>

ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራናት ይሏታል...!!! (ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራናት ይሏታል…!!!

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቅዱስ ሲኖዶሱ መልካም ፈቃድ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለህክምና  እንደሚሄዱ ሐምሌ ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ ባስታወቁት መሠረት ጉዞውን ወደሚያደርጉበት ሀገር በቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና ይዘዋቸው ሊጓዙ ከነበሩት ነዋየ ቅድሳት ጋር በተገናኘ በቅዱስነታቸው ላይ የደረሰው አላስፈላጊ ማጉላላት እና ስም የማጥፋት ዘመቻ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” መሆኑ አሳፋሪ ድርጊት ነው።

ቅዱስ ፓትሪያርኩ  ይዘውት ሊጓዙ የነበሩት ንዋየ ቅድሳት በቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ በግልጽ በተጻፈ ደብዳቤ የሚመለከተው አካል እንዲያውቀው መደረጉ እየታወቀ በቅዱስነታቸው ላይ የተፈጸመው ማጉላላታት እና ስም ማጥፋት ሃይማኖቱ ላይ ብሎም ሀገር የሆነችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተነጣጠረ ሴራ ነው። ከዚህ በፊት ለሃያ ሰባት  ዓመታት ተቋሟን ለሁለት በመክፈል ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳከም ተንኮል ሸራቢዎች ያለፈው ስህተት ሳይጸጽታቸው “ጊዜው የእኛ ነው” ባዮች መሰል ድርጊት ለመፈጸም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ታሪክን መልሶ ለመድገም የሚደረግ ደባ ተቀባይነት የለውም።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ሽማግሌዎችን እና ሀገር አጽንተው ያቆዩ ተቋማትን መዝለፍ፣ ማዋረድ የፓለቲካ እውቀት መለኪያ እስኪመስል ድረስ ሆን ተብለው የሚፈጸሙ የሴረኞቹ ስልት ሲሆን በቅዱስነታቸው ላይ የደረሰውም የዚሁ ሴራ አካል ነው።

ጉዳዩ የሚመለከታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳቱ የሚወጡት በእኔ እውቅና ነው እያለች የተቋሟን ውሳኔ በሚጻረር መልኩ ተቆርቋሪ በመምሰል የተፈጸመው ድርጊት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተቃጣ አደጋ መሆኑ ታውቆ የመንግስት አካላት እና የመንግስት ተከፋይ የስም የማህበረሰብ አንቂዎች ነን ባዮች ከመሰል ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እያሳሰብን የእምነቱ ተከታዮች ብሎም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሊመክሩን ሊያስተምሩን የሚችሉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ላይ በግለሰቦችም ሆነ በቡድን የሚፈጸም ስም ማጥፋት ዓላማው ሀገር ጸንታ የቆመችባቸውን ተቋማት በማፍረስ ኢትዮጵያን እነሱ በሚፈልጉት ወርድና ቁመት ልክ ለመስፋት  የሚደረግ መፍጨርጨር በመሆኑ እነዚህን የህልውናችን መሰረት የሆኑ ተቋማት ነቅተን እንድንጠብቅ ፓርቲያችን ጥሪውን ያስተላልፋል።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

ሐምሌ ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic