>

አሜሪካን ሀገር ሊመሠረት ለታሰበው ገዳም አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያበረከተችው ትዕግሥት በላይ ፈረደ‼  (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

አሜሪካን ሀገር ሊመሠረት ለታሰበው ገዳም አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያበረከተችው የቸርነት እመቤት የባሕርዳሯ ልጅ ትዕግሥት በላይ ፈረደ‼ 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሕዝባችን እኮ ሰው አጣ እንጅ ካመነበትና እውነተኛ ወይም ታማኝ ሰው ካገኘ እኮ ምንም የማድረግና የትም የመድረስ እምቅ አቅምና ፍላጎት ያለው ለመሆኑ ቸሪት እኅታችን ማሳያ ናት‼

ግን ምን ዋጋ አለው ሰው አጥቶ ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካው ተገጥግጠው የተሰለፉት በሙሉ የአሸባሪውና የአረመኔው አገዛዝ ቅጥረኞችና ምንደኞች ሆነውበት ተኮድኩዶ ተያዘ እንጅ‼

እኅታችን ይሄ ችሮታ የመጀመሪያዋ ሳይሆን እንደ እነ ቢንያም በለጠ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ከሐምሳ በላይ አቅመ ደካማ አረጋውያንን ሰብስባ በመጦር ላይ ያለች፣ በገዳምም ለመናንያን መጠለያ ወይም በዓት የገነባች ወዘተረፈ. በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት የከበረች ታላቅ ክርስቲያን ናት‼

እኅታችንን “መድኃኔዓለም ክርስቶስ በዚህ የጽድቅ ሥራሽ ያጽናሽ፣ መልካም ነገር ሲሠራ የሚቀናው ምቀኛው ሰይጣን እንዳያሰናክልሽም ይጠብቅሽ!” ብላቹህ መርቋት እስኪ!?

እነ የወደቁትን አንሱው አቶ ስንታየሁ አበጀ፣ የመቄዶኒያው ቢንያም በለጠ፣ የሙዳይዋ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፣ እኅታችን ትዕግሥት በላይ እና ሌሎችም እኛ የማናውቃቸው እግዚአብሔር ግን የሚያውቃቸው ደጋግ ሰዎች እግዚአብሔር እንደኃጢአታችን ብዛትና ክፋት ጨክኖ እንዳይጨክንብን ያደረጉልን ቅዱሳን ናቸውና ሳሱላቸው፣ ጤናና ሰላም እንዲሰጣቸው፣ ከክፉው ሰይጣን ውጊያ እንዲሰውራቸው ዘወትር ጸልዩላቸው‼

ገንዘብ ያላቹህ ወገኖች እንደእየ ችሎታቹህ መጠን ተመሳሳይ የቸርነት ወይም የጽድቅ ሥራ በመሥራት ካልተጋቹህና በስስት ታንቃቹህ እየተንገበገባቹህ ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ የተወሰናቹህ ከሆናቹህ ዓይነልቡናቹህ የታወረና እጃቹህ ገሃነም ሊያወርዳቹህ በሚፈልገው በምቀኛው ሰይጣን የታሰረ መሆኑን ዕወቁ‼

ጌታ በወንጌሉ “እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል!” ሉቃ. 11፤40-41

ሲራክም በመጽሐፉ “እሳት በውኃ እንዲጠፋ የኃጢአትም ብዛት በምጽዋት ይጠፋል!” ይላልና ከንስሐ ባሻገር የበዛና የከፋ ኃጢአታቹህ ተሠርዮላቹህ ገነት መግባት ወይም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ከፈለጋቹህ ዕወቁበት!!

Filed in: Amharic