>
5:33 pm - Thursday December 5, 2599

ብስቁልና እንደብልፅግና - መንግስታዊ የአስመሳይነት አዙሪት! (ዘሪሁን ገሰሰ)

ብስቁልና እንደብልፅግና – መንግስታዊ የአስመሳይነት አዙሪት!

ዘሪሁን ገሰሰ


“…የምንቃወመውና የምንተቸው ሱስ ኖሮብን አይደለም! ”

ኢትዮጵያውያንን ቃላት ድርደራ ፥ የመድረክ ድስኩርና የማይጨበጥ ተስፋ “የእለት ዳቦ” ሲሆናቸው ማየት ህልም እየሆነ መጥቷል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ በየደቂቃው የሚያሻቅበው የኑሮ ውድነት ፥ ለዜጎች በቀን አንድ ጊዜ መመገብን እንኳ አቀበት እያደረገባቸው ነው፡፡ የመንግሥት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ወርሀዊ ደመወዝ ለአንድ ወር ቀርቶ ለአንድ ሳምንት እንኳ በልተው ማደርን ፈታኝ አድርጎባቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የመንግሥት መሪዎች በየእለቱ በየሚዲያውና በየመድረኩ የሚገልፁት የህዝብን ከመጠን ያለፈ ብስቁልና እንደብልፅግና የሚቆጥር ድስኩር “ማንን ለማታለል ወይም ለመሸወድ እየተጣጣሩ ይሆን?” ያስብላል፡፡ ህሊናቸውን? በስቋላውን ህዝብ ወይስ ማንን ?

“ኢትዮጵያ በስንዴ አቢዎት እየተጥለቀለቀች ነው!” መባል ከጀመረ ሁለተኛ አመት ተቆጠረ፡፡ በሁለቱ አመት ውስጥ ደግሞ የዳቦ ዋጋ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየረከሰና ዋጋ እያጣ የመጣው ክቡር የሆነው የሠው ልጅ ብቻ እንጂ በሰው የሚሠሩ ወይም የሚመረቱ ነገሮች በዋጋ የማይቀመሱ ሆነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ችግኝ መትከላቸውን የተቃወመ የለም፡፡ ነገርግን መንግስታቸው ሀላፊነቱን ተወጥቶ ” ሰላምና ደህንነቴን ያስጠብቅልኛል!” ያላቸው ህዝብ በየእለቱ እንደቅጠል እየረገፈ ” ሰው እየሞተም ለአስከሬኑ ጥላ እንዲሆነው ችግኝ እንተክላለን!” ማለታቸው ከመሪ ሳይሆን ከሰይጣን የሚጠበቅ ምላሽ ነበር፡፡

መናፈሻና አበባ መትከላቸውንም የነቀፈ የለም፡፡ ነገርግን ዜጎች ቁራሽ ዳቦ ርቋቸው “ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ” እያሉ ባለበት ሁኔታ ፥ በብድር የሚመጣን ቢሊየን ዶላር ለመናፈሻና መዝናኛ ቅድሚያ ሰጥተው ማፍሰሳቸው ” ትለብሰው የላት ፥ ትከናነበው አማራት” እንዲሉት ብሂል ስለሚሆን ነው፡፡ ሲጀመር ለራሳቸውና ባለፀጎች እንዲዝናኑበት ካልሆነ በስተቀር ለራበው ህዝብ ዳቦ እንጂ መናፈሻ ምኑ ነው?

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይና መንግስታቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሁሉም መስክ በአንደኛው እንኳ ስኬታማ መሆን ቀርቶ የነበረውን ማስቀጠል የተሳናቸው መሆናቸውን ፥ የኖርንባቸው ያለፉት ወደአምስት የሚጠጉ የመከራ አመታት ከበቂ በላይ አስረጂ ናቸው፡፡

“ኢትዮጵያ ስንዴን ለኬኒያና ጅቡቲ ለመሸጥ ውለታ ፈፀመች” ሲባል ወይም ደግሞ ” የድፍድፍ ነዳጅን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ጀመረች” በሚሉን ጊዜ እያረርን የምንስቀው ፥ እያመመን የምንተቸው የሀገራችንን እድገትና ብልፅግና ጠልተን ወይም ሳንፈልግ ቀርተን ሳይሆን የሀገሪቱን ህዝብ የማይጨበጥ ተስፋ እየመገቡ ፥ ከጊዜ ወደጊዜ በሚባባስ ብስቁልናና የኑሮ ጫና ውስጥ መኖሩን የምንረዳ የአይን ምስክሮች ስለሆንን ነው፡፡ በሚናገሩት ሁሉ የምናፌዘው በድስኩራቸው ልክ የምንተቸውም “ፍየል ወዲያ ቁዝምዝም ወዲህ” በሆነው ምግባርና ድስኩራቸው ስለመረረንና እምነት ስላጣንባቸው እንጂ የመቃወምና የመተቸት ሱስ ኖሮብን አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይና መንግስታቸው የተንደላቀቀ መናፈሻ አሰርተው ጥንዶችን እያጋቡ በዋሉበት እለት አለም የሚያወራው ደግሞ ከኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ባሻገር ፥ ኢትዬጲያ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ አስከፊ ድርቅ መመታቷንና ከ20 ሚሊየን የሚልቁት ዜጎቿ በከፋ የረሀብ ጠኔ ውስጥ ሆነው አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ የሚሹ መሆናቸውን ነው፡፡

ይህ የማስመሰልና የመሪዎች የታይታ የመሞላቀቅ አባዜ ክፉ ጭካኔ ከመሆኑ ባሻገር ፥ ነገ የሚያመጣው ዳፋ እጅግ የከፋና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ተረኛ ገዢ ሄዶ ተረኛ ገዢ እየተተካ ፥ በተመሳሳይ አዙሪትና የማስመሰል አባዜ ውስጥ ፥ ፍዳውን የሚበላው ህዝብ መከራና ግፉ የሚያቆምበት ጊዜ መቼ ይሆን ?

ቀና የህነ ልቦናና ፥ ለራሱ የሚያድር ያልተሸጠ ህሊና ይስጠን!

Filed in: Amharic