>

አርበኛ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ያለ ህጋዊ ምክንያት የታሰሩ ሁሉም የአማራ ህዝብ ታጋዮችን ለማስፈታት ተዘጋጅተናል....!!!  (የአማራ ሕዝባዊ ኃይል - ፋኖ)

አርበኛ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ያለ ህጋዊ ምክንያት የታሰሩ ሁሉም የአማራ ህዝብ ታጋዮችን ለማስፈታት ተዘጋጅተናል….!!!

 

 የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ)

*…. በድርድር ሽፋን የታሰረው ፋኖ ዘመነ ካሴ በአስቸኳይ ይፈታ ፟ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ )

መላው የአደረጃጀታችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊወች አርበኛ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ያለ ህጋዊ ምክንያት የታሰሩ ሁሉም የአማራ ህዝብ ታጋዮችን ለማስፈታት የምናደርገዉ ትግል እንደከዚህ በፊቱ ስክነት እና ብልሃት ያልተለየው እንዲሁም የህዝባችንን አንድነት አደጋ ላይ የማይጥል እንዲሆን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንድትንቀሳቀሱ እናሳስባለን!!!

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት የወለደው አደረጃጀት ነዉ። ህዝባዊ ኃይሉ ነባሩን የፋኖነት ፍልስፍና እና ተግባር ከግዜው እና ከትግሉ ባህሪ ጋር በሚጣጣም መልኩ ለማስኬድ የተተለመ አደረጃጀት ነው::

ይህንን አደረጃጀት ስንመሰርት ታሳቢ ያደረግነውን የአማራን ህዝብ የህልውና አደጋ የመቀልበስ ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት የሚቻለው ደግሞ የነቃ እና የሰለጠነ ኃይል ሲኖር ብቻ መሆኑን ስለምናምን ከምስረታችን ጀምሮ ወጣቶችን በማሰልጠን እና በማደራጀት በኩል በርካታ ተግባራትን መፈፀም ተችሏል።

በተመሰረትን በአጭር ግዜ ውስጥም ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ህዝቡን ከጥቃት ለመከላከል ባደረግነው ጥረት በርካታ ጓዶቻችን መሪር መስዋዕትነት ከፍለዋል::

ዓላማችን በአማራ ህዝብ የህልውና ትግል ውስጥ የበኩላችንን ድርሻ ከመወጣት እና ትውልዱን የትግሉ ባለቤት ከማድረግ የዘለለ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ይፋ ከማድረጋችንም ባሻገር ከተመሰረትንበት ዓላማ ውጭ የሆነ አንዳችም ህገ-ወጥ ተግባር ባለመፈፀም ቃላችንን በተግባር አረጋግጠናል::

ይሁን እንጅ ሀቀኛ የአማራ ትግል ለጥቅማችን አደጋ ይሆናል ያሉ የመንግስት ኃይሎች እና የአማራ ህዝብ ጠላቶች ባከናወኑት የተቀናጀ ሴራ የብልፅግና መንግስት በህልውናችን ላይ ስጋት የሚደቅን ዘመቻ ከከፈተብን አራት ወራት ተቆጥረዋል::

የአማራ ህዝባዊ ኃይልን ጨምሮ ሁሉም የፋኖ አደረጃጀቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ዘመቻ እንደሚከፈት አስቀድመን በመገንዘባችን አክሳሪ ያልሆነ መውጫ መንገድ የቀየስነው ዘመቻው ከመጀመሩ ጥቂት ቀናትን አስቀድመን ነበር::

በዚህም ምክንያት የዘመቻው ዒላማ የተደረጉ የፋኖ አደረጃጀቶች በሀገሪቱ የፀጥታ መዋቅር የአመራር እርከን ቁንጮ ላይ በደረሱ ግለሰቦች የተመራውን ኦፕሬሽን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ራስን መከላከል ላይ ብቻ የተመሰረተ የትግል ስልት እንዲከተሉ ማድረግ ተችሎ ነበር።

በዚህ ምርጫችንም ወንድማማች የሆኑትን ፋኖ እና የክልሉ ልዩ ኃይል በታቀደው ልክ እንዳይጠፋፉ ማድረግ ከመቻሉም በላይ ኦፕሬሽኑ በታሰበው መጠን አውዳሚ ውጤት እንዳይኖረው ማድረግ ተችሏል።

