>

“የዘር ተኮር ጭፍጨፋው ምንጭ አማራን ካጠፋህ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀላል ነው ከሚል የተሳሳተ ትርክት የተቀዳ ነው”   (ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወንድሙ ኢብሳ)

“የዘር ተኮር ጭፍጨፋው ምንጭ አማራን ካጠፋህ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀላል ነው ከሚል የተሳሳተ ትርክት የተቀዳ ነው” 

 (ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወንድሙ ኢብሳ)

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ አፍሪካን እንደ አህጉር በርብረው ያሰሱ ምዕራባዊያን ኹሉ ድምዳሜያቸው አንድ እና ወጥ ነበር፡፡ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ቁጥጥር ሥር ማዋል ቀላል ነው ብለው የሚያስቡት አሳሾቹ ኢትዮጵያ ግን ከሌሎቹ ትለያለች ብለው ይደመድማሉ፡፡ ለቅኝ ግዛት ወረራው ምናልባትም ኃይል እንደ አማራጭ ኾኖ ከቀረበ ለኢትዮጵያ ብቻ መኾኑን ቀድመው ገምተዋል፡፡

የቅኝ ግዛት ወራሪዎቹ አፍሪካን በእጣ ሲሸናሸኑ ጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት እጣ ወጣላት፡፡ ጣሊያን ከወረራው ቀድማ በኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ካንዣበቡ የሌሎች ሀገር ቅኝ ገዥዎች ጋር መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡን እና የሕዝቡን ሥነ ልቦና መረመረች፡፡ ጦርነት አይቀሬ መኾኑን ብታውቅም ጦርነቱን በቀላሉ በድል ለመወጣት ኢትዮጵያዊያንን በዘር እና በሃይማኖት መከፋፈል አዋጭ መኾኑን አጤነች፡፡

ለጣሊያን ሴራ ራሳቸውን ያስገዙ ሆዳሞች እና ባንዳዎች የልዩነቱን ቅርቃር ከጣሊያኖች ልቀው በመተወን መንገዱን ኹሉ ቀና አደረጉላቸው፡፡ ዳሩ ሀገር ወዳዶቹ ኢትዮጵያዊያን ልዩነት አብዝቶ ቢቀነቀን፣ ጥላቻ ያለልክ ቢሰበክ እና አንድነት ጠል የሐሰት ትርክት ቢነዛ በሀገር ጉዳይ አንድ ነን አሉ፡፡ በዓድዋ ተራሮች ነጭ በጥቁር እንደሚሸነፍ ተረጋገጠ፡፡ ሽንፈቱ የጣሊያን ብቻ አልነበረም ይልቁንም መላው ምዕራባዊ ቅኝ ገዥዎች ኹሉ ቅስማቸው ተሰበረ፡፡

ከ1888 ዓ.ም የዓድዋው ድል ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ በምዕራባዊያን ቅኝ ገዥዎች የበቀል ጥርስ ውስጥ ገባች፡፡ እናም ኢትዮጵያን ለመበተን አማራን ማዳከም እንደ አንድ ስልት ተደርጎ ተቀየሰ፡፡  እንዳለመታደል ኾኖ ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ በ1983 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ከአንድነት ኃይሎች እጅ ወጥታ በጽንፈኛ ብሔርተኞች እና በአክራሪ መንደርተኞች መዳፍ ውስጥ ወደቀች፡፡

ገንጣይ አስገንጣዮቹ ገና የሥልጣን ወንበራቸው ሳይረጋ አማራን ከአርሲ እስከ ጉራ ፈርዳ በጅምላ ጨፍጭፎ በጅምላ መቅበር ተጀመረ፡፡ ጽንፈኞቹ የባንክ እና ታንክ ምንጮቻቸው የሰጧቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ከሽግግር መንግሥት እስኪወጡ እንኳን መታገስ አልቻሉም ነበር፡፡ ከዚያ ጀምሮ አማራ ጠል ትርክቱ እና የፖለቲካ ርዕዮቱ ኹሉ ማዕከል መኾን ጀመረ፡፡

በወለጋ እያየነው ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ግድያ ጭፍጨፋ ነው ያሉን ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተማጋቹ ወንድሙ ኢብሳ ናቸው፡፡ ጭፍጨፋ ማለት የጦር መሳሪያ ያልያዙ እናቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋዊያን እና ሴቶችን የጥቃቱ ዒላማ ማድረግ ነው ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ብዙ ጊዜ ጭፍጨፋ የሚፈጸመው ደግሞ በአሸባሪዎች ነው ይላሉ፡፡ በዚህ የተቀናጀ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የኾኑት የትናንት ቀኝ ገዥዎች እና የዛሬ እጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች ተሳትፎ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እምነት አሁን እየተስተዋለ ያለው ሀገራዊ ችግር ምክንያቶቹ ቀላል እና ቅርብ አይደሉም፡፡ እባብ የሚሞተው ጭንቅላቱን ሲመታ ነውና ሽብርተኞችን ከተራ ማሳደድ ወጥቶ ጭንቅላታቸውን መምታት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ አማራን እንደ ሕዝብ ለይቶ ማጥቃት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ውርስ ነው የሚሉት አቶ ወንድሙ “የዘር ተኮር ጭፍጨፋው ምንጭ አማራን ካጠፋህ ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀላል ነው ከሚል የተሳሳተ ትርክት የተቀዳ ነው” ብለዋል፡፡ ሽብርተኞች የሚፈጽሙትን ከሰብዓዊነት በታች የወረደ ድርጊት ለማስቆምም ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ጀምሮ ከምዕራባዊያን ፍትሕን እና ሰላምን አግኝታ አታወቅም ያሉት ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እና በጋራ መቆምን ምርጫ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡

ንጹሐን በግፈኞች ሲጠቁ ለመጮኽ የግድ የአንድ ብሔር ተወላጅ መኾንን አይጠይቅምና ይህን መሰል አሳፋሪ እና አንገት የሚያስደፋ ጭፍጨፋ በጋራ ማውገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ መሰል ድርጊቶችን ለማስቆም መንግሥት ሕዝብን መስማት እና ሕዝብም ከመንግሥት ጎን በመኾን በጋራ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ዝቅተኛ ግዴታ ነው፤ የጥፋት ተባባሪ የኾኑ አካላትን ከላይ እስከ ታች አጣርቶ ለሕግ ማቅረብ እና ተጠያቂነትን ማስፈን ከመንግሥት የሚጠበቅ ኅላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው ከአሚኮ

Filed in: Amharic