>

*በወታደራዊ ኃይል  ህግን ማስከበርም ሆነ የህዝብ ሥልጣንን መቆጣጠር አይቻልም...!!! (ኅብር ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ)

*በወታደራዊ ኃይል  ህግን ማስከበርም ሆነ የህዝብ ሥልጣንን መቆጣጠር አይቻልም…!!!

ኅብር ኢትዮጵያ  ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ


ኅ.ኢ.ዲ.ፓ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የተሠጠ መግለጫ  ግንቦት 15/2014 ዓ.ም  አዲስ አበባ

በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን እንዲሁም ዛሬ የህወሀት የፖለቲካ አስተሳሰብ በወረሰው በብልጽግና መንግስት ያሳለፍናቸውንና አሁንም እያሳለፍን ያለው ብንመለከት የጭቆናው ዘዴና ስልት ይለያይ እንጂ በሁሉም ስርዓቶች ኢትዮጵያውያን ከጭቆና ተላቀን የሀገራችንና የስልጣን ባለቤት ሁነን ወደ ሁሉን አቀፍ  እድገት አልተራመድንም፡፡ምክንያቱን ምንድነው ብለን ከጠየቅን እስካሁን ባለው ታሪካችን ህዝብ በሀቀኛ መንገድ የስልጣን ባለቤት መሆን ስላልቻለና ፖለቲካችንም ከጥላቻ፣ ከመጠላለፍና ከመጠፋፋት አዙሪት ስላልወጣ እና ፖለቲከኞቻችንም መውጣት ስለማይሹ መሆኑን መታዘብ ተችሏል ፡፡በተለይም ባሳለፍነው አራት ዓመታት ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በባሰ መልኩ በከባድ ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡

ይህ ሊሆን የቻለበት ዋናው ምክንያት በእኛ ግምገማና የሁነቶች መገለጫ የብልጽግና መንግስት ለስልጣን ያበቃው ህዝባዊ ትግል  መሆኑን ዘንግቶ ወደ የስልጣን ጥሙን ማርካት ላይ ብቻ የተመሠረተ  ክሹፍ ምግባር በመሸጋገሩ እና እንደቀደሙት ገዢዎች አገሪቷ የሚያስፈልጋትን እውነተኛ መፍትሄ ሳይሆን ፓርቲው ለመጭው አምሳና ስልሳ ዓመታት ያለምንም ተቀናቃኝ ስልጣን ላይ እንዴት ልቆይ እችላለሁ? በሚል ረዥም ርቀት በማይወስደው አጉል ቅዠት ውስጥ መግባቱ ላለንበት ሁለንተናዊ ቀውስ አድርሶናል፡፡

ገዢው ፓርቲ /መንግስት ህግ በማስከበር ሽፋን ምን ፍላጎትና ግብ እንዳለውና መጨረሻው ምን እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ክብር ፋንታ ህዝብን በማደናገር በተለመደው የማንአለብኝነትና እብሪት  መንገድ  ሲጓዝ እየተመለከትን እንገኛለን ፡፡ ትናንት ብልጽግና ከባዶ ተስፋና ስሜታዊነት ወጥቶ በእውነትና ዕውቀት እንደሚመራን ፣ በዚህ መሰረትም  የተገቡልን ቃላት ‹‹ ሳንመረምር አናስርም፣ በእኛ ዘመን አሳዳጅና ተሳዳጅ አይኖርም፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ አያስወነጅልም፣ ›› አለመፈጸም ሳይሆን በተቃራኒው ‹‹እኔን ያየህ ተቀጣ›› ከሚል አልፎ ትናንት ከህገመንግስትና የመንግስት መዋቅር፣ ከመርህና ህግ አግባብ ውጪ  የተፈጠሩት ‹‹ክልላዊ ልዩ ኃይል›› እና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ዛሬ  በተለይ ኢመደበኛ አደረጃጀቱ ሲወደስና ሲሸለም ባየን ማግስት በወንጀለኝነት ሲፈረጅ የምንሰማበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ፡፡

