>

ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ የትግል ህይወት የባህሩን በጭልፋ...! (ጌጥዬ ያለው)

ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ የትግል ህይወት የባህሩን በጭልፋ…!

ጌጥዬ ያለው


ሐቀኛው ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ በአሸባሪው ወያኔ ስርዓት በጋዜጠኝነታቸው ምክንያት በተደጋጋሚ በየፖሊስ ጣቢያው ሲታሰሩ ቆይተዋል። ‘ወግድ ይሁዳ’ በሚለው ተከታታይ ትንታኔያቸው በስፋት ይታወቃሉ። ይህ ትንታኔ በርካታ አድናቆትን ያተረፉበት ሲሆን ከስርዓቱ ጋር ጡት የተጣቡ ጠላቶቻቸውንም አስተዋውቋቸዋል። ጋሼ ለራሳቸው ጥያቄና መልስ በማዘጋጀት፤ ራሳቸው ጠያቂና መላሽ ሆነው በሚያቀርቡት ለብላቢ ቃለ መጠይቅም ይታወቃሉ። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ በነፃው ፕሬስ ውስጥ የታዴዎስ ታንቱ ስታይል ሊባል ይችላል።

ወያኔ የ15 ዓመታት እስር ፈርዶባቸው ለዓመታት በሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ቆይተዋል።

ታዴዎስ ታንቱ በአብዮታዊ ጦር ሃይሎች ዋና የፖለቲካ አስተዳድር ስር በነበረው ‘ታጠቅ’ ጋዜጣ ከ1975 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። ከዚህ በኋላም በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ በኢትዮጲስ ጋዜጣ፣ በአስኳል ጋዜጣ፣ በፍትሕ ጋዜጣ፣ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ እና በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች በአምደኝነትና በአዘጋጅነት ለረጅም ዓመታት በነፃው ፕሬስ አገልግለዋል። በአሁኑ ጊዜ በትርፍ ጊዜያቸው በራስ ሚዲያ በጋዜጠኝነት እያገለገሉ ሲሆን የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆነዋል።

የኅሊና እስረኛው ጋሽ ታዴዎስ ከሀቀኛ ጋዜጠኝነታቸው በተጨማሪ በመምህርነታቸው እና በታሪክ ፀሐፊነታቸው ይታወቃሉ።

በኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ ተከታታይ ቅፅ ያላቸው መፅሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል። ይህ ባለተከታታይ ቅፅ መፅሐፍ ‘ደም መላሽ’  በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን አንደኛውና ሁለተኛው ቅፅ ታትሞ በመነበብ ላይ ነው። ሦስተኛው ቅፅ በወረቀት ደረጃ በዝግጅት ላይ እያለ በወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና የውንብድና  ቡድን ሲታፈኑ በእጃቸው ላይ ስለተገኘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

‘የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ’ እና ‘ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ’ ሌሎች ጋሽ ታዴዎስ ለንባብ ያበቋቸው መፅሐፍት ናቸው። ‘የለውጥ ምጥ በኢትዮጵያ’ በ2009 ዓ.ም. የታተመ ሲሆን የወያኔን ውድቀት አስቀድሞ የተነበየ ነበር። ‘ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኛ’ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ልዕልና የሚያሳይ ሲሆን ባንዳ፣ ሆድ አደር እና ባለሟል ጋዜጠኞችንም ያለ አንዳች ይሉኝታ ለይቶ ያስቀመጠ ነው። ለሐቅ  ውግንና የታየበት መፅሐፍ ነው።

አዛዎንቱ ጋዜጠኛ ታዴዎስ ታንቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሻሸመኔ አፄ ናኦድ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት አፄ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤት እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪ እና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል።

ጋሽ ታዴዎስ ከሁሉም በላይ ብዙዎቻችን ልቦናችን እያወቀው አንደበታችን የማይደፍረውን ሐቅ አፍርጠው በመናገር ይታወቃሉ።

ባለፈው አመት በመጤ የወራሪዎች አገዛዝ “‘የአማራ ደም የእኔም ደም ነው’ ብለሀል” በሚል ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በመናድ በሀሰት ተወንጅለው ታግተው ቆይተዋል። ከግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ “አንድን ብሔር ለይቶ መጥላት” በሚል አስቂኝ ውንጀላ ተወንጅለው የምርመራ ዶሴው ተጠናቆ ክስ እስኪመሰረትባቸው ድረስ ማዕከላዊ ማጎሪያ ቤት ቆይተዋል። ተጠላ የተባለው ብሔር የወራሪዎቹ ወገን ኦሮሞ መሆኑ ነው። በምግባር እንጂ በማሰር መወደድ ይቻል ይሆንን? ከምርመራው በኋላ አምስት ተደራራቢ የሽብር ክሶች በሀሰት ተመስርቶባቸው ዛሬም በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛሉ። ነገ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ይቀርባሉ። ታደሙ! ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ጋዜጠኝነት እና ሕግን ታገናዝቡበታላችሁ።

Filed in: Amharic