>

ከዛፉ`` ቀድማ የበሰለች ፍሬ  ...!!! (ይሁኔ አፈወርቅ)

ከዛፉ“ ቀድማ የበሰለች ፍሬ  …!!!

ይሁኔ አፈወርቅ


“ለውጥ” የተባለውን “ተረኛ አፋኝ“ መንግስት በእልልታ ያነገስንበት የጉድ ዘመን አምጥቶ ከደፋብን ተገለባባጭ ፖተሊከኞች ምስያ የላትም፡፡ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ማንነት ቀለምና ምክንያታዊ ተጠይቅ ይዛ ወደ ህዝብ ጆሮ መጠጋት የጀመረችው ወያኔ ጥርሷ እንደተሳለ ሐቅሟ ሳይከዳት ጀምሮ ነው፡፡ ራሷን በአምሓርነት ለመግለጥ ትሽኮረመም ነበርና እኔ ብዙም አልቀርባትም ነበር ፡፡

‹‹ስለ ስልጣን›› የሚለውን የመጀመሪያ መጽሐፏን ያነበብኩላት 2007 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ ከዚህ መጽሐፏ ገጾች ውስጥ ተካተው ካነብኩላት ሐሳቦች መካከል ‹‹ፋኖው መለስ›› የሚለው ርዕስን መቼም አልረሳውም፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ መስኪን በእስክንድር ነጋ መጽሐፍ ምረቃ ጉዳይ አግኝቼ ሳወራት… ስለዕርሷ የቀደመ መጽሐፏ ሀሳብ ጉዳይ ሳነሳላት ብዙ እርካታ እንደሌላት በፊቷ ገጽ ተረድቻለሁ፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ በእኔ አተያይ ድንቅ ነው፡፡ ላላነበቡትም ምክሬ ፈልጋችሁ አንብቡት ነው፡፡ ታላቋን የዘመን ክስተት የሆነች ወጣት ልሂቅ የቀደመ ብስለት ከማወቅ መጀመሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡  ዛሬ ለውጥ ከተባለው የተረኞች አገዛዝ መከሰት በኋላ በ2013 ዓ.ም 2ኛው ‹‹የዘውግ ፖለቲካ ስረ መሰረቶች›› በሚለው መጽሐፏ ደግሞ ልጅቷ… ድንቅ፣ ደፋር፣ ከሐቅ የተዋደደች፣ በእውቀት የተመላች ተናጋሪ ብቻ ሳትሆን… ‹‹ብዕርሽ አይንጠፍ›› የምታስብል ትንታግ ጦማሪነቷን አስመስክራለች፡፡ ቀስ በቀስ ከጋዜጣ አምደኝነት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ሳይበር ትርምሱ ጎራ ስትቀላቀል ደግሞ ‹‹ከዓይን ያውጣሽ›› የምታስብል ብሩህ የዘመን ክስተት ኮከብ፣ አክቲቪስት፣ ፖለቲከኛነትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትን አጣምራ የመንጋውን ትርምስ አደብ እንዲይዝ በምክንያታዊ ሂስ ትነርተው ጀመረች፡፡ ልጅቷ የዋዛ አይደለችም፡፡ መንጋው… ለውጥ በሚለው የመደመር ባቡር ተሳፍሮ መዳረሻውን ሳያውቅ ቁልቁል ሲተምም… የናቷ ልጅ ጀግኒት ግን…፣ ፌርማታና ወደቡን ባልነገረኝ ባቡር ይሁን ጀልባ አልገባም አለች፡፡ የመደመርን ቁማር ቀድማ ተረድታ በቁማርተኞች የደም  ማእድ እጄን “አላረክስም!” አለች፡፡ ተደማሪና ደማሪዎችን በሩቁ እያዬች…‹‹አይ የመንጋ ነገር›› እያለች ‹‹ለውጥ ሳይሆን ተረኝነት፣ የአንባገነን አገዛዝ እያዋለድን ነው፣ የአንድ ፈላጭ ቆራጭ “ሁሉን አውቅላችኋለሁ” ንጉስ ጫንቃችንን ሊያጎብጥ ነውና በምክንያት እንደግፍ›› ስትል ወተወተች፡፡ እንደርሷ ቀድመው ከነቁት ምስያወቿ ጋር ሆና በተገኘው መድረክ ሁሉ የተረኛውን አንባገነን መንግስት በሐሳብ መሞገቷን ቀጠለች፡፡ ኃይል እንጅ… ሀሳብ የነጠፈበት የኦሮሙማ መንግስትም ጥርሱን መንከስ ጀመረ፡፡ ‹‹ይች ጥሬ ካደረች›› አለ ባለ መንበሩ፡፡