በወሰድነው አማራጭ ህዝቡን የእርስ በእርስ ግጭት ሰለባ ከመሆን፣ ቀጠናውን ከቀውስ እና ትርምስ ነፃ ማድረግ ተችሏል። ይህንን ኃላፊነት የተሞላበት አቅጣጫ ማስቀመጣችንም ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ገምግመናል::

በመሆኑም ላለፉት 126 ቀናት በተደረገው የግድያ እና የእስር ዘመቻ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደጋፊወቻችን እና አባላት ለእስራት የተዳረጉ፣ ጥቂቶች ደግሞ መስዋዕትነት የተቀበሉ ቢሆንም በትንሽ መስዋዕትነት ዘመቻውን ጉልህ በሆነ መልኩ (Significantly) ማክሸፍ በመቻሉ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአንዳንድ ቅን አሳቢ ወገኖች የተጀመረውን እንቅስቃሴ በቀናነት ስንመለከት ቆይተናል:

ይህ በእንዲህ እንዳለ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ብቃት ያለው ትውልድ ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት ፈተና ላይ በወደቀበት እና ክልሉ ለሶስተኛ ዙር አውዳሚ ጦርነት ሰለባ በሆነበት በዚህ ወቅት የህዝባዊ ኃይሉ ሰብሳቢ አርበኛ ዘመነ ካሴ በተፈፀመበት መንግስታዊ ክህደት ምክንያት በመንግስት በመንግስት ሃይሎች እጅ ስር ወድቋል።

በህግ ማስከበር ስም ዘመቻ ከተከፈተብን ግዜ አስቀድሞም ቢሆን የድርጅታችን አመራር እና አባላት ሰላማዊ ኑሯችንን የምንመራ እና ምንም አይነት የወንጀል ተሳትፎ የሌለን እንደመሆኑ መጠን ለሰላም እና ለህዝብ አንድነት የምንሰጠውን ዋጋ በጉልህ በሚያሳይ መልኩ መሪያችን ያለ ጦር መሳሪያ ለሰላም ጥሪው የታመነ ሆኖ ከመገኘቱም በተጨማሪ በመሃል ከተማ የተኩስ ልውውጥ እንዳይደረግ በማሰብ በወሰነው ኃላፊነት የተሞላበት ተግባር ምክንያት በመንግስት ኃይሎች ሊታፈን ችሏል::

በመሆኑም:-

1/ ህዝቡ ከተደጋጋሚ ጥቃት መትረፍ እና ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ማግኘት የሚችለው ራሱን ከጥቃት የሚከላከልበት ጉልበት ሲፈጥር እና አንድነቱን የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን በጋራ ማውገዝ እና መታገል ሲችል ብቻ መሆኑን በመገንዘብ አርበኛ ዘመነ ካሴ ከእስር እንዲፈታ ሁሉን አቀፍ ትግል እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን::

2/ የክልሉ መንግስት ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ለአማራ ህዝብ ትግል የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን እንዲገነዘብ እና በድርድር ሽፋን ያፈነውን አርበኛ ዘመነ ካሴን በአስቸኳይ በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ እና ለሀገር ሰላም ከፍ ያለ ዋጋ እንዲሰጥ እግረ መንገዱንም የፖለቲካ ልዩነት አጥር ያልገደበው አዲስ መንገድ እንዲከተል ጥሪ እናቀርባለን::

3/ መላው የአደረጃጀታችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊወች አርበኛ ዘመነ ካሴን ጨምሮ ያለ ህጋዊ ምክንያት የታሰሩ ሁሉም የአማራ ህዝብ ታጋዮችን ለማስፈታት የምናደርገዉ ትግል እንደከዚህ በፊቱ ስክነት እና ብልሃት ያልተለየው እንዲሁም የህዝባችንን አንድነት አደጋ ላይ የማይጥል እንዲሆን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንድትንቀሳቀሱ እናሳስባለን!!!

4/ በመጨረሻም የተነሳንለት እና መስዋዕትነት የከፈልንለት ዓላማ እንደመሆኑ መጠን የአማራ ህዝብ እረፍት የሚያገኝበትን ሀገራዊ መደላድል በመፍጠር በኩል በነቢብም ሆነ በገቢር የሚኖረንን ሁለንተናዊ ሚና አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን።

የአማራ ህዝብ ህልውና በጠንካራ ህዝባዊ ተጋድሎ ይረጋገጣል!!!

አዲስ ትውልድ! አዲስ አስተሳሰብ! አዲስ ተስፋ!

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ)

ባሕርዳር-ኢትዮጵያ

መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም

Filed in: Amharic