>

እውን የአማራ ሕዝብ ባርነት የሚወድ ሕዝብ ነው? (መስፍን አረጋ)

እውን የአማራ ሕዝብ ባርነት የሚወድ ሕዝብ ነው?

መስፍን አረጋ

ፍራብ (ፍሬ ሐሳብ፣ abstract)

ጦቢያ ውስጥ ሁሉም ለውጦች የተከሰቱት የአማራ ሕዝብ ከሞላ ጎደል ብቻውን በከፈላቸው ከፍተኛ መስዋዕትነቶች ነው፡፡  በከሸፈው የመንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ግልበጣ ጊዜ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ያለቁት ያማራ ወጣት መኮንኖችና ልሂቆች ነበሩ፡፡  ኃይለ ሥላሴን የጣለው ባብዛኛው የአማራ ሕዝብ ነበር፡፡  ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ደርግ በመካከላቸው ባደረጉት የስልጣን ትንቅን ወቅት ባብዛኛው ያለቀው ያማራ ወጣት ነበር፡፡  ወያኔ አዲሳባ የገባቸው የብአዴን ወጣቶችን እየጋለበች ነበር፡፡  ለወያኔ መውደቅ ወሳኙን ሚና የተጫወተው ደግሞ አሁንም የአማራ ወጣት ነበር፡፡

ስለዚህም የአማራን ሕዝብ ታግሎ መጣል የማይችል፣ ባርነትን የሚወድ ሕዝብ ነው ማለት ፍጹም ስሕተት ነው፡፡  ባለመታደል ግን የአማራ ሕዝብ በደሙ ያፈራቸው ሁሉም “የለውጥ ፍሬወች” የአማራን ሕዝብ ውለታ ወዲያውኑ ረስተው ዐመድ አፋሽ በማድረግ፣ ቁም ስቅሉን የሚያሳዩት ራሱን የአማራን ሕዝብ ነው፡፡  ለዚህ ደግሞ ሁለት መሠረታዊ ምክኒያቶች አሉ፡፡  አንደኛው ምክኒያት የአማራ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን የሚያደርገው ለውጥን በማስከሰት በቅድመ ለውጥ ላይ እንጅ የለውጡ ፍሬ ምንና ማን ይሁን በሚለው በድኅረ ለውጥ ላይ አለመሆኑ ነው፡፡  ሁለተኛው ምክኒያት ደግሞ የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላቱን ለይቶ አውቆ በዚሁ በዋና ጠላቱ ላይ ዋና ትኩረቱን አለማድረጉ ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል ደርግ የአማራ ጨቋኝ ቢሆንም፣ ወያኔ ግን የአማራ የሕልውና ጠላት በመሆኑ፣ የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላቱ ወያኔ መሆኑን አውቆ፣ ለወያኔ መንገድ ከፍቶ አዲሳባ ከማስገባት ይልቅ ከደርግ ጋር ተባብሮ ወያኔን ማጥፋት ነበረበት፡፡  አሁን ላይ ደግሞ ወያኔና ኦነግ አማራን የሚጨፈጭፉት ጭራቅ አሕመድ ስላመቻቸላቸው ብቻ ስለሆነ፣  ጭራቅ አሕመድን ጨርቅ ካደረገ ወያኔና ኦነግ እዳቸው ገብስ መሆኑን አውቆ፣ የአማራ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን ጭራቅ አሕመድን በማስወገድ ላይ ማድረግ አለበት፡፡  

ለአማራ ሕዝብ ነጻነት በሚያደርጉት ከፍተኛ ተጋድሎ እጅጉን የማከብራቸው ጀነራል ተፈራ ማሞ “የአማራ ሕዝብ ታግሎ መጣል፣ ታግሎ መቀየር፣ ታግሎ ማሻሻል የሚችል ሕዝብ አይደለም ::  የአማራ ሕዝብ ባርያ ሆኖ መኖር የሚችል ነው” ብለዋል ተብሎ ተዘግቧል፡፡  ጀነራሉ \አሉ\ የተባሉትን በእውነትም ብለው ከሆነ ሊሉ የበቁት፣ ትልቁ የአማራ ሕዝብ በኢምንቶቹ በወያኔና በኦነግ እንዴት ይሸነፋል ከሚል ብስጭት እንደሆነ ይገባኛል፡፡  በተለይም ደግሞ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ለአማራ ሕዝብ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን የአማራ ሕዝብ በሚገባ የተረዳው ስላልመሰላቸው፣ ጭንቀታቸውን ባጽንኦት በመግለጽ የአማራ ሕዝብ በሂወቱ ቆርጦ በነቂስ እንዲነሳሳ ለመቀስቀስ ሲሉ እንደሆነ ይገባኛል፡፡  እንዲህም ሆኖ ግን፣ ጀነራል ተፈራ ማሞ ብስጭታቸውን ለመወጣትና ጭንቀታቸውን ለመግለጽ ሲሉ እንደዋዛ የተናገሩት ንግግር ፍጹም የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ ለወያኔና ለኦነግ ጥይቅ ከማቀበል እንደሚቆጠር ሳልጠቁም ማለፍ አልፈልግም፡፡  የዚህ ጦማር ዓላማም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡  