የመብት ተሟጋች- የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ፖለቲከኞች ከህግ አግባብ ውጪ ሲታደኑ፣ሲታፈኑና ሲገደሉ ይህም እየከፋ፣ እየሰፋና እየተስፋፋ ሲሄድ እየተመለከትን ነው ፡፡ ነገር ግን ካለፉ ጊዜያት በተለየ ህዝብ ምላሽ እየሰጠ በተለይ የኢመደበኛ አደረጃጀት አስተባባሪዎችንና ልጆቹን ‹‹አናስነካም›› በሚል በአማራ ክልል ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከስቶ በህዝብና በመንግስት መካከል ግልጽ ግጭት ውስጥ ሲገባ እየተመለከትን ነው ፡፡

ሠላምና መረጋጋት መስፈን፣ የዜጎች ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ተቃራኒ በመሆኑ በተለይ ገዢው ፓርቲ-መንግስት ካለበት ሃላፊነት አንጻር እነዚህ እንዲሟሉ ከማድረግ በተቃራኒ በህግ ማስከበር ሥም የሚያደርገውን እና ከዚህም ቀደም ሲተገብር የመጣውን የኃይልና አፈና ተግባራት አጥብቀን እናወግዛለን፡፡

እነዚህ የኃይልና አፈና እርምጃዎች ሠላምና መረጋገቱን ቁልቁል እየወረወሩት፣ህገ ወጥነትንና የመንግስት ባለሥልጣናትን ማንአለብኝነት እያፈረጠሙና እያስፋፉ  ወደ ከፋ  የፖለቲካ ቅርቃር፣ኢኮኖሚ ውድመትና ማኅበራዊ ትርምስና ቀውስ ከመዳረግ ውጪ የሚመጣ አዎንታዊ ውጤትና መፍትሄ የለም፡፡

ይልቁንም በተያያዘው አካሄድ  ህዝቡ የቱንም የትግል አማራጭ ለመከተል የሚያበረታታ በመሆኑ ገዢው ፓርቲ-መንግስት  ከያዘው የጥፋት መንገድ እንዲመለስና የመጨረሻውን ሰላማዊ ዕድሉን እንዲጠቀም አጥብቀን እንመክራለን፡፡

ፓርቲያችን ኅብር ኢትዮጵያም  የአገራችን ፖለቲካ  በአንክሮ ተከታትሎ የትኛውም አይነት ጥያቄአቸውን በሃይል ለማስመለስ የጦር መሣሪያ ትግልን አማራጭ ያደረጉ እና እያደረጉ የሚገኙ አሰላለፎች እና በነዚህ ሁኔታዎች ላይ የህወሀት/ኢሀአዴግ ቅጥያ የሆነውን ብልጽግና መንግስት ገና ከጅምሩ ያሳይ የነበረውን ሃላፊነት የጎደለው ተግባርና ሃዲዱን የሳተ የፖለቲካ አካሄድ በመረዳት ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ሀገርን እስከማፍረስ ሊያደረሱ እንደሚችሉ ጠቁመን  አበው «ሳይቃጠል በቅጠል» እንዲሉ  ሁሉን አቃፊና አሳታፊ ብሄራዊ መግባባትና ሀገራዊ  ዕርቅን ማዕከል ያደረገ የሸግግር  ሂደትን እንዲጀመር ጠይቀናል፤ አሁንም በመጠየቅ ላይ እንገኛለን፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጰያ ህዝብ- የፖለቲካ ፓርቲዎች፡የሃይማኖት ተቋማት፡ የሲቪክ ማህበራት፣የአገር ሽማግሌዎች፡ ልህቃንና ማህበራዊ አንቂዎች ከጊዜያዊና አጭር ምልከታ  በመላቀቅ በሀቅ ጎዳና በመጓዝ አገራችን ከገጠማት እጅግ አሳሳቢ ፈታኝ  ሁኔታ ለማውጣትና ለፈተናዎቿ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አገርና ህዝብ ማዕከል ባደረገ የኃላፊነት አስተሳሰብ የየበኩላችሁን  በጎ አስተዋዕኦ ታበረክቱ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ኅብር ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

     ግንቦት 15 / 2014 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ

Filed in: Amharic