>

የአማራ ሕዝብ ትልቅ ፈተና ለአማራ ሕዝብ የከፈተው ትልቅ ዕድል  (መስፍን አረጋ)

የአማራ ሕዝብ ትልቅ ፈተና ለአማራ ሕዝብ የከፈተው ትልቅ ዕድል  

 

መስፍን አረጋ

አበሳ ወይ ሊጥል ወይ ሊያነሳ

(What doesn’t kill you makes you stronger)

 

    መከራህ ለጊዜው ቢመስልህም ጎጅ

    ያጠነክርሃል አይግደልህ እንጅ፡፡

    ብረት ወርቅ ተብሎ የሚከብረው ገ(ን)ኖ

    ካለፈ ብቻ ነው በሳት ተፈትኖ፡፡

    

የአማራ ሕዝብ በጭራቅ አሕመድ ዘመን የገጠመው ያሁኑ የሕልውና ፈተና ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በግራኝ አሕመድ ዘመን ከገጠመው የሕልውና ፈተና እጅግ የከፋ ነው፡፡  ያሁኑን የሕልውና ፈተና እጅግ የከፋ ያደረገው ደግሞ በአማራወቹ ነገስታት በነ አጤ ልብነድንግል እና አጤ ገላውዲወስ ከፍተኛ ተጋድሎ የሉባ ጭፍጨፋ እንዳይደርስበት የተደረገው የትግሬ ሕዝብ፣ ከዘመናችን ሉባ (ጭራቅ አሕመድ) ጋር እጅና ጓንት ሁኖ የአማራን ሕዝብ በጀርባው እየጨፈጨፈው መሆኑ ነው፡፡  

በሌላ በኩል ግን ሳይደግስ አይጣላምና  ወይም ደግሞ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ሁሉም ደመና ጸዳል አለውና (every cloud has a silver lining)፣ ጭራቅ አሕመድ ዝንጀሮ አነግሳለሁ ብሎ የተኛ አንበሳ ቀስቅሷል፡፡  በዚህም ምክኒያት ያሁኑ የአማራ ሕዝብ ትልቅ የሕልውና ፈተና ለአማራ ሕዝብ ትልቅ ዕድል ፈጥሮለታል፡፡  ይህም ትልቅ ዕድል ዘርፈ ብዙ ቢሆንም፣ ዋና ዋናወቹ ግን የሚከተሉት ሦስቱ ናቸው፡፡

  1. ጦቢያን፣ ጦቢያዊነትንና የጦቢያዊነትን ትውፊቶች ሁሉንም ያማራ ሕዝብ የግሉ ብቻ ማድረግ፡፡
  2. የአማራን ሕዝብ ዐጽመ ርስት ሁሉንም የምታጠቃልል፣ አማራነት የገነነባትን አዲሲቷን አማራዊት ጦቢያ መመሥረት፡፡
  3. አማረኛ በአማራዊት ጦቢያ ውስጥ እንግሊዘኛን ሙሉ በሙሉ እንዲተካና ካፍሪቃ ወል ቋንቋወች (lingua franca) ውስጥ አንዱና ዋናው እንዲሆን ማድረግ፡፡ 

የአማራ ሕዝብ ትልቅ የሕልውና ፈተና ለአማራ ሕዝብ እነዚህን ሦስት ትላልቅ ዕድሎች እንዴት እንደፈጠራቸው በዝርዝር እንመልከት፡፡ 

 

አንደኛ ትልቅ ዕድል፤ ጦቢያን፣ ጦቢያዊነትንና የጦቢያዊነትን ትውፊቶች ሁሉንም ያማራ ሕዝብ የግሉ ብቻ ማድረግ

የኦሮሞ ጽንፈኞች መፈክር ጦቢያ ከኦሮሚያ ትውጣ (Ethiopia out of Oromia) ሲሆን፣ የትግሬ ጽንፈኞች ትእዛዝ ደግሞ ጦቢያ ከምትባል አገርና ከጦቢያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር ምንም ግንኙነት እንዳይኖርህ፣ ካማራ ጋር እንዳትጋባ፣ ከተጋባህም ተፋታ ነው፡፡  መለስ ዜናዊ አድዋ የዘመተው ልሙጥ ባንዲራ አይወክለኝም ብሎ ምናምንቴ ጨመረበት፡፡  ጭራቅ አሕመድ ደግሞ በጀግንነቱ የሚተማመነው ጥቁር አንበሳ የሚወክለው የአማራን ትምክሕተኝነት ነው በማለት፣ በውበቷ የምትኩራራውን ጣወስን (peacock) ዓርማው አደረገ፡፡  