ሕዝብን በጥቅል በመፈረጅ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ማለት ትክክል ባይሆንም፣ አንበል ከተባለ ግን ባርነትን የሚወዱት የትግሬና የኦሮሞ ሕዝቦች እንጅ የአማራ ሕዝብ አይደለም፡፡  ትግሬወችና ኦሮሞወች ባርነትን እንደሚወዱና የፈረንጅ ባርያ ከመሆን ያገዷቸው የአማራ ገዥወች እንደነበሩ ራሳቸው ፈረንጆቹ መስክረውላቸዋል፡፡  ከነዚህም የፈረንጅ መስካሪወች ውስጥ አንዱና ዋናው፣ ሁለተኛው የጣልያን ወረራ ከመጀመሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጦቢያ የተባረረው ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) የሚባለው ነምሳዊው (Austro-Hungarian Empire) የናዚ ባላባት (baron) ነበር፡፡  የመሰከረላቸው ደግሞ ጥቁሩ አደጋ (die Schwarze Gefahr) በሚል ርዕስ በጀርመንኛ በጻፈው፣ አደገኛዋ ጥቁር ጦቢያ (Abissinia pericolo nero) በሚል ርዕስ በጣልያንኛ በተተረጎመው፣ የኛው ደበበ ሰይፉ ደግሞ ጦቢያ፣ የበርሜል ባሩድ (Abissinia: The Powder Barrel) በሚል ርዕስ ከእንግሊዘኛ ወደ አማረኛ በመለሰው መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡

የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን ለነጭ የሚሽቆጠቆጡ የነጭ ቅጥቅጦች መሆናቸውን የሚጠራጠር ካለ የፕሮቻዝካን መጽሐፍ ገዝቶ ያንብብ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ መለስ ዜናዊ ከጅሚ ካርተር ጋር የነበረውን፣ ጭራቅ አሕመድ ደግሞ ከጆ ባይደን ጋር ያለውን የጌታ-ሎሌ ግንኙነት ይመርምር፡፡  ለማጠናከሪያ ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአማራ ሕዝብ በመለስ ዜናዊ ዘመን በቀጥታና በተዛዋሪ ሲጨፈጨፍ፣ ባስር ሺ የሚቆጠሩ አማሮች በጭራቅ አሕመድ ዘመን ሲታረዱ፣ ድምጻቸው ያልተሰማው ጥቁርጠል ነጭ ላዕልተኞች (white supremacists)፣ የትግሬ ሴቶች ባማራ ወንዶች ተደፈሩ፣ ኦሮሞወች ባማሮች ተጨቆኑ እያሉ የአማራን ሕዝብ ዘወትር የሚወቅሱበትንና የሚከሱበትን ምክኒያት ራሱን ይጠይቅ፡፡    

የአማራ መኳንንት እንደ ትግሬው ኃይለሥላሴ ጉግሳ ወይም እንደ ኦሮሞው ጅማ አባጅፋር ባርነትን የሚወዱ ቢሆኑ ኖሮ፣ ጣልያንን ለመፋለም ጫካ ገብተው፣ ራሳቸውን ለስቅላት፣ ሕዝባቸውን ደግሞ ለቦንብ ድብደባና ለመርዥ ጭስ ልብለባ ባልዳረጉት ነበር፡፡  ለዚህ ደግሞ የሸንቁጥ ልጆችን  ያርበኝነት ትግልና ጣልያን በመንዝ ሕዝብ ላይ ያዘነበውን የቦንብ ዶፍ ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡  

