>

ሕገ መንግስቱ አማራ ብቻ ሳይሆን ተጋሩ ጠልም ነው... ዜጋ ጠል ..!!! (ግርማ ካሳ)

ሕገ መንግስቱ አማራ ብቻ ሳይሆን ተጋሩ ጠልም ነው… ዜጋ ጠል ..!!!

ግርማ ካሳ

 


ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር ሆኖ አገልግሏል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆነው፣  ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካንም ይወክላል በሚል፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ድጋፍ ስላደረጉለት ነው፡፡

ይህ ሰው ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ፣ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ የደረሰ ነው፡፡ ከርሱ ዓለም አቀፋዊ አመለካከት ፣ አቃፊነትን እንጂ ዘረኛና የጎጥ አመለካከትን ማንጸባረቅ አይጠበቅም፡፡ ለርሱ  ከዓለም አቀፋዊነት ወደ ትግራይ ጎጠኝነት መውረድ አሳፋሪነትና ትንሽነት ነው፡፡

እንደ ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም ያሉትን ሳስብ ለትግራይ ሕዝብ አዝናለሁ፡፡ ተማሩ የተባሉ፣ ትልቅ ደረጃ ደረሱ የተባሉ፣ ከትግራይ ሕዝብ የወጡ፣ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅመውን መረዳትና ማወቅ ሲሳናቸው ከማየት የበለጠ የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ ማንም በትክክል የሚያገናዝብ፣ የሰፋ አይምሮ ያለው ተጋሩ፣ የትግራይ ብሄረተኝነት ፖለቲካ ትግራይን እንደጎዳ መረዳት ይችል ነበር፡፡

እነ ዶር ቴዎድሮስ አዎን በግለሰብ ደረጃ ትልቅ ቦታ ነው ያሉት፣ ግን አሁን የትግራይ ሕዝብ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ???? እስቲ ቆም ብለን እንጠይቅ፡፡

ሕወሃቶች የሚመጻደቁበት እነርሱ ከኦነግ ጋር ሆነው ያመጡት።  የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ የሚሉት፣  የዘር ፖለቲካ፣  የዘር ሕገ መንግስት፣ የዘር አወቃቀር፡፡ ስሜታዊነትን ለጊዜው እንተወውና፣ ሜዳ ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፣ በእጅጉ የትግራይን ሕዝብ የጎዳ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የበለጠ የሚጎዳ እንደሆነ ማየት የሚቻለው፡፡  የትግራይ ሕዝብ ለጦርነት የተዘፈቀው፣ ከጎሮቤት አካባቢዎች ጋር ፣ ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከአፋር፣ ከኤርትራ  ማህበረሰብ ጋር እሳትና ጭድ እንዲሆን የተደረገው  በዘር ፖለቲካው ነው፡፡ በህወሃቶች ጠባብና ዘረኛ እልህና እብሪት፡፡

ለዚህ ነው በኔ እምነት ከማንም በላይ የሕወሃትና የኦነግ  ሕገ መንግስት መቃወም ያለባቸው ተጋሩዎች ናቸው የምለው፡፡  ይሄንንም  ስል በምክንያት ነው፡፡

አሁን ያለውን የዘር ሕግ መንግስት መቃወምና እንዲወገድ መታገል አማራውን መጥቀም አይደለም፡፡ አማራዉን፣ ትግሬዉን፣ ሁሉንም ዜጎች መጥቀም፡፡

ኦፌሲላዊ የሆነ የሕዝብ ቆጠራ የተደረገው ከ15 አመታት በፊት ነው፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ 73 ሚሊዮን ነበር፡፡ አሁን 110 ሚሊዮን ይጠጋል ብንል፣ ቁጥሩ በ44% አድጓል፡፡ በዚህ ቀመር መሰረት የትግራይ ክልል ይባል የነበረው ሕዝብ፣  7 ሚሊዮን  ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ከ7 ሚሊዮኑ 1.3   ሚሊዮኑ በነ ወልቃይትና ራያ የሚኖር ነው፡፡ (900 ሺህ በወልቃይትና ጠለመት፣ 400  ሺህ በራያ)፡፡  ስለዚህ በትግራይ  ያለው 5.7  ሚሊዮን ደረሰ ማለት ነው፡፡

ሌላው በትልቁ መረሳት የሌለበት ነገር አለ፡፡ የዜጎች ፍልሰት፡፡ ከ97 በኋላ እጅግ በጣም ብዙ ተጋሩዎች ትግራይን ለቀው ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ሄደዋል፡፡ በአዲስ አበባ ምን አልባትም ከአማራዎች ቀጥሎ ትልቅ ቁጥር የሚኖራቸው ተጋሩዎች ናቸው የሚል አመለካከት አለ፡፡ የትግራይ ብልጽግና  ከሁለት አመታት በፊት፣  ስብሰባ ላይ፣  ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተጋሩ  ከትግራይ ክልል ውጭ እንደሚኖሩ ሲነገር ሰምቻለሁ፡፡ ከነዚህም ግማሹ ከ97 በኋላ ትግራይን የለቀቁ ናቸው ብለን ብንገምት፣ ግማሹ ከትግራይ የመጡ ናቸው፡፡ ይሁእን ማለት 5.7 ሚሊዮን የተባለው የትግራይ ሕዝብ ቁጥር ወደ ወደ 4.9  ሚሊዮን ያወርደዋል፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት በተደረገው ጦርነት፣ ብዙ ሰው ሕይወቱ አልፏል፡፡ በበሽታ፣ በረሃብ፣ በመድሃኒኡት እጦት ወዘተ፡፡ በጦርነት የሞቱት ግን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ራሳቸውን ህወሃቶች እንዳመኑት፣  300 ሺህ ወጣቶች የት እንዳሉ እንደማያወቁ ነው የተናገሩት፡፡  እነዚህን 300 ወጣቶች ከግምት ስናስገባ፣  በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ያለውን ነዋሪ 4.6 ሚሊዮን ቢሆን ነው ማለት ነው፡፡

