ኦህዴድ ብልጽግና ኢሕአዴግ ከተጓዘበት በከፋ መልኩ በአገር አጥፊነት መንገድ እየተጓዘ ነው….!!!
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
*… አገራችን ሀላፊነት በማይሰማው እጅ ላይ መውደቋ የሰሞኑ የገዢው ቡድን ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ከበቂ በላይ አስረጅዎች ናቸው!!!”
በ«ብሔራዊ ውይይቱ» የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የአዲስ አበባ ህዝብና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ውይይት አድርገውባቸው እና መክረው መግባባት ላይ ይደርሱባቸዋል ወይም ደግሞ በህዝበ ውሳኔ ብያኔ ያሳርፉባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ አጨቃጫቂና አገራዊ የቅራኔና ያለመግባባት መንስዔ ከሆኑ አንኳር ጉዳዮች አንዱ የአዲስ አበባ አስተዳደራዊና የወሰን ማካለል ጉዳዮች እንደሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው።
በነዚህ አይነት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ ውይይት ሳይደረግባቸው የኦሮሞ ብልጽግና በግራም በቀኝም ዋነኛ ተዋናይ የሆነበት እና መጨረሻው ቀድሞ የሚታወቅ ድራማ እየተሰራ ነው።
የኦሮሞ ብልጽግና ኦሮሞ ክልልን እና አዲስ አበባ መስተዳድርን ወክሎ የሚሰራው የ«አዲስ አበባ» እና «ኦሮምያ» ክልልን ወሰን ማካለል ድራማ ሁለት ነገሮችን በግልጽ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።
1) ገዢው ኦህዴድ መራሹ «ብልጽግና ፓርቲ» ለብሔራዊ ውይይቱ ደንታ እንደሌለውና በብሔራዊ ውይይቱ ላይ «የእኔው የእኔ ነው፣ በአንተው ላይ ግን እንነጋገር፣ እንደራደር» በሚል መርህ ብቻ ለመሳተፍ እንጅ በሰለጠነ ውይይት በሚደረስበት «ፍትሐዊ አማካኝ» ላይ በመሳተፍ ፍላጎቱን ማስፈፀም የማይፈልግ ይሉኝታ ቢስ ቡድን መሆኑን፣ በዚህም የብሔራዊ ውይይቱ ገና ከመነሻው በገዢው ቡድን የተጨናገፈ ሂደት መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን
2) ኦህዴድ/ኦሮሞ ብልጽግና «በብልጽግና» ወስጥ ሲካሄድ የቆየውን ውስጠ ድርጅት የስልጣን ትግል በበላይነት ደምድሞ፣ የፈለገውን ውሳኔ በሌሎች የብሔሮች ቅርንጫፎቹ ላይ መጫን በሚችልበት ቁመና ላይ መድረሱን አመላካች ነው።
ከመጀመሪያውም ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደተናገርነው ብልጽግና ፓርቲ ኢሕአዴግ ከተጓዘበት በከፋ መልኩ በአገር አጥፊነት መንገድ እየተጓዘ ነው።
አገራችን ሀላፊነት በማይሰማው እጅ ላይ መውደቋ የሰሞኑ የገዢው ቡድን ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ከበቂ በላይ አስረጅዎች ናቸው።