>

ማቆሚያ ያጣው መከራችን...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ማቆሚያ ያጣው መከራችን…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ትላንት በመቀሌ የተደረገውን የአየር ድብደባ በተመለከተ የቪኦኤው ዘጋቢ በቪዲዬ አስደግፎ ያቀረበው ዘገባ እጅግ ልብ የሚሰብር፣ የሚያሳዝና እና አስደንጋጭም ነው። ተኩስ አቁሙ በፈረሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግጭቱ ከድንበር አካባቢዎች አልፎ መቀሌን ኢላማ ማድረጉ ወደ መጥፎ ሁኔታ መልሰን እየገባን መሆኑን ማሳያ ነው። የጥቃቱን ኢላማ ላይ ሁለቱም ወገኖች የተለያየ መረጃ ቢሰጡም ሲቪሊያን መጎዳታቸውን ግን የቪኦኤ ዘጋቢው በአይኑ ያረጋገጠውን በፊልም አስደግፎ ዘግቧል። ከወራቶች እረፍት በኋላ አለም ሁሉ ሰላም ሊወርድ ነው ብሎ በጉጉት ሲጠብቅ እንዲህ  ያለ አሰቃቂ ነገር ዳግም መስማትና ማየት እጅግ ያስከፋል፣ ያሳዝናል። አሁንም ተኩስ ቆሞ የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ሕዝብና አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጫናውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ከተሞችን ያማከሉ ተመሳሳይ የአየር ጥቃቶች የንጹሀንን ህይወት የመቅጠፍ እድላቸው ሰፊ ነው። መንግስት አስቀድሞ ንጹሀን ዜጎች ከወታደራዊ የጥቃት ኢላማ ሥፍራዎች ይራቁ የሚል መግለጫ ቢያወጣም መብራትና ኢንተርኔት ለሌለው፣ ከክልሉ ሬድዬና ቴሌቪዥን ሌላ አማራጭ ሚድያ ማግኘት የማይችለው  የትግራይ ሕዝብ በምን እና እንዴት ማሳሰቢያው ሊደርሰው ይችል ይሆን? የሚል ስጋትና ጥያቄ አጭሮብኝ ነበር። ስለሆነም በትግራይ ህጻናት፣ ሴቶች፣  እናቶች፣ የአልካ ቁራኞች እና ከጦር ቀጠናዎች እሮጠው ማምለጥ ለማይችሉት ወገኖች ሲባል መንግስት ከተሞች ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃቶችን ከመሰንዘር እንዲታቀብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እና እንደ ሰው መንግስትን እማጸናለሁ።😭 ትላንት በጥቃቱ ለተጎዱት ወገኖቼ ከልቤ አዝናለሁ። ነፍስ ይማር! ። እንደተባለው ኢላማ የተደረገው የሲቪሊያን መኖሪያ እና የመዋዕለ ሕጻናት ከሆነ የከፋ የአለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ስለሆነ መንግስት በጉዳዩ ላይ በቂ ማብራሪያ ቢሰጥበት ጥሩ ነው። የህውሃት መሪዎችም በትግራይ ሕዝብ ህይወት መቆመራቸውን አቁመው ለሰላም ድርድር እድል እንዲሰጡ እማጸናለሁ። አሁንም ለሰላምና ለድርድር እድሎች አሉ።

▶️፡ የመቀሌ የአየር ድብደባ

ቪኦኤ

የኢትዮጵያ መንግሥት “ሲቪሎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት ፈፅሟል” ሲል ህወሓት ከሰሰ።

የትግራይ የውጭ ጉዳዮች ቢሮ የተባለው አካል ባወጣው መግለጫ “መቀሌ ውስጥ ወታደራዊ ዒላማ በሌለበት የህፃናት መጫወቻ ሥፍራና መዋዕለ ህፃናት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል” ብሏል።

የመቀሌ ሪፖርተራችን የአይደር ሆስፒታል ኃላፊዎችን አነገግሮ በሰጡት መግለጫ ሁለት ህፃናትን ጨምሮ አራት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንደነገሩት ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ሲቪሎች ላይ የተፈፀመ ድብደባ አለመኖሩን ገልፆ ክሱን ማስተባበሉንና ዒላማው ወታደራዊ ተቋማት መሆናቸውን መናገሩን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የአየር ጥቃቱ ዘገባ ከመሰማቱ በፊት የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ የተመረጡ የሕወሃት ወታደራዊ ይዞታዎችን እንደሚመታ ገልፆ ሲቪሎች ወታደራዊ ትጥቆችና ማሰልጠኛዎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር ታውቋል።

ሁለቱም አካላት ግጭቱን በማቆም ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሃገር ውስጥ አካላትና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ተማፅኖ እያሰሙ ቢሆንም ሁኔታው እስካሁን የመብረድ አዝማሚያ እንደሌለው ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን “ህወሓት ዘርፎታል” የተባለውን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንዲመልስ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወርና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሃፊና የአስቸኳይ ድጋፍ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ አድራጎቱን አውግዘዋል።

ይሁን እንጂ ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ “ነዳጅ አልዘረፍኩም” ብሏል።

[ሙሉውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ]https://fb.watch/f9Nq2fPvxe/

Filed in: Amharic