ክቡርነትዎ አልወከልኩዎትምና ወክለውኝ እንዳይደራደሩ…!!!
አሳዬ ደርቤ
ጉዳዩ፡- እኔን ወክለው እንዳይደራደሩ ስለማሳወቅ
ክቡር ሚኒስትር፡- የትኛውም አገራዊ ትርምስና አለመረጋጋት የእርስዎን ሰላም ማናጋት እንደማይቻለው በማመን ‹‹ሰላም ነዎት ወይ›› ብዬ ሳልጠይቅ ወደ ዋናው ሐሳቤ ስገባ ‹‹ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል›› የሚለው አባባል እውነት የመሰላቸው ባለሥልጣናት በተናገሩ ማግስት ሲባረሩ ታይተዋል፡፡ እርስዎ ግን ‹‹ባለመናገር ምክትልነት ይጸናል›› በሚል ፍልስፍና የሚመሩ በመሆንዎ ከጎንዎ የነበሩ ጓዶችዎ ከጸረ አማራ ንቅናቄው ጋር በሚጋጭ ተግባራቸውና በአፈንጋጭ ንግግራቸው ሲቀበሩ፣ ሲታሰሩና ሲባረሩ ምክትልነትዎን እንዳስከበሩ እስካሁን ድረስ ዘልቀዋል፡፡
በእነዚያ የዝምታና የመኝታ ዓመታት ታዲያ የአማራ ሕዝብ በቀድሞው ሥርዓት ማንነቱን፣ መሬቱን፣ ክብሩን፣ ዜግነቱን ሲነጠቅ ቢኖርም እርስዎ ግን የተነጠቀውን ሊያስመልሱለት ቀርቶ ‹‹የጎንደርን ምድር ለሱዳን ፈርሞ ሰጥቷል›› እየተባለ ሲነዛብዎት የነበረውን ክስ እንኳን ማስተባበል የቻሉት ህውሓት ከተባረረ በኋላ ነበር፡፡
ያንንም የሥም ማጥፋት ዘመቻ ካስተባበሉ በኋላ በፈርዖን አንደበት ‹‹ሥልጣን ልልቀቅ›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ብሶትዎን የተጋራው የአማራ ኤሊት ‹‹እኛ ሳንፈቅድ ንቅንቅ ማለት አይቻልም›› በሚል ጫጫታ የእርስዎ ምክትልነትና የአማራ ሕዝብ ባርነት ይቀጥል ዘንድ ይሁንታውን ቸረ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶም የፈረደበት አማራ ‹‹ነፍጠኛ ነህ›› እያለ ከሚያባርር ጠላት እና ‹‹ከተማ ታቆሽሻለህ›› ከሚል መንግሥት እጅ ወድቆ አገሩን የዘረፈውን አገር መፈለግ ጀመረ፡፡
ክልላቸውን በወረረ ጠላት የተፈናቀሉ እናቶችና ሕጻናትም ሸኖ ላይ ከሚያግት መንግሥት እጅ ወድቀው ‹‹የኢትዮጵያ ዜጎች ሆነን ሳለ የሦሪያ ስደተኞች ከሚኖሩበት የአዲስ አበባ ከተማ መግባት እንዴት ተከለከልን›› እያሉ ሲያለቅሱ ነበረ፡፡
እንዳጠቃላይም በብአዴን እና በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የአማራ ሕዝብ ከጸሐይ በታች ያሉ ግፎችን ሁሉ እያስተናገደ ‹‹ያልፋል›› በሚለው ቀን ውስጥ እየተጨፈጨፈ ሲያልፍ ነበር፡፡
በተለይ ደግሞ በብልጽግና ዘመን ያጋጠመው ጥቃት ሕይወቱን ከመንጠቅ ባለፈ ሥነ ልቦናውን የማድቀቅ ግብ ያለው በመሆኑ እልቂትና ውርደት ይዘው የሚመጡትን መጪ ጊዜያት ሊጠብቅ ቀርቶ አባቶቹ ከእራሳቸው ባለፈ አገራቸውን አስከብረው ያሳለፉትን የትናንት ጊዜያት እንዳይናፍቅ በሚያደርጉ ዘመቻዎች አሳሩን ሲበላ ነበር፡፡
ክቡር ሚኒስትር፡- በሥልጣን ሽግግሩ ማግስት ብአዴንም ሆነ አብን በባለፈው ሥርዓት የአማራን ሕዝብ ለሰቆቃ የዳረጉና መልስ የሚፈለጉ ጥያቄዎችን ዘርዝረው ማስቀመጣቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ችግሮቹ ሲረቀቁና ሲጸድቁ ፊርማውን ባኖረ ድርጅት የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ‹‹ለሰባቱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች መፍትሔ አመጣለሁ›› ብሎ ቃል የገባው የእርስዎ ድርጅት ሰባ ሰባት ችግሮች አምጥቶ ሲያስታቅፈን ከርሟል፡፡
ከእነዚያም ሰባት ጥያቄዎች አንዱ የወልቃይትና የራያን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን በእልፍ አእላፍ ወገኖች ነፍስ መልስ አግኝቶ የነበረውን የራያን ሕዝብ ደፍጥጦ ያለምንም ትግል ለቀድሞ አፋኙ ያስረከበው ድርጅት በወልቃይት ማንነት ላይም ለመደራደር መዘጋጀቱ ግልጽ ሆኗል፡፡
ይሄውም የድርድር ኮሚቴ በእርስዎ የሚመራ መሆኑ ቢነገርም በበኩሌ ግን የድርጅትዎም ሆነ የእርስዎ ያለፉ ዘመናት ትግሎች በአማራ ሕዝብ ጉዳት ላይ የአገር ቀጣይነትን ሲያረጋግጡ፣ በወገን በደል ላይ uየሌሎችን ድል ሲያስጨብጡ፣ የአማራን ሕዝብ ጸጋ ነጥቀው የሕልውና አደጋ ሲያመጡ…. የኖሩ በመሆናቸው አሁንም ቢሆን በድርድር ለሌሎች የሚሰጡት ካልሆነ በስተቀር የሚያመጡት ቅንጣት ታክል በጎ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
ስለሆነም አገርዎንም ሆነ ክልልዎን ወክለው የሚያደርጉት ድርድር እንደ አንድ አማራ እኔን የማይወክል መሆኑን ስገልጽ ‹‹ሕገ-መንግሥቱ ላይ ካልሆነ በቀር ለሱዳን የተሸጠው መሬት ላይ አልፈረምኩም›› ያሉትን ፊርማ ወልቃይት ላይ እንዳያስቡት በመምከር ነው፡፡