እሾህን በእሾህ ነውና የክልልነትን ጥያቄ ያነሡ ወገኖችን እንደግፍ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
*… አገዛዙ “የክልልነትን መዋቅር ጥያቄ የሀገሪቱ አቅም ከዚህ በኋላ ሊያስተናግድ ወይም ሊሸከም አይችልም፣ የድንበር ይገባኛል ግጭቶችን መበራከት ነው የሚያስከትለው ይሄም ሀገሪቱን የቀውስ ማጥ ውስጥ ከቶ ያፈርሳታል … !” የሚል ከሆነ ወይ ይሄንን ጥቂቱን ባለመብት አብዛኛውን መብት አልባ ያደረገውን ጠንቀኛውን የዘር የክልል መዋቅር መብትን ሙሉ ለሙሉ ያስቀር ወይ ደግሞ ያለ አንዳችም አድሎ ክልልነትን ለጠየቁ ወገኖች ሁሉ ያለምንም ማወላዳት ይስጥ!!!
ወጥር ጉራጌ!!!
ጠንቀኛው የጎሳ ወይም የዘር የክልል መዋቅር እንዲቀር የማይደረግ ከሆነ የጎሳን ወይም የዘር ክልልን በትግላችን እስናጠፋው ድረስ እሾህን በእሾህ ነውና ነገሩ “ሁሉም ብሔረሰቦች ዕኩል ናቸው፣ ዕኩል መብት አላቸው!” ከተባለ የክልልነት መብት ለአንዱ ተፈቅዶ ለሌላው የሚከለከልበትና ሕዝባቸው በአሥተዳደር በደል፣ በብሮክራሲ ውጣውረድና በፖለቲካ ሴራ ሕዝብ በአንድ ቅርጫት ታጉሮ መቸገርና መንገላታት፣ መብትና ጥቅሙንም ማጣት ስለሌለበት ብሔረሰቦች የክልልነት ጥያቄ እንዲያነሡ እንድንቀሰቅስ ጥሪ ያቀረብኩት ለውጥ ከምትሉት ድራማም በፊት ነው!!!
ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ ጽፌያለሁ፡፡ ኢትዮ 360ዎችን ጨምሮ ዛሬ የክልልነት ጥያቄ ያነሡ ወገኖችን ደግፈው የቆሙ ሁሉ ጨዋታውና ፖለቲካው ስላልገባቸው በወቅቱ ተቃውመውኝ ነበር!!!
አንድ ሕዝብ ወይም ብሔረሰብ በክልል መዋቅር እንዳይዋቀር ምንም የሚከለክል ሕግና መስፈርት በሌለበትና መስፈርቱ የሕዝቡ ወይም የብሔረሰቡ ጥያቄና ፍላጎት ብቻ በሆነበት ሁኔታ አገዛዙ ለአንዱ ፈቅዶ ለሌላው የሚከለክልበት ምንም ዓይነት አሠራር ሊኖር አይችልም፡፡ ያለው አሠራር ሕገወጥና አንባገነናዊ አሠራር በመሆኑ አጥብቀን ልንቃወመውና ልንዋጋው ይገባል!!!
አገዛዙ “ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዕኩል መብት አላቸው!” ብሎ ሕገመንግሥት በሚለው ሰነዱ በደነገገበት ሁኔታ ለሁሉም ያልፈቀደውን ወይም ያልሰጠውን የክልልነትን መብት ለጥቂት ብሔረሰቦች መፍቀድ ወይም መስጠት አልነበረበትም ወይም የለበትም!!! አሠራሩ የለየለት አድሏዊና ኢፍትሐዊ አሠራር ነው!!!
አገዛዙ “የክልልነትን መዋቅር ጥያቄ የሀገሪቱ አቅም ከዚህ በኋላ ሊያስተናግድ ወይም ሊሸከም አይችልም፣ የድንበር ይገባኛል ግጭቶችን መበራከት ነው የሚያስከትለው ይሄም ሀገሪቱን የቀውስ ማጥ ውስጥ ከቶ ያፈርሳታል … !” የሚል ከሆነ ወይ ይሄንን ጥቂቱን ባለመብት አብዛኛውን መብት አልባ ያደረገውን ጠንቀኛውን የዘር የክልል መዋቅር መብትን ሙሉ ለሙሉ ያስቀር ወይ ደግሞ ያለ አንዳችም አድሎ ክልልነትን ለጠየቁ ወገኖች ሁሉ ያለምንም ማወላዳት ይስጥ!!!
አገዛዙ ሲያደርገው እንደቆየውና አሁንም እያደረገው እንዳለው የራሱን ሕግ በሚፃረር መልኩ የክልልነት ጥያቄ የመብት ጥያቄ መሆኑን ማመንና መቀበል ትቶ የራሱ ችሮታ ጉዳይ አድርጎት ከቀጠለ ግን ከሕዝብ ጥቅም በተፃራሪ ለራሱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሴራ እንዲመቸው ያሰበው ሸፍጥ አለ ማለት ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን የአገዛዙን ሸፍጠኛና ሕገወጥ አሠራር አጥብቆ ማውገዝና መዋጋት አለበት!!!