሩ!(ባልደራስ)

ዜና ባልደራስ

“ፋኖ ን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ናችሁ ” በሚል ከሠራዊት አባልነት የተመለሱ 32 ወታደሮች ታሰሩ!

*…  በመርዓዊ ከታሰሩት መካከል አምስቱ ለመከላከያ ተሰጥተዋል!

*…. በዳንግላ የሚኖሩ ወታደሮችን ለማሰር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው የሚል ስጋት ውጥረት እየፈጠረ ነው!

በምዕራብ ጎጃም ዞን፤ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፤ ከባሕር ዳር ከተማ በአጭር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው #መርዓዊ ከተማ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከአማራ ልዩ ሃይል አባልነት በፈቃዳቸው የተመለሱ 18 ወታደሮች ታስረዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም፤ ደቡብ አቸፈር ወረዳ፤ #ዱርቤቴ ከተማ ውስጥ 14 ተመላሽ ወታደሮች በአብችክሊ ዙሪያ ፖሊስ  ጣቢያ ታስረዋል።

ዜጎች የፈለጉት ሰራዊት አባል የመሆን መብት ቢኖራቸውም፤ በሁለቱም ተቀራራቢ ከተሞች  ወታደሮቹ የታሰሩት “የአማራ ሕዝባዊ ኃይልን (ፋኖ) ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ናችሁ” በሚል ምክንያት ነው እየተባለ ነው።

በመርዓዊ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከታሰሩት 18  ወታደሮች መካከል አምስቱ ቀደም ሲል የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን በርካታ ግዳጆችን በብቃት የተወጡ ናቸው። አምስቱንም ፖሊስ ጣቢያው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አሳልፎ የሰጣቸው ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ አልታወቀም።

ከዚህ ቀደም ብሎ “ትታሰራላችሁ ወይም እርምጃ ይወሰድባችኋል” የሚል ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸው እንደነበርም ለታዳኞች ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች ተናግረዋል።

ለእስር እየተፈለጉ ከሚገኙት መካከል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ በሚያዩት እንቅስቃሴ በመከፋት፤ ከሰራዊቱ በፈቃዳቸው ከወጡ በኋላ የአማራ ልዩ ሃይልን ለመቀላቀል ጠይቀው የተከለከሉ ይገኙበታል።

# በዳንግላ የሚኖሩ ወታደሮችን ለማሰር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው የሚል ስጋት ውጥረት እየፈጠረ ነው!

/

ከአማራ ልዩ ሃይል፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከመደበኛ ፖሊስ ሰራዊት አባልነት ተመልሰው በአማራ መስተዳድር፤ አዊ ዞን፤  በዳንግላ ከተማና አቅራቢያው የሚኖሩ የሰራዊት ወታደሮችን ለማሰር አገዛዙ እየተንቀሳቀሰ ነውየሚል ስጋት በከተማዋ ውጥረት ፈጥሮል።

አገዛዙ ወታደሮችን ለማሰር የፈለገው፣  የአማራ ሕዝባዊ ሃይልን (ፋኖን) ይቀላቀላሉ’ ከሚል ስጋት ሳይሆን እንዳልቀረም ምንጮች ፣ጠቁመዋል። በከተማዋ ፋኖዎችን ትጥቅ የማስፈታት አዝማሚያ እየታየ መሆኑንም ገልፀዋል።

ትናንት ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማዋ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት በኩል ወጣ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ በሕጋዊነት የተመዘገበም ቢሆን ጠመንጃ ይዞ መንቀሳቀስን ከልክሏል። “ከተፈቀደለት የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ውጭ የተመዘገበም ሆነ ያልተመዘገበ የጦር መሳሪያ፤ የወገብም ሆነ የትክሻ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው። ድምፅ አልባ መሳሪያዎችን፤ ስለታማ የሆኑ እንደ ጩቤ፣ገጀራ፣አንካሴ፣ ጦርና ፌሮ ብረት ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው” በማለትም አውጇል።

አዋጁ “በሕግ የሚፈለጉትን ወይም ተጠርጣሪዎችን ሽፋን የሰጠ፣ የደበቀ፣ መረጃ ሰጥቶ ያስመለጠ ይጠይቃል” በማለት ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ከሰራዊት አባልነት የተመለሱ ወታደሮችን ለማሰር እያደነ እንደሆነ የወጣውን መረጃ እውነትነት ለማረጋገጥም አንዱ መንገድ ሆኗል። በመንግሥት ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ማድረግን ከልክሏል። በምሽት የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖርም ገድቧል። ይህንን ተከትሎ ትናንት እና ዛሬ አመሻሽ በዳንግላ መቀዛቀዝ ተስተውሏል።  ዳንግላ በ2008 ዓ.ም. ወያኔን ለውድቀት ያበቃው ሕዝባዊ አመፅ ቀድሞ ከተቀጣጠለባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን፤ ደቡብ አቸፈር ወረዳ፤ ዱርቤቴ ከተማ ውስጥ ከትናንት ጀምሮ ቁጥራቸው በርከት ያለ የመንግሥት ታጣቂዎች በመንቀሳበስ በሕዝቡ ዘንድ ፍርሀት ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑን ኗሪዎች ተናግረዋል።

በአጭር ኪሎ ሜትር የሚራራቁት ዳንግላ እና ዱርቤቴ ከተሞችና ዙሪያዎቻቸው ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ፣ ቢትወደድ አያሌው መኮንን እና ፊታውራሪ አውደው ሐበሻን ጨምሮ  የጣሊያን ወራሪ ሃይልን ድባቅ የመቱ በርካታ አርበኞች የፈለቁባቸው አካባቢዎች ናቸው። እንደ ኗሪዎች ገለፃ አገዛዙ ሰሞኑን እያሳየ ያለው ፋኖን ትጥቅ የማስፈታት አዝማሚያ ልጆች የአባቶቻቸውን የአርበኝነት ፈለግ እንዳይከተሉ የሚያደርግ ነው።

Filed in: Amharic