>

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ....! (ሞሀመድ ሀሰን)

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ….!

ሞሀመድ ሀሰን


ሀይለስላሴ ጨቋኝ ንጉስ ናቸው በሚል ሀሳብ ተማሪዎቹ ~ ተስማሙና ተሰባሰቡ።  የተስማሙበትን መሰረታዊ የትግል ሀሳብ ጠፋባቸውና እርስበርስ ሲራኮቱ በመካከል ወታደሩ ሰተት ብሎ በመግባት ሀይለስላሴን አውርዶ ስልጣን ያዘ።

ደርግን ከሰልጣን ለማውረድ ወያኔና ሻእቢያ ግንባር ፈጠሩ። አድዋ ንግድ ባንክን ለመዝረፍ በነበረው ኦፐሬሽን ኦፐሬሽኑን እንዲመሩ ሀላፊነት የተሰጣቸው አይተ መለስ ዜናዊ የዘረፋ እቅዱ ተነቅቶ ከደርግ ወታደር ጋ በገጠሙ ጊዜ ጓዶቻቸውን ማዋጋት ትተው ሸሽተው ነበር። በዚያ ውጊያ ብዙ የወያኔ መስራች ተዋጊዎች እንዳለቁ አቶ ገብረመድህን አርአያ፣ አብራሀም ያየህና አቶ መኮንን ዘለለው ምስክርነት ሰተው ነበር። ያኔ አይተ መለስ ዜናዊ የሸሹት ወደ ኢሳያስ አፈወርቂ ነበር። ልጅ ነው እየመከራችሁና እየቀጣችሁ አሳድጉት ብለው መለሱትና ጓዶቹን በመክዳት ወንጀል ከሞት ፍረድ የተረፉት በአቦይ ስብሀት፣አባይ ፀሀዬና ስዩም መስፍን አማካኝነት ነበር። ጥምረቱ አድጎ ደርግ ሲወድቅ ኤርትራ ከኢትዬጵያ ተገንጥላ ሉአላዊ ሀገር ትሆን ዘንድ ከተባበሩት መንግስታት የእውቅና ደብዳቤ የፃፉት አይተ መለስ ዜናዊ ነበሩ። በኋላ ወያኔና ሻእቢያ በኢትዮ–ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሆኑትን ሆኑ። ዛሬም ላይ ያሉበትን ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገር ምስክር ነው።

ወያኔ ስልጣን ላይ ስትወጣ የተወዳጀችው ኦነግ ጋ ነበር። ከህገ መንግስቱ መፅደቅ በኋላና የመጀመሪያ የወያኔ ምርጫ ሰሞን በተነሳ አለመግባባት ወያኔ ኦነጎችን አሽንቀጥራ ጣለቻቸው። ምንም እንኳ ኦነግ ለወያኔ የሚጨክን አንጀት ባይኖራቸውም።

ወያኔን ለማስወገድ በኦሮማራ የኢህአዲጎቹ ኦፒዲና ብአዴን ተጣመሩ። ወያኔ ከሄደች በኋላ እንኳን የኦሮማራ የትግል ሀሳብ ይቅርና በብአዴን በኩል የነበሩት የኦሮማራ ሀሳብ አቀንቃኞች አሁን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መንደር ላይ የሉም። አቶ ደመቀ መኮንን ምንጊዜም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ exception ናቸውና እሳቸው ለምስክርነት መጥራት አይቻልም።  የኦሮማራ መሰረታዊ ጥምረት በወያኔ መወገድ በኋላ እንደ ኢህአዴግ ዘመኑ ብሄር ላይ የተንጠለጠሉ ፓርቲዎችን አክስሞ አገራዊ ራእይ ያለው ጠንካራ ፓርቲ መመስረት የሚል የነበረ ቢሆንም ብልፅግና የኢህአዴግ upgraded version ሆኖ በዚያ በኢህአዴግ የብሄር ፓርቲነት መሰረቱን ተክሏል።

ይሄ ሁሉ ነገር ለምን ሆነ ቢባል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከንጉሱ መወደቅ በኋላ በፖለቲካ ትግል ውስጥ የታወፉ ድርጅቶች ሀገራዊ የሚባል ራእይ የሌላቸው በመሆናቸው እንጂ የፖለቲካዊ አስተዳደር ፍልስፍና ያመጣው ችግር አልነበረም። ለኛ ንጉሳዊ አስተዳደር የሚመጥነን አይለም ብንልም እንኳ ዛሬም ድረስ በንጉሳዊ አስተዳደር ስርአት ውስጥ ያሉ በርካታ ሀገራት አለማችነወ ላይ አሉ። ኮሙኒዝም የሶሻሊዝም ከፍተኛው የአስተሳሰብ ጥግ ነው ይላሉ። በኮሙኒዝም አስተሳሰብ ቻይና የሀገራቸውን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ከመቀየር አልፈው የአለም የመሪነትን ሚና ከአሜሪካ እጅ ለመቀበል ትንቅንቅ ላይ ናቸው። ዘርና ቋንቋ ላይ ራሱን ያቆመው የኛ ፌደራሊዝም አለም ላይ ብቸኛ ቢሆንም በፌደራሊዝም ፖለቲካቸውንም ሆነ ኢኮኖሚያቸውን ያሳደጉ አያሌ  ሀገራት አለማችን ላይ አሉ።

የኛ ሀገር ምን በሽታ ገጠመው ቢባል የፓርቲ ፖለቲካ አላማ እንጂ ሀገራዊ የፖለቲካ አለማ የሌላቸው በዚያ ላይ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ የፖለቲካ ስልጣንና ገንዘብ ያሰባሰባቸው  ፓርቲዎች ሀገራችንን ማስተዳደራቸው ነው። ኦሮሚያ ብልፅግና ከብአዴን በኩል የነበሩ የኦሮማራ ፖለቲከኞችን አፅድቶ በኢህአዴግ ዘመን የነበረውን የብአዴን አይነት ተላላኪና ታዛዥ በአዴፓ ውስጥ ሰብስቦ አጭቆታል። ዛሬ የኦሮማራ ፖለቲካ በስዪም ተሾመ ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው ያለው። ዛሬ ከአዴፓ ውጭ በኦሮሚያ ብልፅግና የተሰበሰቡት አብኖችም አሁን ያለው በወያኔ ዙሪያ ያለው ፖለቲካ በጦርነትም ሆነ በድርድር ከተጠናቀቀ የብአዴን ኦሮማራ ፖለቲከኞች እጣ እንደሚደርሳቸው የታወቀ ነው።

Filed in: Amharic