>

እጮሃለሁ!  (ሜሮን ጌትነት)

እጮሃለሁ!

ሜሮን ጌትነት


አባቴ ተሰቅሎ፣

ወንድሜ ተቃጥሎ።

እህቴ ታግታ፣

እናቴ ተቀልታ።

አያቴ ተሰ’ዶ 

ህፃን ልጄ ታርዶ…  አሞኛል! 

                ወገን ሞቶብኛል! 

                ሰው ተገ’ሎብኛል

በማያውቀው ጉዳይ ባልገባው ጨዋታ፣

በሌለበት ግንባር ባልዋለበት ሜዳ ቀድሞ እየተመታ፣

ተጨምቆ ተጨምቆ ጠብ ላይልለት የድላቸው ፋይዳ፣

መከራ የሚገፋው እየወደቀበት የማያውቀው እዳ…።

ሞት እያንዣበበ… ደክሞት ካረፈበት ከደሳሳ ቤቱ፣

ለማይሞላ ኑሮው ለማይነጋው ሌቱ።

    ዛች ጥርስ እያፋጨ፣

    ጥይት እያፏጨ።

     ካራ እየተሳለ፣

     ቀስት እየተሾለ…

                       አለ!

    ከተፈጥሮ ታግላ፣

    ጎታች ባህል ጥላ፣

    ልትማር የተጋች ቀን ይወጣል ብላ።

    መድረሻ ተነፍጋ መንገድ ላይ የቀረች

                                እህቴ…. የታለች?

አሞኛል! 

ሰው ተገድሎብኛል!

ሰው ተሳዶብኛል! ተፈናቅሎብኛል! ከኖርበት ቀዬ፣ 

የአቅሜን እጮሃለሁ …

              “የሰላም፣ ፍትህ፣ የህግ ያለህ!” … ብዬ።

“የኔ አቅም ለቅሶ ነው ድምፅ ልሁናቸው ልጩህላቸው” ስል

ይመጣል ሳይፈራ አሳ’ቆ ሊያፍነኝ ቃላቱን የሚስል

“ምንድነሽ?” ይለኛል “ለእገሌ ለእንትና” ጉዳቴ ሳይገደው

“የሟች ወገኑ ነኝ!” ንፁህ ሆኖ ሳለ ለሞት ‘ሚማገደው።

“የት ነበርሽ?” ይለኛል

“ለምን ዛሬ?” ይለኛል… ይሳለቅብኛል ድምፄን እየለካ

ስጮህም ዝምም ስል ለ’ሱ ፖለቲካ

“መርጠሽ ነው” ይለኛል…

         መርጦ ገዳይ ካለ በየአደባባዩ፣

መርጬስ ባለቅስ ማን ይሆን ከልካዩ?

መርጬ አለቅሳለሁ ለተገፋው ህዝቤ ለሞተው ወገኔ

ቡድኑን አንተ አብጀው ንፁህ መሆኑ ነው የሚያገባኝ እኔ።

በፈለግኩት ጊዜ በፈለግኩት ቦታ

ስችል አለቅሳለሁ ሳልችል በዝምታ

ፈቃጅ አልፈልግም ለራሴ ስብራት ሀዘን አስተማሪ

አስታዋሽ አልሻም ላጣሁት ወገኔ የ’ጩሂለት’ ጥሪ

በፈለግኩት ጊዜ በፈለግኩት ቦታ

ስችል አለቅሳለሁ ሳልችል በዝምታ

“የማን ነሽ? ምንድነሽ? ከየት ነሽ?” ይለኛል ከየትስ ብመጣ?

ገድዬ አልፎከርኩኝ ሞቶብኝ ነው እንጂ አቅሌን የማጣ

ገዳይ ንፁህ ፈጅቶ በኮራበት ሀገር

ለተገፋ ማልቀስ ለምነው ‘ሚያስወግር?

ገድሎም አይበቃውም “እሰይ” ብሎ አይረካ

እንባዬን አድርቆ ሀዘኔን መቀማት አዲስ ፖለቲካ

እጮህለታለሁ…

ንፁሁ ሲጎዳ ባልመረጠው ደሙ ባልመረጠው መልኩ

ክርስቲያንም ሙስሊም ጥፋት ከሆነበት በምርጫ ማምለኩ

ለአማራ እጮሃለሁ በጅምላ ለሚያልቀው ለሚፈሰው ደሙ

ለትግራይ እጮሃለሁ ጦርነት ሲጎሰም በልቶት ሰቀቀኑ፣

ስደት ለመረጠው ከገዛ ሀገሩ፣ ከገዛ ወገኑ።

ለተደፈረችው፣ ለተሰበረችው እንግልት እህቴ፣

                                             ላዘነች እናቴ

ለኦሮሞ ወንድሜ፣ ለደቡብ አባቴ፣ ለሀረሪ፣ ሱማሌ፣

ቤኑሻንጉል፣ አፋር፣ ድሬደዋ ላለው ወይ አዲስ አበቤ።

                             ለተበዳይ ህዝቤ፣ ለሞተ ወገኔ…

እጮህለታለሁ!

ቡድኑን አንተ አብጀው ንፁህ መሆኑ ነው የሚያገባኝ እኔ።

ትናንት ጮኼያለሁ፣ እጮሃለሁ ዛሬ፣ እጮሃለሁ ነገ

ሁሉም ወገኔ ነው ድምፅ የተነፈገ።

እጮህለታለሁ! … እጮሃለሁ!

 

በአርቲስት ሜሮን ጌትነት

 

Filed in: Amharic