ስለዚህም ያንዱ መዳብ የሌላው ወርቅ ነውና (One’s trash is another’s treasure) የትግሬና የኦሮሞ ጽንፈኞች አምርረው የሚጠሏቸውን፣ የአማራ ሕዝብ ግን ከራሱ በላይ የሚወዳቸውን ኢትዮጵያ (ጦቢያ) የሚለውን ስም፣ ልሙጡን ባንዲራ እና ጥቁር አንበሳን የአማራ ሕዝብ የራሱ የግሉ ብቻ የማድረግ ትልቅ ዕድል ተፈጥሮለታል ማለት ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ ደግሞ ይህን መቸም የማይገኝ ትልቅ ዕድል በደንብ መጠቀም አለበት፡፡  

የመላው ጥቁር ሕዝበ መመኪያ የሆኑት ጦቢያ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ እና ጥቁር አንበሳ የአማራ ሕዝብ መለያ ናቸው ብለው ለአማራ ሕዝብ ብቻ በመስጠታቸው፣ የአማራ ሕዝብ የኦሮሞና የወያኔ ጽንፈኞችን ዝንታለም ሊያመሰግናቸው ይገባል፡፡             

ሁለተኛ ትልቅ ዕድል፤ የአማራን ሕዝብ ዐጽመ ርስት ሁሉንም የምታጠቃልል፣ አማራነት የገነነባትን አዲሲቷን አማራዊት ጦቢያ መመሥረት

ሕዝብ ማለት በቀደዱለት ቦይ የሚፈስ ውሃ ማለት ነው፡፡  የኦሮሞና የትግሬ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ ባይጠላም፣ የኦሮሞና የትግሬ ልሂቃን ግን በአማራ ጥላቻ ተመርዘው በጠና የታመሙ በሽተኞች ናቸው፡፡  የአማራ ጥላቻ በሽታቸውን ደግሞ በሕዝባቸው ላይ እንደ ወረርሽኝ አዛምተውበታል፡፡

የወያኔና የኦነግ ልሂቃን እንወክለዋለን በሚሉት የትግሬና የኦሮሞ ሕዝብ ላይ (በተለይም ደግሞ በወጣቱ ትውልድ ላይ) የነዙበት የአማራ ጥላቻ እየከረረ የሚሄድ እንጅ መቸም ሊወገድ የማይችል ጥላቻ ነው፡፡  ሊወደግ የማይችልበት ምክኒያት ደግሞ ጥላቻው በእንቶ ፈንቶ ታሪክ ላይ የተመሠረተ፣ አውነተኛ ምክኒያተ የሌለው ምክኒያትአልባ ጥላቻ ስለሆነ ነው፡፡    

የወያኔና የኦነግ ጽንፈኞች የአማራን ሕዝብ የሚጠሉት በድርጊቱ ሳይሆን በማንነቱ (በባሕሉ፣ በትውፊቶቹና በቋንቋው) ነው፡፡  ባላደረከው ነገር የምትጠላ ከሆነ ደግሞ ምንም ማድረግ አትችልም፡፡  ማድረግ የምትችለው በማንነትህ የሚጠላህ ቡድን ማንነትህን እንዳያጠፋ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ብቻ ነው፡፡   

ስለዚህም የአማራ ሕዝብ፣ ባማራ ጥላቻ ከተመረዘው ከኦሮሞና ከትግሬ ሕዝብ ጋር ባንድ አገር ውስጥ በመከባበርና በመተባበር እኖራለሁ የሚለውን እንቶ ፈንቶ እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ በሉባ ተስፋፊ የተነጠቃቸው ግዛቶች አንዳቸውም ሳይቀሩ ሁሉም የሚጠቃለሉበትና በቀድሞ ስማቸው የሚጠሩበት ካርታ ሰርቶ፣ ስሟ ጦቢያ፣ ባንዲራዋ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ፣ አርማዋ ጥቁር አንበሳ የሆነ የራሱ የአማራ አገር የሆነች፣ አማራነት የገነነባት፣ አማራዊት ጦቢያን ለመመሥረት ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡  

ቀጥሎ ደግሞ ርስት በሺ ዓመቱ ለባለቤቱ ነውና፣ በሉባ ተስፋፊወች የተነጠቃቸውን (ባዲሱቱ አማራዊት ጦቢያ  ካርታ ውስጥ ያጠቃለላቸውን) ያባቶቹ አጽመ ርስቶች፣ አንዳቸውም ሳይቀሩ ሁሉንም የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅም በውድም በግድም ወደ አማራዊት ጦቢያ እንደሚያስመልሳቸው በይፋ የሚገልጽበት ልፈፋ አማራ (Amhara manifesto) ማውጣት አለበት፡፡   

በልፈፋው ላይ ደግሞ በደማቸው አማራ ሁነው ሳለ አማራዊ ማንነታቸውን እንዲያጡ የተደረጉትን እልፍ አእላፍ ጦቢያውያን፣ አማራነታቸውን አውቀው ወደ ቀድሞ እውነተኛ ማንነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንደሚመለሱ ለማድረግ አጥብቆ እንደሚሠራ መግለጽ አለበት፡፡  

በጦቢያ ምድር ላይ ከጣና እስከ ጫሞ 

በኦሮምኛ ቃል ያለ ተሰይሞ

ከመስፋፋት በፊት ሁሉም አስቀድሞ

አይደለም ኦሮሞ ወይም የኦሮሞ፡፡

በስሙ ኦሮሞ ከሆነው ሕዝብ ላይ

ዘጠና በመቶ ወይም ከዚያ በላይ

በደሙ ያይደለ ብሔሩን የረሳ

ወይ ጉዲፈቻ ነው አለያም ሞጋሳ፡፡

ሦስተኛ ትልቅ ዕድል፤  አማረኛ በአማራዊት ጦቢያ ውስጥ እንግሊዘኛን ሙሉ በሙሉ እንዲተካና ካፍሪቃ ውል ቋንቋወች ውስጥ አንዱና ዋናው እንዲሆን ማድረግ

የወያኔና የኦነግ ጽንፈኞች የአማራን ሕዝብ አምርረው የሚጠሉበት አንዱና ዋናው ምክኒያት የአማረኛ ቋንቋ ነው፡፡  በነዚህ ጽንፈኞች ጠንጋራ አመለካከት፣ አማረኛ የቅኝ ገዥ ቋንቋ ሲሆን፣ እንግሊዘኛ ግን የነጻ አውጭ ቋንቋ ነው፡፡  ስለዚህም የአማራ ሕዝብ በሚፈጥራት ባዲሲቱ አማራዊት ጦቢያ ውስጥ፣ ኦሮሞ ወይም ትግሬ ይቀየማል ብሎ ሳይሰጋ ወይም ደግሞ ይሉኝታ ሳይሰማው እንግሊዘኛን ሙሉ በሙሉ ባማረኛ ሊተካ ይችላል፣ መተካትም አለበት፡፡  ልጆቹን ደግሞ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ሙሉ በሙሉ ባማረኛ በማስተማር፣ እንደ ጃፓንና ኮርያ አገሩን በፍጥነት የሚያሳድግ ትውልድ በፍጥነት መፍጠር ይችላል፡፡ 

በደርግ ዘመን የአማረኛ ትምህርት ከዩኒቨርስቲ እንዲወገድ ያደረጉት አማራ ጠሎቹ የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን ነበሩ፡፡  ለምሳሌ ያህል በ1976 ዓ.ም የፍልስፍና ትምህርት ባዲሳባ ዩኒቨርሲቲ ባማረኛ ተሰጥቶ አመርቂ ውጤት ቢያስገኝም፣ አማራ ጠሎቹ የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን ግን ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳት ትምህርቱ ባማረኛ መሰጠቱ እንዲቀር አድርገዋል፡፡  

ዐረብኛን ከተለያዩ ቋንቋወች ጋር በማዳቀል ትናንት የተፈጠረው፣ የላቲን ፊደል የሚጠቀመው መናኛው የስዋሂሊ ቋንቋ የምሥራቅ አፍሪቃ ወል ቋንቋ (lingua franca) ለመሆን ሲበቃ፣ አፍሪቃዊ ፊደል ያለው ታላቁ የአማርኛ ቋንቋ ግን ድንበር ሊሻገር ያልቻለው፣ የጦቢያን ቢሮክራሲ ባብዛኛው የተቆጣጠሩት፣ አማረኛን እጅግ አምርረው የሚጠሉት የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን አንቀው ስለያዙት ብቻና ብቻ ነው፡፡ 

