ካራማራ በአዲስ መዝገብ
ጌጥዬ ያለው
ዝም ከተባሉ አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ገና ሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች ሁሉ በቅብብል ያስሩታል። ከወራሪዎቹ ወገን ነን የሚሉ የግል ኩባንያዎችም አሳሪ፣ ከሳሽ እና ፈራጅ ሆነው ከች ሊሉ ይችላሉ። ጀንበራቸው እስክትጠልቅ ግፋቸው የትየለሌ ነው።
ለማንኛውም የሥርዓቱ አስጨናቂ በኩላሊት ህመም እየተሰቃየ ህክምና ተከልክሏል። በባሕር ዳር ከታፈነ ወዲህ ለ3ኛ ጊዜ በተከፈተበት ምርመራ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት የቀረበ ሲሆን ለተጨማሪ ምርመራ በሚል ለነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።
ስንትሽ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በድርጅት ሥራ ላይ እያለ አፋቸውን ባልፈቱ የወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና የስለላ ሠራተኞች በባሕር ዳር ታፈነ። የባሕር ዳሩ ማዕከላዊ በተባለው አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ መብራት፣ ውሃ እና ፍራሽ በሌለበት ተባያማ ክፍል ተቀጣ። የጣቢያው ኮማንደር እንደሚገድለው ሲዝትበት ሰነበተ። ዘለግ ላሉ ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በአደራ ታሳሪነት ታገተ።
ይህንን ተከትሎ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በፖሊስ ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መሰረተ። የባሕር ዳር ወረዳ ፍርድ ቤትም መዝገቡን ከፍቶ ለሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ፖሊስ ስንታየሁን ይዞ እንዲቀርብ አዘዘ። በማናለብኝነት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሻረ። የችሎቱን ጥሪ እንደ ቡና ጠጡ ጥሪ ቆጥሮት ፖሊስ አጣጣለው።
በብዙ ግፊት ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጥሪ ያደረገው ፍርድ ቤት ሥልጣኑ የለህም ተብሎ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ስንትሽ የአማራ መስተዳድር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀረበ። በዚህም ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በማሰብ ብሎም ሕዝብና መንግሥት እንዳይተማመኑ በፌስቡክ በመቀስቀስ ተብሎ በሐሰት ተወየጀለ። ወንጃዩ የፌዴራል ፖሊስ ነው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ከችሎት ሲወጣ ይኸው ፖሊስ አፍኖ ለመውሰድ ያደረገው ሙከራ በአማራ ፖሊሶች ተቃውሞ ከሸፈ። ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎት መቅረቡን ተከትሎ ከአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ባሕር ዳር ሰባታሚት ወህኒ ቤት ተዘዋወረ።
ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ተወሰነ። ሆኖም በዚሁ ዕለት ምሽት የሰባታሚት ወህኒ ቤት በራፍን ሳይራመድ የፌዴራል ፖሊሶች አፍነው በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ አመጡት። ሜክሲኮ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ አሰሩት። በዚህ ቢሮ ውስጥ ከዕለታት በአንዱ ቀን ጎርፍ ገብቶ ክፍሉን በማጥለቅለቁ ከሌሎች እስረኞች ጋር ከስቃይ ላይ ስቃይ ተሰቃየ። በዚህ እስር ቤት ውስጥ ቤተሰቦቹ እንዳይጠይቁት በተደጋጋሚ ይከለከል ነበር። ከሐምሌ 30 ጀምሮ አድራሻው ሁሉ ጠፍቶ ቆየና በብዙ ጭንቀትና ፍለጋ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ አባ ሳሙኤል ወህኒ ቤት መዘዋወሩ ታወቀ።
ከዚህ በፊት ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ ምርመራ ተከፍቶበት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ቀርቧል። ውንጀላው ከባሕር ዳሩ መዝብ ጋር በፍሬ ነገር ተመሳሳይ ነበር። ልዩነቱ “አማራ በጅምላ ሳይጨፈጨፍ በጅምላ ተጨፍጭፏል ብለሀል” የሚል ታሪካዊ ውንጀላ መጨመሩ ነው።
ከአንድ ወር በላይ ክርክር በኋላ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሀገር እንዳይወጣ ታግዶ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወሰነ። ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ተፈች ተብሎ አስጨናቂ ስሙ ሲጠራ በጭብጨባ ሸኙት። የሆነው ግን የሚያስጨበጭብ ሳይሆን የሚያሳዝን ነበር። በር ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ መኪና ከእነ ሹፌሩ አሰናድቶ ጠበቀው። ስንትሽን አጅበው ወደ ቤታቸው ለመውሰድ ባለቤቱና ልጆቹ በር ላይ እንደቆሙ እንደ አዲስ እስረኛ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ማለትም ማዕከላዊ ገባ።
ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ሦስተኛ የምርመራ መዝገብ ተከፍቶበት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ቀረበ። ከቅብብሎሽ እስሩ እኩል የሚገርመው በዚህ መዝገብ ከቀረቡበት የሀሰት ውንጀላዎች መካከል ከ40 በላይ የባልደራስ አባላት እና በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች በዚሁ ፍርድ ቤት ከአንድ ወር በላይ ታስረን በዋስትና የወጣንበት የካራማራ ውንጀላ ተመልሶ መምጣቱ ነው። የዘንድሮው የካራማራ የድል በዓል አባበር ላይ ከታፈስን ሰዎች ጋር ስንትሽም አብሮን ነበር። መኖር ብቻ ሳይሆን ለሰዓታት ልደታ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ አብሮን ታስሮ ነበር። ሆኞም እኛ ስንታሰር በፖለቲከኞች ውሳኔ ‘እርሱን ለማሰር ጊዜው አይደለም’ በሚል እንድምታ ከሌሎች አመራሮች ጋር የምርመራ መዝገብ ሳይከፈትበት ተፈቷል። ዛሬ ጊዜው ሆነና ካራማራን በድጋሜ ታሰረበት።
የእነርሱ ጭንቀት እና የእኛ ዝምታ በዚህ ከቀጠለ ስንትሽን ገና ሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ሁሉ እየተቀባበሉ ያስሩታል። ላንታሰር አልታገልንም፤ ላንሞት አልተወለድንም! ወራሪዎች ሆይ አምላክ በሌላ ሜዳ ያገናኘን!