>

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በ፵፩ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ንግግር:-

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በ፵፩ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ንግግር:-

“መሬቱ እንደኾነ የትም አልሔደም፣ ሊሔድም አይችልም…!”

አባይ ነህ ካሴ

*…. ሕዝባችን በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱንና ንብረቱን፤ ልጁንና ሚስቱን፤ ቤተ ሰቡንና ሰላሙን እያጣ ነው፡፡ ያላጣው ነገር የለም ሁለመናው ተነክቷል፡፡

ኹሉ የሚቻለው የሚሳነው ነገርም የሌለው አምላካችን እግዚአብሔር ፵፩ኛውን ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ሰዓት እንድናካሒድ ስለፈቀደልን ክብርና ምስጋና አምልኮና ውዳሴ ለእርሱ ይኹን።

እናንተንም አቅፎ ደግፎ በሰላም ወደ ሀገራችሁና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ መንፈሳዊ ጉባኤ ስላመጣልን በድጋሚ እርሱን እያመሰገንን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ደስታችንን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፡፡

• ገሥጽዎሙ ለሕዝብ ወእጽንዕዎሙ ይቤ እግዚአብሔር፡ አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳ ፵፩)

እንዲሁም ኢትግሥሡ መሢሐንዬ፡ ማለት በልጅነት ያከበርኳቸውን ሕዝቤን አትንኩ” ብሎ ሲያስጠነቅቅ እንሰማለን፣ የሚነካም ካለ እናንተ ሕዝቤን አጽናኑ ብሎ አዝዞናል። የተነካውን ሕዝበ እግዚአብሔር ማጽናናት የእኛ ተቀዳሚ ተልእኮ እንደኾነ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በአጽንዖት ሊቀበል ያስፈልጋል።

ሕዝባችን በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱንና ንብረቱን፤ ልጁንና ሚስቱን፤ ቤተ ሰቡንና ሰላሙን እያጣ ነው፡፡ ያላጣው ነገር የለም ሁለመናው ተነክቷል፡፡

ይህ ሲኾን ሕዝቡን ማጽናናት ከኛ ይጠበቃል። ሕዝቡን የምናጽናናው በቃላት ብቻ ሊኾን አይገባም! በመኻሉ ገብተን በመገሠጽና በመምከር፤ በማስተማርና በማሳመን፣ በማስታረቅና እፎይታን በማጐናጸፍ ሊኾን ይገባል፡፡

ሕዝቡ ሕዝባችን ነው፡ እኛም የእርሱ ነን፡፡ ሕዝባችን እርስ በርስ ነው እየተላለቀ ያለው፣ ሌላ ተጨማሪ ቢኖርም ከኛ በተፈጠረው ክፍተት እንጂ በሌላ አይደለም፡፡

ሕዝባችንን የሚያጣላና የሚያፋጅ፣ አሁን ከደረሰበት ደረጃም የሚያደርስ በቂ ምክንያት የለውም፡፡ ቢኖርም በውይይትና በምክክር፣ በፍቅርና ጊዜ ሰጥቶ በማሰላሰል መልክ ሊይዝ የሚችል ነው። መሬቱ እንደኾነ የትም አልሔደም፣ ሊሔድም አይችልም፣ እዚያው ከነበረበት ነው ያለው። ሕዝባችንን ግን ከነበረበት እያገኘነው አይደለንም፡፡ በዚህ ዓለም ድጋሚ ላናገኘው አግባብ በሌለው አኳኋን በየቀኑ እየተሰናበተን ነው። አሁን ጥያቄው ምን እናድርግ? ነው ሲሉ እንደወትሮው ጠንካራ መልእክት አስተላልፈዋል።

ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ዐዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic