>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4310

ተመስገን ደሳለኝ ዶሴ፦ ከክርክር በፊት ፍርድ (ጌጥዬ ያለው)

የተመስገን ደሳለኝ ዶሴ፦ ከክርክር በፊት ፍርድ

ጌጥዬ ያለው


በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዶሴ ላይ ከክርክር አስቀድሞ ሁለት ጊዜ ሕገ ወጥ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቷል። ያለው ዕድል የጥፋት ማቅለያ ማቅረብ ነው።  የመጀመሪያው ፍርድ የተሰጠው በወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና አምበል አብይ አሕመድ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ውስጥ ነው። ይህ ሰው በሕግ አውጭው ምክር ቤት ፊት ሕግ ተርጉመው “መከላከያን በብሔር፣ በሃማኖት ለይቶ ማቅረብ አይቻልም። ክልክል ነው። ወንጀል ነው። ያሳስራል” በማለት የተናገሩት በቀጥታ በተመስገን ላይ የተወሰነ የጥፋተኝነት ብይን ተብሎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም። ጥፋተኛ ብለውታል። የቀራቸው ለጥፋቱ ተመጣጣኝ ያሉትን ቅጣት መጣል ነው። ይህንም ቢሆን እስራት ብለዋል። እስሩ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ነው ያለገለፁት።

ሁለተኛው ፍርድ የተሰጠው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ውስጥ ካባ በደረቡ ዳኛ ነው። ዳኛው ከሦስቱ የችሎቱ ዳኞች መካከል አንዱ ናቸው። ፕሮቶኮላቸው ከሰብሳቢ ዳኛው በስተቀኝ ይመስለኛል። ተረኝነት የሕግ አተረጓጎም ሙያቸውን አስክዷቸዋል። ክሱ የተመስገንን የዋስትና መብት የማያስከለክል መሆኑን ሲረዱ በቀጠሮ ቀን ችሎቱን ትተው ጠፉ። ባልተሟላ ዳኛ ክርክር ቢደረግ እንኳን ብይን መስጠት ስለማይቻል መዝገቡ ሳይከፈት ለሌላ ቀጠሮ ተሸጋገረ። ተሜ ላይ ጥቂት የእስር ቀናት ጨመሩ ማለት ነው። በሌላ በኩል ለከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የይግባኝ ሰነድ ማዘጋጃ ተጨማሪ ጊዜም ደረጎቱት። እኒህ ዳኛ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ያለ ቅድመ ሁኔታ ከእስር ተፈተው የተቋረጠውን የእነ እስክንድር ነጋን ዶሴ ይዳኙ በነበረበት ጊዜ የክርክሩን ሂደት ሊቀይሩ የሚችሉ ብይኖች በሚሰጡባቸው ቀጠሮዎች ጠብቀው ከችሎት ይጠፉ ነበር። አንድ ጊዜ ጧት አከራክረው ከሰዓት ጠፉ። ሰብሳቢ ዳኛው ከግራ ዳኛዋ ጋር ተሰየሙና ቤተሰብ ታሞባቸው ከክፍለ ሀገር በመምጣቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄዳቸውን ነገሩን። ሆስፒታል ሄዱ በተባለበት ሰዓት ደብረ ዘይት ከካድሬዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው ታዩ። የተሜ ቀጠሮ ዕለትስ የት ሄደው ይሆን?

የሆነው ሆኖ ሌላኛው ቀጠሮም ደርሶ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ቤት ወደ ችሎት ተወሰደ። በዚህ ዕለት ሁለቱ ዳኞች የመቶ ሺህ ብር ዋስትና በመፍቀድ ከእስር ቤት ውጭ ሆኖ እንዲከራከርና ከሀገር እንዳይወጣ ሲወስኑ ጠፍተው የነበሩት ዳኛ የዋስትና መብቱን መነጠቅ አለበት በሚል የልዩነት ውሳኔ አስመዘገቡ። በርግጥ በመጨረሻ የሁለቱ ውሳኔ ፀድቋል። የሚገርመው በልዩነት መውጣታቸው አይደለም፤ ሕጉን የተረጎሙበት አባባል እንጂ፤  የልዩነት ውሳኔያቸውን ሲያብራሩ “ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተመሳሳይ ስህተት የሚፅፍ። ከስህተቱ የማይማር። ዋስትናው ተከብሮ ከእስር ቢወጣም ይህንን ከማድረግ የማይቆጠብ” ነበር ያሉት።

‘ከስህተቱ የማይማር’ ከማለት ውጭ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግስ ምን ሊል ይችላል? ይህ እኮ ከውሳኔም በላይ የጥፋተኝነት ማክበጃም ጭምር ነው። አስቀድመው እዚህ ውሳኔ ላይ ከደረሱ ዳኛ ፍትሕ ጠብቆ እንዴት ነው መከራከር የሚቻለው?

በአጠቃላይ ይህ ዳኛ እና ጠቅላይ ሚንስትር ተብየው በተመስገን ላይ ከክርክሩ አስቀድመው የጥፋተኝነት ውሳኔ ወስነዋል። ከውሳኔ በኋላ መከራከር ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ነው። የቅጣቱን ልክ ስላልበየኑ ተሜ ያለው ዕድል የጥፋት ማቅለያ ማቅረብ ነው። ብቻ ፍርዱም ሆነ ክርክሩ ከሕግ ውጭ ነው!

Filed in: Amharic