ከ 4.6 ሚሊዮን  ተጋሩ አይደለንም የሚሉ ኢሮቦች፣ ኩናማዎች፣ ራያ አዘቦ ውስጥ የሚኖሩ ራያዎች፣ ተንቤን የሚኖሩ ላስታና ዋጎች ነን የሚሉ ወዘተ የመሳሰሉት አሉ፡፡ ኢሮቦች ከአዲግራት በስተሰሜን ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ ኩናማዎች ደግሞምከሽሬ በስተሰሜን ወደነ ሽራሮ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ራያዎች ደግሞ እንደ ነ ማይጨው ባሉ አካባቢዎች፡፡  እነዚህን ተጋሩ ያልሆኑትን ከግምት ብናስገባ፣ አንድ ሚሊዮን ይደርሳሉ ብንል፣ በትግራይ የተጋሩ ቁጥር 3.6 ሚሊዮን ብቻ ነው ሆነ ማለት ነው፡፡

ይህ ቁጥር የአዲስ አበባን ሕዝብ አንድ ሶስተኛ  እንደማለት  ነው፡፡ ከሲዳማ ክልል ጋር የሚቀራረብ ነው የሚሆነው፡፡ የሕዝብ ቆጠራ ተቆጥሮ በፓርላማም ሆነ በሌሎች መድረኮች፣ የትግራይ ድርሻ ሲታይ  እጅግ በጣም አናሳ ነው የሚሆነው፡፡ አናሳ ሲኮን ደግሞ  ተሰሚነትና ተጽኖ ፈጣሪነት፣ በጎሳ ፖለቲካ በጣም ነው የሚቀንሰው፡፡ የትግራይ ክልል እጅግ በጣም ደካማ ክልል ነው የምትሆነው፡፡ በዘር፣ በክልል የመስራቱና የማሰቡ ነገር ስላለ ለትግራይ ኪሳራ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን አንዱን ትልቁ ነጥብ፡፡

በትግራይ ያለውንና ከትግራይ ውጭ ያለው ተጋሩ ስንደመር (3.6 + 1.5)   5.1 ሚሊዮን ይሆናል፡፡ ያ ማለት ከትግራይ ውጭ የሚኖረው ተጋሩ በአገር ደረጃ  ካሉ ተጋሪዎች  30%  የሚደርስ ይሆናል፡፡

ይህ 30% የሚሆነው፣ ከትግራይ ውጭ የሚኖረው ተጋሩ፣አሁን ባለው ሕገ መንግስት አወቃቀር መሰረት፣ አዲስ አበባ፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሞ ክልል ወዘተ አገሩ አይደለም፡፡ አገርህ ትግራይ ነው፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ፣ መጤ ነህ ቢባል የሚሰጠው መልስ  አይኖረውም፡፡ አሁን ያለውን ሕገ መንግስት የሚደግፍ ተጋሩ፣ በኦሮሞ ክልል ቅድሚያ ለኦሮሞ፣ በአማራ ክልል ቅድሚያ ለአማራ ቢባል ምን ብሎ ነው ብሶት የሚያሰማው ?  ለምን የርሱ አገር አይደሉማ፡፡  እርሱ የባለቤትነት መብት ያለው ጎንደር፣ ጂጂጋ፣ አዋሳ ወዘተ ሳይሆን መቀሌና አክሱም የመሳሰሉት ብቻ ስለሆነ፡፡ ደግሜ እላለሁ፣ ይህን ስል  አሁን ባለው ሕገ መንግስት መሰረት ነው፡፡ እንጂ በመሰረቱ የተጋሩ አገሩ መላው ኢትዮጵያ ነው፡፡

በአህኑ ወቅት በትግራይ ከፍተኛ ችግር ነው ያለው፡፡ አብዛኛው ተጋሩ ትግራይን ለቆ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመንቀሳቀስ መስራት፣ መሻሻል ወዘተ ይፈልጋል፡፡ መብቱም ነው፣ ለምን ወያኔዎች አገርን ትግራይ ብቻ ነው አሉት እንጂ፣ መላው ኢትዮጵያ የተጋሩ መሬት ነው፡፡ ተጋሩዎች ጠንካራዎች ናቸው፡፡ በሄዱበት  ብዙ መሻሻሎችን የሚያመጡ ታታሪዎች ናቸው፡፡ ግን አሁን ባለው የዘር ፖለቲካና የጎሳ አወቃቀር ምክንያት፣ በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል በነጻነት መስራት፣ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው የሆነባቸው፡፡  ህወሃት አራት ኪሎ ይዛ የነበረ ጊዜ፣ ባንኩም ታንኩም እነርሱ ጋር ስለነበረ ያኔ ችግህር አለነበረም፡፡  አሁን ግን የተለየ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ ነጥብ ሁለት ነው፡፡

ለዚህ ነው አሁን ያለው ሕግ መንግስትና የጎሳ አወቃቀር ተጋሩን የሚጎዳ ነው የምለው፡፡

Filed in: Amharic