>

ከስሜታዊና ከሆይሆታ  “ትግል” እንውጣ!!! (ፊልጶስ)

ከስሜታዊና ከሆይሆታ  “ትግል” እንውጣ!!!

ፊልጶስ

እየተከፈለ ያለውና የሚከፈለው መሰዋአትነት የሕይወት ነው።  ያውም ካልተወለደ ፅንስ እስከ ሽማግሌ። ከምድረ ገፅ እድንጠፋ የሚፈልጉት ደግሞ ከውስጥ የተደራጁና የታጠቁ ከሰበአዊነት ውጭ የሆኑ መንግሥታዊ መምበሩን የሚዘውሩ  በጎሰኝነትና በበታችነት ያበዱ ናቸው።  እነዚህ ደግሞ በዓለማችን አሉ በሚባሉ አገሮች ይደገፋሉ፣ ይታጠቃሉ፣ ይመከራሉ፤ እለንላችሁ ይባላሉ።

 በአጠቃላይ ውጫዊና ውስጣዊ ድጋፍ ያላቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን አድደው መሞቅ የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆኑ እያደረጉም ያሉ እኩይ ፍጥረቶች  “የእፍኝት ልጆች“” ናቸው።

ታዲያ ለዚህ ዓይነቱ  የህልውና ጥያቄ የሚመጥን  የተደራጀ፣ ፅናት፣ መርሕና ዕራየ ያለው ሁለገብ ትግል ማድረግ እንጅ፤ ሆን ተብሎ ገዥዎቻችን አጀንዳ በሰጡን ቁጥር በስሜትና በሆይሆታ  የምናደርገው መስዋእትነት እስከ አሁንም ከዕልቂትና ርስበርስ ከመቆራቆስ ውጭ ያተረፍነው ነገር የለም። ፈረሳዮች “ መሳሳት ያለ ነገር ነው፤ ከስህተት  ያለ መማር ግን ‘ጌኛነት’ ነው።” ይላሉ። 

ስለዚህም  በወሬ ሳይሆን በተግባር ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚታገሉት በሚደርስባቸው እስራት ሆነ ግድያ ሳንዘናጋቸውና ለቤተስቦቻቸውም ጋሻና መከታ በመሆን፣ ብሎም ዋናው ትግል ላይ አንድነታችን አስከብረን፤ ከመንደርተኝነትና ከጎሰኝነት ነፃ የሆነች፤ ሁላችንም  በእኩልነትና በነፃነት  የምታስከብር ሃገር እንድትኖረን ከሚያሻው ትግል ላይ  ማተኮር ይጠብቅብናል። ድሮም  ታጋይና የህዝብ ልጅ ይታሰራል። ይገደላል። ቁምነገር ግን መሰዋአትነታቸው ለፍሬ እንዲበቃ፤ የትግሉ ቀጣይነትና በፅናት ከግብ  ማድረሱ ላይ ነው። 

እንደ ምሳሌ  በስንት መስዋአትነት  የተያዙትን የወያኔ አድራጊ ፈጣሪዎችን እነ ስብሃት ነጋን የፈታ መንግሥት በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትንና የብዕር ዓርበኞችን  የማሰር ሞራል ሊኖር ባልተገባ ነበር።  ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የሚታገሉትን ለማጥፋትና ለማሰር የዘመተውን ያህል፤ የሰውን ልጅ በማንነቱ ብቻ እንደ እንሰሳ የሚያርዱቱን የዳቦ ስም በሰጣቸው በኦነጋዊሸኔ ላይ ግን እጁን አያነሳም።  

በዚች ሰዓት ዜጎች ከወያኔ ጋር በሚተነቁበት ወቅት በመሃል ሃገር በየምክንያቱ የሚያስረውና የሚያሳድደው የትግሉን አቅጣጫ ለማዘናጋትና ነገከነገ ወዲያ እንደ ተለመደውከወያኔ ጋር ለሰላም ስል ተኩስ አቁም አድርጊያለሁ።ቢል፤ ለምን ብሎ  የሚጠይቅና የሚገዳደረው ኃይል እንዳይኖር መሆኑን መገንዘብ አለብን። 

የስሜትና የሆሆታ ትግል ማለት የጀበና ቡና ማለት ነው። ጀበናው እሳቱ ሲጠፋ መፍላቱን ያቆምን ሌላ እሳት ካላገኘ ይሰክናል። የስሜትና የሆሆታ ትግልም እንደዚሁ ነው። ገዥዎቻችን አንድ እጀንዳ ሲሰጡን በስሜትና በሆይሆታ እንወራጫለን። ለዋናውን ትግላችን መዋል የሚገባውን ግዜ፣ እውቀትና መስዋእትነት በገዥዎች ማዘናጊያ አጀንዳ ላይ እናውለዋለን።  ግዜው ሲያልፍ ደግሞ ስንተፋተፍ አዲስ አጀንዳ ይዘጋጅልናል። 

እናም እንዘናጋ፤ ትግላችን የህልውና፣ የመኖርና ያለመኖር ብሎም አገርን የመታደግ ነው።  ይኽችን መጣጥፍ በምከትብበት ሰዓት እንኳን የስሜኑ ጦርነት አልበቃ ብሎ በኦነጋዊ ብልፅግና ክንፍ  በሸኔ፣  ወለጋ ውስጥ ዜጎችድረሱልንእያሉ እየተማፀኑ፤ ሰሚ  አጥተው  እንደተለመደው በመታረድ ላይ ናቸው። 

ስለዚህም  በዘርፈብዙው ጠላቶቻችን  ሳንበገርና በስሜትና በሆይሆይታ ሳንነዳ፣ ለረጅሙ ግባችን፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነታችን በፅናት እንታገል። ቅድም የምንሰጠውን ትግልና ፍልሚያ እንወቅ።

 የጥንት አያቶቻችንና አባቶቻችን ከሁሉም ጠላቶቻቸው ጋር ታግለው አሸንፈው እኛ ከዚህ ደርሰናል። ምን መከራው ቢበዛና ጠላትና ሆድ አደር ባንዳ  እንደ አሸን ቢፈላ፤ የግዜ ጉዳይ እንጂ ዙሮዙሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸነፊ መሆኑን የታሪክ  ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ትላንት ዛሬም ፤

—ሙቼ እየተነሳሁ፣ ልሞት እንደገና

እንድ ሞት ለአገሬ አይበቃኝምና።-++

የሚሉ ሚሊዮን  የአብራኳ ክፍይ ልጆች አሏት።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

———//———ፊልጶስ

E-mail: Philiosmw@gmail.com

Filed in: Amharic