አርበኛ ዘመነ ካሴ ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ!!!
ቀን 12-03-2015
ጉዳዩ:- ቅሬታ ስለማቅረብ
“…እዚህ ፍርድ ቤት ላይ መገኘት ከጀመርሁበት ዕለት ጀምሮ ወደ ችሎት የምመጣው ጠላቶቼ በየጊዜው ለጥፋት በሚቆፍሯቸው የሞት ሸለቆዎች መሃል እየተሽሎኮሎክሁ ቢሆንም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቼ እና ቤተሰቦቼ ችሎት እንዳይከታተሉ እየተደረገ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ባህርዳር ከተማ የውጊያ ግንባር እስኪመስል ከፍርድ ቤት ቀጠሮ ዋዜማ ጀምሮ በምድርም በሰማይም ከዲሽቃ እስከ ክላሽ በታጠቁ ኃይሎች ይወጠራል።
“…እኔ ዘመነ በድንግል ማርያም ልጅ መንፈስ የምመራ፣ የሰውን ልጅ በሙሉ የማፈቅር ንፁህ ነፃ አውጪ እንጂ አንድ ክፉ ጥግ ያበቀለኝ ወንበዴ አይደለሁም። ይህን ሊያጠፉኝ ሌት ተቀን እረፍት አጥተው የሚሠሩ እኩያን እንኳን ያውቃሉ። እኔ ከአንድ ካድሬ አንድ የለሊት ልብስ (ቢጃማ) ዋጋ ያነሰ ደመወዝ የሚከፈላቸው ዩኒፎርም ለባሽ የድሀ ልጆች ጋር ችግር የለብኝም። ነፍሴን ሊያጠፉ ብዙ ሺህ ጥይቶች ተኩሰውብኝ እንኳን አልጠላኋቸውም። ፈጽሞ አልጠላቸውምም። አንድ ቀን ያውም በቅርብ አንድ ህዝባዊ ዩኒፎርም እንደምንለብስ እርግጠኛ ስለሆንሁም ጭምር። ነገር ግን ዘመን ባሰከራቸው ጌቶቻቸው ትዕዛዝ በሚሰማሩ ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቼ ወደ ፍርድ ቤት አካባቢ እንኳን እንዳይደርሱ በቆመጥና በሩምታ ተኩስ ጭምር ይከለከላሉ። ቤተሰቦቼም ይከለከላሉ፣ ይታሰራሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተደብድበዋል፣ አካላቸው ጎሏል፣ ለረዥም ጊዜ ታስረዋል።
“…በዚህ ሁኔታ ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት ዳገት ስወጣ፣ ቁልቁለት ስወርድ በመንፈስ አብሮኝ ሲወጣና ሲወርድ የኖረው አሁንም እየተጨነቀ ያለው መላውን ዐማራና ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ለሌላ ጉዳት ምክንያት ልሆንባቸው ስለማልሻ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲቆም ካልተደረገ ከዛሬ በኋላ እዚህ ችሎት ላይ ለመገኘት የማልችል መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ።
• (ክፋት ለማንም፤ በጎነት ለሁሉም)
• አዲስ ትውልድ ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ተስፋ!!
• አሸናፊነት ግንባራችን ላይ የተጻፈ እጣ ፈንታችን ነው!!
• ድል ለዐማራ ህዝብ!
• ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
አርበኛ ዘመነ ካሴ
ከባህርዳር ወኅኒ ቤት