>

ለፋኖ አደረጃጀት የቀረበ መነሻ ሐሳብ (መስፍን አረጋ)

ለፋኖ አደረጃጀት የቀረበ መነሻ ሐሳብ

መስፍን አረጋ

የወታደራዊ አደረጃጀት ዝርዝር ሚስጥራዊ መሆን ያለበት ቢሆንም፣ መሠረታዊ መዋቅሩ ግን በግልጽ የሚታወቅና መታወቅም ያለበት ነው፣ ወታደሮች የሚመለመሉት እሱን መሠረት በማድረግ ነውና፡፡  ስለ ፋኖ አደረጃጀት መነሻ ሐሳብ ለማቅረብ የተነሳሁትም በዚሁ እሳቤ መሠረት ነው፡፡

 

ፀራማራ ሥላሶች

የአማራ ሕዝብ ወያኔ፣ ኦነግና ብአዴን  የሚባሉ ሦስትም አንድም የሆኑ ፀራማራ ሥላሶች በለኮሱበት እቶን እሳት እየተለበለበ ነው፡፡  ስለዚህም የአማራ ሕዝብ እነዚህን ፀራማራ ሥላሶች ባስቸኳይ ካላጠፋቸው በስተቀር በእቶን እሳታቸው ተንጨርጭሮ መጥፋቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  እነዚህ ፀራማራ ሥላሶች ለማጥፋት ደግሞ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት (ፋኖ) በሦስት ዘርፎች ሊደራጅ ይችላል፡፡  እነዚህ የፋኖ ሦስት ዘርፎች ደግሞ ደመላሽ ፋኖሳተና (ተወርዋሪ) ፋኖ፣ እና ደጀን ፋኖ ሊባሉ ይችላሉ፡፡  

ደመላሽ ፋኖ

ደመላሽ ማለት የደም ብደር ከፋይ፣ ተበቃይ፣ ገዳይን ገዳይ ማለት ነው (አለቃ ደስታ ተክለወልድ ገጽ 356 ይመልከቱ)፡፡  የአማራ ሕዝብ ዋና ገዳይ የኦነግ ጠቅሊሞ (generalissimo) የሆነው ጭራቅ አሕመድ ቢሆንም፣ ይህ ጭራቅ አማራን የሚዘነጣጥልባቸው ጥርሶቹ ግን ብአዴኖች ናቸው፡፡  

የአማራ ሕዝብ ለዚህ ሁሉ ውርደት የተዳረገው በወያኔና በኦነግ ኃይል ሳይሆን ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጡሩነህ፣ ሰማ ጥሩነህ፣ አበባው ታደሰ፣ ግርማ የሽጥላና እነሱን የመሳሰሉ ብአዴኖች የአማራን ሕዝብ በገፍና በግፍ እያስጨፈጨፉ በራሱ በአማራ ሕዝብ መኻል ዝንባቸው እሽ ሳይባል ተኩራርተው እንዲኖሩ ስለተፈቀደላቸው ብቻና ብቻ ነው፡፡  

 ስለዚህም የደመላሽ ፋኖ ተግባር አማራን እያረዱና እያሳረዱ ያሉትን የወያኔ፣ የኦነግና የብአዴን አመራሮች፣ መውጫ መግቢያቸውን አጥንቶ፣ ባስፈላጊው መንገድ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ነው፡፡  በተለይም ደግሞ ጭራቅ አሕመድን ጨርቅ ማድረግ ይዋል ይደር የማይባል ነው፡፡  ደመላሽ ፋኖ ማለት ሻቢያ ፈዳይ ይለው የነበረው ዓይነት ነው፡፡  

ሳተና (ተወርዋሪ) ፋኖ

ሳተነ የሚለው ቃል የተገኘው ሰየጠነ ከሚለው ቃል ሲሆን ትርጉሙም በረታ፣ ሮጠ፣ ቀለጠፈ፣ ፈጠነ ነው፡፡  ስለዚህም ሳተና ማለት የሚሳትን፣ ብርቱ፣ ሯጭ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ ማለት ነው፡፡  በመሆኑም ሳተና ፋኖ (commando fanno) ማለት ተወርዋሪ ፋኖ ወይም ፈጥኖ ደራሽ ፋኖ ማለት ነው፡፡ 

የሳተና ፋኖ ተግባር የአማራ ጠላት አማራን ለማጥቃት ከመዝመቱ በፊት ገና ሲዘገጃጅ እቦታው ድረስ በድንገት ተወርውሮ ጠላትን ደምስሶ እቅዱን ከጅምሩ ማምከን ነው፡፡   ሳተና ፋኖ ባውሎ ነፋስ ይመሰላል፡፡  አውሎ ነፋስ ባልታሰበበት ሰዓት ካልታሰበበት አቅጣጫ በድንገት ነፍሶ፣ የሚጠራርገውን ጠራርጎ ወዳልታሰበበት አቅጣጫ  ይነጉዳል፡፡  ሳተና ፋኖም እንደዚሁ፡፡  

ሳተና ፋኖ በመብረቅም ሊመሰል ይችላል፡፡  መብረቅ ሲበርቅ እንጅ መቸና በየት በኩል እንደሚበርቅ አይታወቅም፡፡  ከበረቀ በኋላ ደግሞ ዓይን ቢጨፍኑ ዋጋ የለውም፡፡  ሲበርቅ ቢጨፍኑ ከመወጋት አይድኑ፡፡ 

ጠላት መጠቃት ያለበት የኔ ነው በሚለው በራሱ ቀጠና ውስጥ ማንም አይነካኝም ብሎ ዘና ባለበት ሁኔታ ነው፡፡  ኦነግ መመታት ያለበት ወደ ላኮመልዛ ተሻግሮ አማራን ከማረዱ በፊት ቢዛም (ወለጋ) ላይ ነው፡፡  ወያኔም ቢሆን ተከዜን እንዲሻገር ሊፈቀድለት አይገባም፡፡  ስለዚህም የሳተና ፋኖ ተግባር ጠላትን እራሱ እጠላት ቀጠና ውስጥ መቀጥቀጥ ነው፡፡         

ደጀን ፋኖ

ደጀን የሚለው ቃል የተገኘው ደገነ (ጠመንዣን አጎረሠ፣ ቃታ ያዘ፣ አነጣጠረ) ከሚለው ቃል ሲሆን፣ ትርጉሙም በስተኋላ ሁኖ የሚጠብቅ፣ የኋላ ዘበኛ፣ ረዳት ሠራዊት ማለት ነው፡፡  የደጀን ተመሳሳይ ቃል ወቦ (ወዎ) ሲሆን፣ ትርጉሙም የፊታውራሪ አንጻር፣ የኋላ ጠባቂ፣ የቆሰለ አንሺ፣ የሞተ ቀባሪ ማለት ነው (አለቃ ደስታ ተክለወልድ ገጽ 353፣ 405፣ 419 ይመልከቱ)፡፡  

ስለዚህም የደጀን ፋኖ ተግባር በገዛ ራሱ ቀጠና ላይ ተሰማርቶ የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ማስከበር ነው፡፡  ተጨማሪ ተግባሩ ደግሞ ለተወርዋሪ ፋኖ እና ደመላሸ ፋኖ የሠራዊት ምንጭ መሆን ነው፡፡  

 አንድም ሦስትም ፋኖ (ሥላሴ ፋኖ)

 የአማራ መሠረታዊ ጠላቶች ወያኔ፣ ኦነግና ብአዴን አንድም ሦስትም እንደሆኑ ሁሉ፣ የአማራ ቤዛ የሆኑት ደመላሽ ፋኖ፣ ተወርዋሪ ፋኖ እና ደጀን ፋኖ አንድም ሦስትም መሆን አለባቸው፡፡  

የአካል ብልቶች ብዙ ቢሆኑም፣ የአንድ በአንድ ለአንድ ናቸው፡፡  ዓይን ጆሮን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የደንቆሮ ዓይን ይሆናል፡፡  ጆሮ ዓይንን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የእውር ጆሮ ይሆናል፡፡  እጅ እግርን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የስንኩል እጅ ይሆናል፡፡  እግር እጅን ንቆ አያስፈልገኝም ቢል፣ የዱሽ እግር ይሆናል፡፡  

የፋኖ መሪ የመጀመርያው ተግባር ሁሉም የፋኖ ክፍሎችና አባሎች ላንድ ዓላማ ባንድነት የቆሙ አንድ መሆናቸውን በማሳመን በመካከላቸው ፋኗዊ ፍቅርና መከባበር እንዲያደር በማድረግ አንተ ትብስ አንቺ ትብስን ማስፈን ነው፡፡  መናናቅ አብሮ ለመወደቅ፣ መከባበር አብሮ ለመናር፡፡   

Email:  mesfin.arega@gmail.com

 

Filed in: Amharic