እራሳቸው ጀነራል ተፈራ ማሞ መመስከር እንደሚችሉት፣ ወያኔን አዲሳባ ያስገባት የትግሬ ሕዝብ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ነበር፡፡  የአማራ ሕዝብ በደርግ ላይ ተስፋ ቆርጦ፣ የባሰ አይመጣም በማለት ወያኔን ነጻ ባይለቃት ኖሮ፣ በአማራ ግዛት ላይ ተረማምዳ አዲሳባ መግባት ቀርቶ የአማራን ድንበር መርገጥ ባልቻለች ነበር፡፡  እራሳቸው ጀነራል ተፈራ ማሞ አባል የነበሩበትን ብአዴንን የመሠረተችውም እንደ ስሙ የአማራን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለማገዝ ሳይሆን በአማራ ምድር ላይ ለመረማመድ የምትችለው እሱንና እሱን ብቻ እየጋለበች መሆኑን ስለምታውቅ ነበር፡፡   

አማራዊ ሳይሆን አማራዊ ነው ይባል የነበረው ደርግ፣ ከአማራ ሕዝብ ጋር ተጣልቶ የአማራ ሕዝብ ፊቱን ባያዞርበት ኖሮ፣ ሻቢያ፣ ወያኔና ኦነግ በተናጠል ቀርቶ ባንድነትም ሁነው ሊገረስሱት ቀርቶ ሊነቀንቁት ባልቻሉ ነበር፡፡  በውሸት ለውሸት የተፈጠረው ውሸታሙ ወያኔ ተራራን አንቀጠቀጥኩ እያለ የሚቦፍፈው፣ የአማራ ሕዝብ ገዝግዞ የጣለውን ደርግ ይባል የነበረውን ግንድ፣ ብአዴን የሚባለውን አሽከሩን በማሰማራት ስለቆራረጠውና ስለፈላለጠው ብቻ ነው፡፡  

ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፣ ምንትሴን የገረሰሰ ምንትሴ እያሉ ቱልቱላ መንፋት ውሸትነቱ ቢያስጸይፍም ዋና ዓላማው ግን በዝቅተኝነት ስሜት ተጸንሶ፣ ደቁኖ የቀሰሰውን የወያኔን በራስ መተማመን መገንባት ስለሆነ፣ የወያኔ ሙሉ መብት ነው፡፡  በዚህ የቱልቱላ የሚተለተለው ግን በራስ መተማመኑን በውሸት ላይ በመገንባት ማንነቱን በድቡሽት ላይ ያነጸው ራሱ ወያኔ ነው፡፡  ባህያ ቁርበት የተሠራ ቤት ይንኮታኮታል ጅብ የጮኸለት፡፡

ባህያ ቁርበት የተሠራውን የወያኔን ቤት ያንኮታኮተው ደግሞ የአማራ ወጣት እንጅ ልክ እንደ ወያኔ በውሸት ለውሸት የሚኖሩት ወሸታሞቹ ኦነጋውያን እንደሚሉት ቄሮ አልነበረም፡፡  ወያኔ የመውደቂያ ቀኗን ሀ ብላ መቁጠር የጀመረችው የአማራ ወጣት የኦሮሞ ደም ደሜ ነው ብሎ ከተነሳበት ዕለት ጀምሮ ነው፡፡  ከዚያ በፊት ግን የቄሮ መፈራገጥ ለመላላጥ መሆኑን ወያኔ ታውቅ ስለነበር፣ ከቁም ነገር አትቆጥረውም ነበር፡፡

ወያኔ አጥብቃ ትፈራ የነበረው የአማራን ሕዝብ እንጅ በኦሮሞ ሕዝብ በኩል ምንም ስጋት አልነበረባትም፡፡  ለዚህ ደግሞ የወያኔው ጦር መሪ ሰየ አብርሃ ኦነግን ከሳንቲም አንቆጥረውም ሲል የተናገረው በቂ ምስክር ነው፡፡  የብአዴኑን ሙሉ ዓለምን የመሰለ የብአዴን ሰው አማራን የሚደግፍ ትንሽ ነገር ከተናገረ ሳትውል ሳታድር የምታጠፋው፣ የኦፒዲኦውን አባዱላን የመሰለ የኦፒዲኦ ሰው ግን ያሻውን ቢናገር ሰምታ እንዳልሰማች የምታልፈው በዚሁ ምክኒያት ነበር፡፡  ቄሮ የፈለገውን ያህል ቢፈነጭም፣ በባሩድ ጭስ ብቻ አስደንብራ ገደል እንደምታስገባው ወያኔ ታውቅ ስለነበር፣ የቄሮ ጉዳይ እጅግ አያሳስባትም ነበር፡፡  ለዚህ ደግሞ የደብረዘይቱን የኢረቻ ክስተት መጥቀስ ይበቃል፡፡

የአማራ ወጣቶች ሲነሱባት ግን ወያኔ እጅግ ስለምትደነግጥ የምትሆነውን ያሳጣት ነበር፡፡  ባንድ ቀን ብቻ አመሳ (50) የአማራ ወጣቶችን ባሕርዳር ላይ የጨፈጨፈችውም በዚሁ ምክኒያት ነበር፡፡  ከ1997 ምርጫ በኋላ አዲሳባ ላይ የጨፈጨፈቻቸው በመቶ፣ ምናልባትም በሺ የሚቆጠሩ ሰማዕታትም አብዛኞቹ የአማራ ወጣቶች ነበሩ፣ ያዲሳባ ሕዝብ አብዛኛው አማራ ነውና፡፡

በተጨማሪ ደግሞ በወያኔ ጊዜ ቄሮ ሰልፍ ይወጣ የነበረው፣ በራሱ ተነሳሽነት ሳይሆን የጊዜው የኦፒዲኦ (OPDO) ባለስልጣኖች በተለይም ደግሞ አባዱላና ደቀመዝሙሮቹ (ለማ መገርሳ፣ ጭራቅ አሕመድ ወዘተ.) ውስጥ ለውስጥ እየቆሰቆሱት እንደነበር ወያኔ ታውቅ ነበር፡፡ የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ ኦፒዲኦ ቢገልጡት ኦነግ ነው ያለበትም አንዱ ምክኒያት ይሄው ነበር፡፡  በራሱ ተነሳሽነት ሳይሆን በሌላ ግፊት የሚወጣ ሰልፈኛ ደግሞ፣ ምንም እንደማይተክርና እንደ ጠዋት ጤዛ ትንሽ ጮራ ሲነካው በንኖ እንደሚጠፋ ከወያኔ የተሰወረ አልነበረም፡፡  

አባዱላና ደቀመዝሙሮቹ ቄሮን ሰልፍ ያስወጡት የነበረው ውሎ አበል እየከፈሉት ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም፡፡  ወያኔ ከወደቀ በኋላ፣ ቄሮ ገንዘብ ካልተከፈልኩ አልወጣም በማለት አያሌ የድጋፍ ሰልፎችን ያስተጓጎለው የለመደው ስለቀረበት መሆን አለበት፡፡  

በተጨማሪ ደግሞ ቄሮ ገንዘብ እየተከፈለውም ቢሆን ሰልፍ ይወጣ የነበረው፣ ወያኔ (በንቀቱ ምክኒያት) እንደማይጨክንበትና ግፋ ቢል ወደ ሰማይ እንጅ ወደሱ እንደማይተኩስበት ስለሚያውቅ ነበር፡፡  በወያኔ ዘመን በተደረገ በማናቸውም የቄሮ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ወይም በጥይት ጩኸት በሚደነብር ሰልፈኛ ተረጋግጦ ከሞተ ጥቂት ቄሮ ውጭ፣ እንደ ወልድያ ሕፃናት ግንባሩን በወያኔ ጥይት ተበርቅሶ የሞተ አንድም ቄሮ አልነበረም፡፡

ስለዚህም፣ ቄሮን ወያኔን የገለበጠ ጀግና አስመስሎ መሳል፣ የነ አባዱላ ፖለቲካዊ ቁማር አንዱና ዋናው ዘርፍ እንጅ ቅንጣት እውነታ የለውም፡፡  ወያኔን ለመጣል ቄሮ የነበረው ሚና አልቦ በሚያስብል ደረጃ ኢምንት ነበር፡፡  እንዲህም ሆኖ ግን ትርክት መፍጠር እንችላለን በማለት የተመጻደቁት እነ ጭራቅ አሕመድ፣  እንቁራሪቱን ቄሮ እጅግ አግዝፈው ዝሆን አሳከሉት፡፡  

በሌላ በኩል ግን የአማራ ወጣት ወያኔን በመቃወም ሰልፍ ይወጣ የነበረው፣ አማራን እንወክላለን የሚሉት በረከት ስምዖንና ደቀመዝሙሮቹ በጥይት እሩምታ ያለርህራሄ እንደሚረፈርፉት በደንብ እያወቀ የእሳት ራት ለመሆን ቆርጦ ነበር፡፡  ስለዚህም፣ በትክክል እንናገር ከተባለ እንደ አማራ ወጣት ጀግና የሆነ ወጣት በጦቢያ ውስጥ የለም ወይም ደግሞ አልታየም፡፡    