የአማራ ሕዝብ በሚመሠርታት፣ አማራነት በገነነባት ባዲሲቷ አማራዊት ጦቢያ ውስጥ ግን የአማረኛ እጣ የሚወሰነው በራሱ በአማራ ሕዝብ እንጅ ፀራማራ በሆኑት በትግሬና በኦሮሞ ጽንፈኞች አይደለም፡፡  የአማራ ሕዝብ ደግሞ የሱ የራሱ የሆነ፣ እንዳበጁት የሚበጅ ምርጥ ቋንቋ እያለለት፣ ፈረንሳይ ሲነግስ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝ ሲነግስ እንግሊዘኛ፣ ቻይና ሲነግስ ቻይንኛ እየተጠቀመ የባዕድ ቋንቋ እንደ ሸሚዝ የሚለዋውጥበት ምንም ምክኒያት የለውም፡፡  

እንግሊዘኛ ደግሞ እንግሊዞች በቅኝ ወረራ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እንዲሆን ያደረጉት፣  ውስጡ ለቄስ የሆነ፣ በግድ እንጅ በውድ ሊመረጥ የማይችል ቅጥ ያጣ ቋንቋ ነው፡፡  በተለይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ለሰገል (science) እና ኪንሲን (technology) ሊያገለግል የቻለው አመቺ ሁኖ ሳይሆን በዓለም ልሂቃን ያላሰለሰ ድካም ነው፡፡  ስለዚህም የአሜሪቃ ኃያልነት ሲያከትም፣ የእንግሊዘኛም ዓለም አቀፍ ቋንቋነት እንደሚያከትም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል እንግሊዞኝ የዩክሬኑ የዜሌንስኪ ቀንደኛ ደጋፊወች የሆኑት፣ ለዩክሬን ሕዝብ አስበው ሳይሆን፣ ራሺያ ድል አድርጋ የምዕራባውያንን የበላይነት ላንዴና ለመጨረሻ ከሰበረች፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የመጨረሻው መጀመርያ (the begining of the end) መሆኑን ስለሚያውቁ ነው፡፡   

የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን እንግሊዘኛን አመለኩ አላመለኩ፣ የአማራን ሕዝብ የማይመለከት የነሱ የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ ግን እንግሊዘኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እስከሆነ ድረስ በእንግሊዘኛነቱ ብቻ እያጠና፣ እንዳበጁት የሚበጀውን የአማረኛ ቋንቋውን ግን ከእንግሊዘኛ በሚበልጥ ውበት ለሰገል (science) እና ኪንሲን (technology) እንዲያገለግል በቀላሉ ማድረግ ይቻላል፡፡  ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው ደግሞ በአማረኛ የሰዋሰው ደንቦች መሠረት አስፈላጊወቹን አዳዲስ ቃሎች መፍጠር ብቻና ብቻ ነው፡፡  ለዚህ ደግሞ ግእዝን የሚያህል ተቀድቶ የማያልቅ የቃላት ምንጭ አለው፡፡  

ማጠቃለያ 

ባጠቃላይ ለመናገር ጭራቅ አሕመድ የአማራን ሕልውና ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል፡፡  የአማራ ሕዝብ ደግሞ ቀበቶውን አጥብቆ፣ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ፈተናውን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ካለፈው፣ የጭራቅ አሕመድን ሕልም አብንኖ፣ የራሱን ራዕይ አውኖ፣  በወያኔና በኦነግ መቃብር ላይ አማራ ባማራነቱ የሚገንባትን አማራዊት ጦቢያን ይገነባል፡፡  አድዋ የዘመተው ባንዲራና፣ ባርበኝነት ዘመን ጣልያንን የተዋጋው ጥቁር አንበሳ ደግሞ ወደ ቀድሞ ክብራቸው ይመለሳሉ፡፡  አማረኛም የሚገባ ደረጃውን በማግኘት ካማራዊት ጦቢያ አልፎ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ብሎም የመላው አፍሪቃ ወል ቋንቋ (lingua franca) ይሆናል፡፡  

  መስፍን አረጋ ⇓

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic