>

የፕ/ር፣ ዶ/ር፣ ኢንጂነር ማእረግ የእውቀትና ጥበብ ምልክት አይደለም...!  (ግርማ ካሳ)

የፕ/ር፣ ዶ/ር፣ ኢንጂነር ማእረግ የእውቀትና ጥበብ ምልክት አይደለም…!

 ግርማ  ካሳ


“ይድረስ ከአባ ጅፋር ፣ የሰው ባሪያ የለውም፡፡ ሁላችንም የ እግዚአብሄር ባሪያዎች ነን፡፡ እግዚአብሄር መርጦ ከሰው አልቆ ሲያስገዛ ጊዙእ በሰው መጨከን አይገባም፡፡ ለሰው ቢያዝኑ እድሜ ይሰጣል፡፡ ድሃ ሊኖር በተመኘው ቦታ ይኑር”

ዳግማዊ አጤ ሚኒሊክ ለጅማ አባ ጅፋራ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ

ተማርን የምንል፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፕሮፊሰር  ወዘተ ማእረጎች ከስማችን ፊት የምንቆልል ብዙ አለን፡፡ ስለ አርቲቪሻል ኢንቲሊጀንስ ፣ ስለ አስትሮ ፊዚክስ፣ ስለ ሳይበር ሴኩሪቲ ፣ ስለ አሪስቶተል፣ ፕላቶ፣ ሶክራትስ፣ ሩሶ፣ ቮልቴር ፍልስፍና አስተምህሮዎች የምንጠቀስ ፈላሳፋዎች ፣ የማህ በረሰብ ሳይንስ  ተመራማሪዎች ነን፣ አዋቂዎች ነን የምንል፡፡ ነገር ግን የቀለም ትምህርት አዋቂነት አያስብልም፡፡ የቀለም ትምህርት ጠቢብ አያስብልም፡፡ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው፡፡

በአገራችን የመንግስት ዋና ስልጣን ያለው ጠቅላይ ሚኒስተሩና ካቢኔው፣ ወይንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚባለው ጋር ነው፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ጌዴዎን ማቴዎስ፣ ዶር ይናገር ደሴ፣ ዶር በለጠ ሞላ፣ ዶር ሊያ ታደሰ፣ ቢያንስ አምስት PhD ያላቸው አሉ፡፡ ሌሎችሊኖሩ ይችላሉ፡፡  እንደ መላኩ አለበል፣ አህመድ ሺዴ የመሳሰሉ ማስተርስ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በትላልቅ የትምህርት ተቋሟት ተምረናል የሚሉ ናቸው፡፡

ግን እንዴት ነው አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት ብለን ብንጠይቅ፣ አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ መረዳት እንችላለን፡፡  እያስተዳደሩ ያሉት እንደ መሃይማን ነው፡፡ በእውቅት፣ በጥበብ ከመቶ አመት በፊት የነበሩ አጤ ሚኒሊክ የትናየት ይበልጧቸዋል፡፡

አጤ ሚኒሊክ ድሃ በተመኘው፣ በወደደው ቦታ ሁሉ ይኑር ነበር የሚሉት፡፡ ያ ማለት አንድ ኢትዮጵያዊ ከቦንጋ ተነስቶ  ጂጂጋ፣ ከመቀሌ ተነስቶ ኮፈሌ፣ ከዳንግላ ተነስቶ ዶዶላ፣ ከጎሬ ተነስቶ ሽሬ፣ ከሻኪሶ ተነስቶ ወሊሶ፣  ከአዋሳ ተነስቶ አሶሳ፣ ከሁመራ ተነስቶ ቡታጅራ፣ ከዉቅሮ ተነስቶ ጭሮ፣ ከደሴ ተነስቶ መገናሴ፣ ከሆሳና ተነስቶ ቢቸና፣ ከሰቆጣ ተነስቶ ሞጣ .. ፣ በወደደው ቦታ ይኑር ማለታቸው ነበር፡፡ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከዚህ ማለፍ አትችልም፣ አገርህ ይች አካባቢ ብቻ ናት ተብሎ አጥር አይበጅለት ማለታቸው ነበር፡፡

​አሁን ያሉት ገዢዎች ከደናቁርት ዘረኛ ህወሃቶች መማር ሲገባቸው፣ የባሱ ደናቁርት ሆነው፣ ኢትዮጵያዉያን በወደዱት ቦታ እንዲኖሩ ማድረግ አልቻሉም፡፡ እነርሱ እየመሯት ባለችው ኢትዮጵያ ፣ “አገራችሁ አይደለም፣ እዚህ መኖር አትችሉም” እየተባሉ ዜጎች በግፍና በጭካኔ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ የዘር አጥር፣ የዘር ክልል፣ የዘር መከፋፈል፣ የዘር ልዩነት እንደ ትልቅ ጀበድ ተቆጥሮ አገር እየጠፋች ነው፡፡

አሁንም የምንለው ይሄን ነው፡፡ “የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት ” ወዘተ እየተባለ ኢትዮጵያን በዘርና በጎጥ የመከፍፈል አሰራር ይቁም፡፡ኢትዮጵያዉያን በዘርና በጎጥ እንዲከፋፈሉ፣ እንዲከፋፈሉ ብቻ ሳይሆን ተከፋፍለው ደም እንዲቃቡ ያደረገው የዘር ህገ መንግስት ፣ የእድገት፣ የሰላምና የብልጽግና ጸር ስለሆነ፣ ይቀየር”  እንላለን፡፡

“የትግሬ አገሩ ትግራይ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያ ነው፡፡ የአማራ አገሩ መላው ኢትዮጵያ ነው፡፡ የጉራጌ አገሩ መላው ኢትዮጵያ ነው፡፡  ዜጎች በወደዱበት ቦታ የመኖር፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ የመነገድ፣ የመውጣት፣ የመግባት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው ይረጋጋጥ!!!!!!” እንላለን፡፡

(በነገራችን ላይ ቀንተህ ነውም አንተ ዲግሪ ስለሌለ የምትሉ ካላችሁ፣ በሞያዬ ሶፍትዌር ኢንጂነርና ፊዚሲስት ነኝ፡፡ በ Applied Physics (Superconductity)   እና በ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ  ሁለት ማስተርስ ዲግሪዎች ያሉኝ ሰው ነኝ፡፡ ከላይ እንዳልክት ኝ ዲግሪ መቆለል የ እውቀትና የጥበብ ምልክት አይደለም)

Filed in: Amharic