ፍርሓት አንዳች ጎብኝቷት የማታውቀው ጀግኒት በመንግስት ቁማር እያደረች መብከንከኗ ቀጠለ፡፡ በአምሓራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ያለ ከልካይ በ4 ኪሎው መንግስት ድጋፍ መፈጸሙ መረጃው ከተጎጅዎች መሰማት ሲጀምር ደግሞ… አርበኛዋ ትዕግስቷ ተሟጠጠ፡፡ ወኪል አልባ ሆኖ… የዘር ፍጅት ለሚፈጸምበት አምሓራ ድምጽ መሆንን… የየለት ስራዋ አደረገች፡፡ በዚህ ጊዜ… ኦሮሙማ አይኑ መቅላት ጀመረ፡፡ ጉዱን ማፍረጥረጧን በአይኑ እያዬ ባላዬ ማለፍ አልቻለም፡፡ በልዩ ልዩ መንገድ ማስጠንቀቂያ ያደርሳት ጀመር፡፡ በምታስተምርበት ሐዋሳ ዩንቨርሲቲ ዙርያ ደስታዋን ማደብዘዝ፣ ምቾቷን መንጠቅ ጀመሩ፡፡ እርሷ ግን፣ ወይ ፍንክች! ጭራሽ የአምሓራ ህዝብ በደል  ‹‹የከተማው ፋኖ›› አደረጋት፡፡ ለዚህ ምስጉን ህዝብ እርጉዝ ሆና እስከ እመጫት ጊዜዋ ያለ እረፍት አደባባይ ለመውጣት ድካም አጣች፡፡ የአምሓራ ህዝብ የትግል አቅጣጫን ያስመለከተውን ሰነድ አርቅቃ ስትመጣ ግን… ቤተ መንግስቱ ተናወጠ፡፡ በተቃራኒው የአምሓራ ህዝብ የመብት ታጋይ ቡድኖች ክስተት የኦሪዮ ኮከብ ሆነች፡፡ ‹‹ሴቷ ፐ/ር አስራት ወልደዬስ ከወዴት መጣችልን⁈›› እና ከወዴት መጣችብን ሐሳቦች አየሩን ያስጨንቁት ጀመር፡፡ ነገር ግን፣ መንበረ ስልጣኑን የጨበጠው ተረኞው የኦሮሙማ ኃይል ነውና… ሊነክሳት ማድባቱን ቀጥሎ ነበር፡፡ እነሆ… አውሬዉ ኦሮሙማ… በጭቆና ቀንበር ሊያማቅቀው ለተነሳው ህዝብ የሐሳብ ፋኖ ሆና ልትከላከልለት የተነሳችውን ታላቅና ሩቅ አሳቢ እምጫት ሴት… ከጨቅላ የ7 ወር ህጻን ልጇ ነጥሎ ከባህርዳር አዲስ አበባ ኤርፖርት እንደደረሰች አፍኖ ሰውሯት ሰንብቷል፡፡

አንዳች በደል የሌለባትን ንጹህ የመብት ታጋይ ጀግናዋ ብላቴና… ተረኛው አንባገነን የኦሮሙማ መንግስት ትላንት ፍ/ቤት አቆሞ ምን ብሎ እንደከሰሳት ስንሰማ ደግሞ… በዚህ ሐገር የፍትህ ስርዓት ተስፋ እንድንቆርጥና ሌላ መላ እንድንመታ ግድ መሆኑን ፍንጭ አይተንበታል፡፡ ‹‹እርሷ ፋኖ ናት›› ጭቆናን “እንቢኝ” ብላለች፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ ሊሆናት ይገባል፡፡ በተለይ የአምሓራ ህዝብ… ልጅህን ወዴት ነች⁈ ብለህ ጠይቅ!!! የነቃውን ልጅህን የሚያሳድደው አውሬ… አንተን ስለናቀ ነው፡፡ እንደ ህዝብ አንበርክኮና አዋርዶ ለመግዛት… የነቁ ተቆርቋሪ ልጆችህን እንዳበደ ውሻ እየነከሰ ያለው መንግስትና ተላላኪ ባንዳው  በህዝብ “ተው!“ ሊባል ይገባል፡፡ ‹‹ሰበርናቸው›› ያለህ ተረኛ ቡድን በግፍ ስራው ቀጥሏል፡፡ አለመሰበርክን የምታሳዬው ጸጋህ በሆነው ድል አድራጊነት… በጨቋኝህ ላይ ስትነሳ ነው፡፡

Filed in: Amharic