>

ፀረ- አማራ የሆነው ህገ-መንግስት  የድርድሩ ማጠንጠኛ መደረጉ  ለአማራው የተቀበረ ፈንጅ ነው...! (ደሞዝ ካሳዬ መኮንን)

ፀረ- አማራ የሆነው ህገ-መንግስት  የድርድሩ ማጠንጠኛ መደረጉ  ለአማራው የተቀበረ ፈንጅ ነው…!

ደሞዝ ካሳዬ መኮንን – የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ጠበቃ

ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች!


ደቡብ አፍሪካ በታካሄደዉ ድርድር በዋናነት ትህነግን ማትረፍ ተችሏል፡፡ የቤት ባሪያዎቹ ዥዋዥዌ ከመጫዎት ዉጭ ምንም ሚና ስለማይኖራቸዉ ስለእነሱ ብዙም መጨነቅ የለብንም፡፡ ይሁን እንጅ ከራሳችንና ከቀጠናዉ ጥቅም አንፃር ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን አነሳለሁ፡፡

1. በዚህ ድርድር ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጠዉ ዋና አቅጣጫ ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ነዉ፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ትህነግና ኦህዴድ/ኦነግ ናቸዉ፡፡ ምክንያቱም ይህ ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ፀረ- አማራ መሆኑ የታወቀ ሀቅ ስለሆነ፡፡

2. ይሄ ድርድር ዋናዉንና ወሳኙን የማንነትና የወሰን ጉዳይ (ወልቃይት፣ጠለምትና ራያ) በማድበስበስ ያለፈዉ በመሆኑ ችግሮች መቀጠላቸዉ አይቀርም፡፡

3. በዚህ ጦርነት ብዙ ጉዳት የደረሰባቸዉ አማራና አፋር በድርድሩ ባለመወከላቸዉ የሰላም ስምምነቱን ዘላቂነት ጥያቄ ዉስጥ ይከተዋል፡፡ የኤርትራ አለመሳተፍም ነገሩን ማወሳሰቡ አይቀርም፡፡ በዚህም የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ጉዳይ አደጋ ዉስጥ ይገባል፡፡

4. የዚህ ጦርነት ዋና ግብ ትህነግን ማክሰምና ምልክቱን፣ አስተሳሰቡንና ስሙን መጠቀም ወንጀል የሚሆንበትን ስርዓት ማስፈን/ማንበር  መሆን ሲገባዉ ትህነግ ህልዉናዉ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ ትህነግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ተሳተፎዉ እስከቀጠለ ድርስ ለኢትዮጵያም ሆነ ለምስራቅ አፍሪካ የሰላም ስጋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ትህነግ በምርጫ አሸንፎ ክልሉን ማስተዳደሩ ስለማይቀር ለአማራ ህዝብ የስጋት ምንጭ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

5. ትህነግ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ለፈፀመዉ የዘር ማጥፋት፣ የጦር መንጅልና በሰብአዊነት ላይ ለፈፀመዉ ወንጀል ተጠያቂ ስለማይሆን ቁርሾዉ ከህዝባችን ጋር አብሮ ይቀጥላል፡፡

6. በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ የደረሰዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ተገቢዉ ትኩረት ባለመሰጠቱ እነዚህን አከባቢዎች መልሶ የማልማትና ማህበራዊ ምስቅልቅሉን የማስተካከል ስራዎች ዝቅተኛ ይሆናሉ፡፡

7. የአማራን ህዝብ ጥያቄ በሚያነሱ ሀይሎች ላይ ትህነግ፣ ብአዴንና ኦህዴድ/ኦነግ በመተባበር ርምጃ ይወስዳሉ፡፡

Filed in: Amharic