ስለዚህም መሠረታዊው ጥያቄ፣ የአማራ ወጣት ወደር የሌለው ጀግና ሁኖ ሳለ፣ የሚከፍላቸው የጀግንነት መሥዋእቶች ግን አንዳቸውም መልካም ፍሬ ሳያፈሩ ውሃ በልቷቸው የሚቀሩበት ምክኒያት ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡  ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ ሁለት መሠረታዊ መልሶችን መስጠት ይቻላል፡፡  

የመጀመርያው መልስ ነብታሚ (ፕሮፌሰር) መስፍን ወልደማርያም ባንድ ወቅት በሰፊው እንዳብራሩት የአማራ ሕዝብ ሙሉ ትኩረቱን የሚያደርገው ታግሎ በመንቀል ላይ እንጅ፣ ታግሎ በመንቀልና በመትከል ላይ አለመሆኑ ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ መንቀል የሚፈልገውን ሁሉ በነቂስ ወጥቶ፣ የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ከፍሎ ከነቀለ በኋላ፣ በተነቀለው ቦታ ስለሚተከለው ተተኪ ግን ጉዳይ ሳይሰጠው፣ ጣጣውን የጨረሰ ይመስል፣ ነገር ዓለሙን ረስቶት፣ ቤቱ ገብቶ፣ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል፡፡  የአማራ ሕዝብ ኃይለሥላሴን ነቅሎ ቤቱ ሲገባ፣ ብልጣብልጡ ደርግ ተተከለ፣ ደርግን ነቅሎ ቤቱ ሲገባ ብልጣብልጡ ወያኔ ተተከለ፣ ወያኔን ነቅሎ ቤቱ ሲገባ ደግሞ ብልጣብልጡ ኦነግ ተተከለ፡፡

ስለዚህም የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚከፍልበት እኩይን የመንቀል መራራ ትግል መልካም ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው፣ በሚነቀለው እኩይ ምትክ የሚተከለውን ሰናይ በጥሞና አስቦበት አስቀድሞ ካዘጋጀው ብቻ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡  አለበለዚያ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ይሆንና ግርግር ይፈጠራል፡፡  ግርግር የሚጠቅመው ደግሞ በትግሉ ወቅት ከዳር ቁመው ለሚታዘቡ ሌቦች ነው፡፡  ደርግ፣ ወያኔና ኦነግ የአማራን ሕዝብ ትግል ሰርቀው ስልጣን የያዙ የትግል ሌቦች ናቸው፡፡ 

የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋእትነተት ከፍሎ ቅራቅር ላይ ወያኔን ድባቅ ከመታ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ባሕርዳር አዙሮ የወያኔን ሎሌ ብአዴንን ድራሹን ማጥፋት ነበረበት፡፡  የአማራ ሕዝብ ኮበሌወቹን ለረሻኝ፣ ልጃገረዶቹን ለቡድን ደፋሪ ገብሮ ወያኔን ከደብረብርሃን ከመለሰ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ዐራት ኪሎ አዙሮ፣ ወያኔ ደብረብርሃን እንድትደርስ ያበቃትን ጭራቅ አሕመድን ማንቁርቱን ይዞ፣ እጅ እግሩን ጠፍንጎ፣ መስቀል አደባባይ ላይ ዘቅዝቆ መስቀል ነበረበት፡፡

የአማራ ሕዝብ መራራ ትግል ለምን ፍሬ አያፈራም ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ሁለተኛው መልስ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላቱን ለይቶ አውቆ በዚሁ በዋና ጠላቱ ላይ ዋና ትኩረቱን አለማድረጉ ነው፡፡  በተለይም ደግሞ ይህ መልስ ይበልጥ አግባብነት የሚኖረው ባሁኑ በጭራቅ አሕመድ ኦነጋዊ ዘመን ነው፡፡  

ጭራቅ አሕመድ ለአማራ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን፣ የሕልውና ጠላት መሆኑን ባምስት ዓመት የስልጣን ዘመኑ በግልጽ አስመስክሯል፡፡  የአማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላት ስለሆነ ደግሞ የአማራ ሕዝብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ዶክተር፣ እሳቸው፣ እርስወ እያለ በክብር ሊጠራው አይገባም፣ በክብር የምትጠራውን በጽኑ አትታገለውምና፡፡  የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላቱን ጭራቅ አሕመድን በጽኑ ታግሎ ጨርቅ ካደረገ፣ ወያኔና ኦነግ እዳቸው ገብስ ነው፡፡ 

Email:  mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic