>
5:13 pm - Friday April 19, 8318

የዶክተር ደረጀ ዘለቀ ቅጥፈት እና ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ ያለው እውነታ (ጌታ በለጠ፣ ደብረ ማርቆስ፣ጎጃም)

የዶክተር ደረጀ ዘለቀ ቅጥፈት እና ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ ያለው እውነታ

(ጌታ በለጠ፣ ደብረ ማርቆስ፣ጎጃም)


በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆነው ዶክተር ደረጀ ዘለቀ ከርዕዮት ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያ ፓትረያርክ የነበሩትን አቡነ ቴዎፍሎስ በተመለከተ የተሳሳተ ማንነት ከመስጠቱም ባለፈ የኦነግ ሰላይ እና መረጃ አቀባይ አድርጎ ይከሳቸዋል። ዶክተር ደረጀ “አቡነ ቴዎፍሎስ ኦሮሞ ናቸው፥የተገደሉትም ለኦነግ መረጃ ሲያቀብሉ ነው” ሲል እጅግ ድፍረት በተሞላበት አኳኋን ተናግሯል።በመሰረቱ ዶክተር ደረጀ ዘለቀ የአቡነ ቴዎፍሎስን ማንነት ሲቀይርም ሆነ ባልሰሩት ወንጀል ሲከሳቸው ምንም አይነት የታሪክ ማስረጃ አላቀረበም። ያለ ማስረጃ ሰዎችን መወንጀል አንድ ሕግ የተማረ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ድርጊት አይደለም። ዶክተር ደረጀ ዘለቀ ግን አደረገው፡፡ 

 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ዶክተር ደረጀ ዘለቀ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ያቀረበውን ያልተገባ ክስ እና የማንነት ቅየራ በማስረጃ ማስተባበል ነው፡፡ከዚህ ባለፈ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የሚቀርቡ ያለጠሩ አመለካከቶች ፈር ይይዙ ዘንድ የጠራ ማስረጃ እናቀርባለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ፡፡ 

  1. አቡነ ቴዎፍሎስ ኦሮሞ ናቸው ውይስ አማራ?
  2. አቡነ ቴዎፍሎስ ለምን ከእስር ተዳረጉ?  እውን አቡኑ ኦነግን ይረዱ ነበር?
  3. አቡነ ቴዎድሮስን ማን ገደላቸው? አፅማቸውስ የት እና እንዴት ተገኘ?

አቡነ ቴዎፍሎስ እውን ኦሮሞ ናቸው?

አቡነ ቴዎፍሎስ የተወለዱት ሚያዝያ 16 ቀን 1899 ዓ/ም በጎጃም ክፍለሀገር፣ ደብረ ማርቆስ አውራጃ፣ ደብረ ኤልያስ ከተባለ ቦታ ነው። እዚህ ላይ ዲያቆን መርሻ አለኸኝ “ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን” ሲል በ1996 ዓ/ም በጻፈው መጽሐፍ ገጽ 33 ላይ የአቡኑን የውልደት ዘመን ሚያዚያ 1902 ዓ/ም እንደሆነ ጽፏል፡፡ነገር ግን የአቡነ ቴዎፍሎስ ታናሽ ወንድም ልጅ የሆነው እና አቡኑ ራሳቸው ያሳደጉት መምህር ታምራት አበራ ጀንበሬ ውቤ የተባለ ግለሰብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የአቡነ ቴዎፍሎስ የትውልድ ዘመን ሚያዚያ 16 ቀን 1899 ዓ/ም እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በነገራችን ላይ ታምራት አበራ ጀንበሬ “ቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ( የሕይወት ታሪክ)” በሚል ርዕስ የአቡኑን የሕይወት ታሪክ ለንባብ አብቅቷል። 

የአቡነ ቴዎፍሎስ አባት ሻቃ ጀንበሬ ውቤ እና እናታቸው ወይዘሮ ዘርትሁን አደላሁ እዚያው የደብረ ኤልያስ ተወላጅ የሆኑ የጎጃም አማራ ናቸው፡፡ሻቃ ጀንበሬ ውቤ ወታደር ስለነበሩ እስከ ጅማ እና ከፋ ድረስ በመኼድ ሐገራቸውን አገልግለዋል፡፡በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ደብረ ኤልያስ ተመልሰው እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ኖረዋል፡፡ ሻቃ ጀንበሬ አቡነ ቴዎፍሎስን የወለዷቸው ከከፋ ወደ ትውልድ መንደራቸው ደብረ ኤልያስ ተመልሰው ሚስታቸውን ወይዘሮ ዘርትሁን አደላሁን አግብተው ነው።

የአቡነ ቴዎፍሎስ የልጅነት ሥም ይታዬው ነበር፡፡ ይታዬው የሚለውን ሥም ያወጡላቸው አባታቸው ሻቃ ጀንበሬ ውቤ ናቸው፡፡ ገና በልጅነታቸው ከዚያው ደብረ ኤልያስ ደብር ንባብና ዳዊት ከመርጌታ ረዳኸኝ ዘንድ ተማሩ። ንባብና ዳዊት ሲጨርሱ የዜማ ትምህርት እዚያው ደብር ካሉ መምህር ግራጌታ ሣህሉ ዘንድ ተማሩ። ከዚያ በኋላ ቅኔ፣ ቅዳሴ፣ ውዳሴ ማርያም እና የወንጌል ትርጓሜ ከየኔታ ገብረሥላሴ ዘንድ ተማሩ።የኔታ ገብረሥላሴ ለህፃኑ ይታዬው (በኋላ አቡነ ቴዎፍሎስ) መልእክቱ የሚል ሥም አወጡላቸው፡፡ የኔታ ገብረሥላሴ የወለጋ ኦሮሞ ናቸው፡፡ከወለጋ ወደ ጎጃም ለትምህርት እንደመጡ ደብረ ኤሊያስ ከተባለ ቦታ ኖሩ፡፡ዶክተር ደረጀ ዘለቀ “አቡነ ቴዎፍሎስ ኦሮሞ ናቸው” ሲል ምን አልባት የአቡነ ቴዎፍሎስ የልጅነት መምህር የሆኑትን የኔታ ገብረሥላሴን ከአቡነ ቴዎፍሎስ መለየት ተስኖት ከሆነ በግልጽ ይናገር፡፡

የሆነ ሆኖ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1920 ዓ/ም (በ1922 ዓ/ም የሚሉ አሉ) አዲስ አበባ ከሚገኙት ሊቀ ሐዲስ ተክሌ ዘንድ በመኼድ መጻሕፍተ ሐዲሳትና እና የፍትሐ ነገሥትን ትርጓሜ አጠኑ። ከአስር (አስራ ሁለት) ዓመታት በኋላ (1930 ዓ/ም) ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመኼድ የምንኩስና ማዕረግ ተቀበሉ። አባ መልእክቱ ተብለው ተጠሩ። በጣሊያን ወረራ ወቅት አቡነ ቴዎፍሎስ ከመምህራቸው ሐዲስ ተክሌ ሳይለዩ ረዳት መምህር በመሆን የቤተክርስቲያን ትምህርት እንዳይቋረጥ በትጋት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። 

በ1934 ዓ/ም ጃንሆይ ኃይለሥላሴ ለተለያዩ ምሑራን ዘመናዊ የትምህርት ዕድል ሲሰጡ አቡነ ቴዎፍሎስ አንዱ የዕድሉ ተጠቃሚ ስለነበሩ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት( በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አጠኑ፡፡በ1935 ዓ/ም የመካነ ሥላሴን ገዳም በአለቅነት እንዲያስተዳድሩ መምህር ተብለው ተሾሙ፡፡መካነ ሥላሴ ተሰርቶ መንበረ ጸባኦት ቅዱስ ሥላሴ ካቴድራል ሲሰኝ በ1938 ዓ/ም የመጀመሪያው አለቃ በመሆን ሊቀ ስልጣናት ተብለው ተሾሙ፡፡ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ/ም ለመዓርገ-ጵጵስና ተመርጠው ሊቀ ጳጳስ ተባሉ። በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያው ፓትሪያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ ሆነው በመሾም እስከ 1963 ዓ/ም ድረስ በተለይ የውጭውን ጉዳይ ኃላፊነት ተሸክመዋል፡፡ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፓትርያርክና ዕጨጌ ዘመንበረ-ተክለሃይማት ሆነው በኢትዮጰያ ምድር ተሹመዋል፡፡በዚህም በኢትዮጵያ ምድር የተሾሙ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ለመሆን በቅተዋል፡፡ የካቲት 9 ቀን 1968 ዓ/ም በዕለተ ማክሰኞ ከመኖሪያ ቤታቸው በምሽት በደርግ መንግስት ታፍነው ወደ ቤተ መንግስት ተወስደው ታሰሩ። ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ/ም በዕለተ ቅዳሜ ተገደሉ። 

አቡነ ቴዎፍሎስ ለምን በደርግ መንስግስት ተገደሉ? እውን ኦነግን ሲረዱ በመያዛቸው ነበር የተገደሉት?

ዶክተር ደረጀ ዘለቀ ያለምንም ማስረጃ “አቡነ ቴዎፍሎስ የተገደሉት ለኦነግ መረጃ ሲያቀብሉ ነው” ማለቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ በውል የማያውቅ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ዶክተር ደረጀ የውሸት ውንጀላ ከማቅረብ ያለፈ የጠቀሰው የታሪክ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ “ውሸታም”ብለን ከማለፍ የተሸገረ ክርክር አናደርግም፡፡አቡነ ቴዎፍሎስን አስሮ የገደላቸው የደርግ መንግስት እንኳን ሌሎች ክሶች አቀረበ እንጅ አቡነ ቴዎፍሎስን የኦነግ የመረጃ አቀባይ አድርጎ አይከሳቸውም፡፡ዶክተር ደረጀ አቡነ ቴዎፍሎስን የኦነግ መረጃ አቀባይ አድርጎ የከሰሳቸው “አቡኑ ኦሮሞ ናቸው” የሚለውን የውሸት ትርክቱን ለማጠናከር ብቻ ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የአቡነ ቴዎፍሎስን አያያዝ እና አገዳደል በተመለከተ ትቂት ማውራቱ አስፈላጊ በመሆኑ የሚከተለውን አቀርባለሁ፡፡የደርግ መንግስት አቡነ ቴዎፍሎስን ያለ ፍርድ ነው የገደላቸው፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ያለ ፍርድ መግደሉ ብቻ ሳይሆን ከገደላቸው በኋላ ሥማቸውን ለማጥፋት የኼደበት ርቀት ነው፡፡

የደርግን ፀረ ኦርቶዶክስ ፖሊሲ እንደማይቀበሉ የተገነዘበው የደርግ መንግስት አቡነ ቴዎፍሎስን ያለተገባ ሥም በመስጠት በሕዝቡ ዘንድ ለማስጠላት ያላደረገው ጥረት አልነበረም፡፡የደርግ መንግስት ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረው ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ “አብዮቱ እና ትዝታዬ” ሲል በሰየመው መጽሐፉ ገፅ 199 ጀምሮ ስለ አቡነ ቴዎፍሎስ አያያዝ እና አገዳደል የጻፈውን እንመልከት፡፡

ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ መንግስት የተያዙበትን ምክንያት ሲገለጽ “ፓትርያርኩ የራሳቸውን ዘመዶች ይሾማሉ፣በመንግስት ላይ አሻጥር ይሰራሉ፣ለዲያቆናት እና ቀሳውስት ደመወዝ ጭማሬ ከልክለዋል፣በጣሊያን ወረራ ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ሲገደሉ እጃቸው አለበት የሚል የተፈረመበት ክስ ደርሶናል”ይላል፡፡እያንዳንዳቸው ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን እንመልከት፡፡

የመጀመሪያው ክስ አቡነ ቴዎፍሎስ የራሳቸውን ዘመዶች ይሾሙ ነበር የሚል ነው፡፡ በእርግጥ የደርግ መንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት አቡነ ቴዎፍሎስ ለአቡነ ጳውሎስ፣ ለአቡነ ባስልዮስ እና አቡነ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ሹመት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ሦስቱም አቡኖች አይደለም የአቡነ ቴዎፍሎስ ዘመድ ሊሆኑ ቀርቶ የአንድ አካባቢ ሰዎች እንኳን አልነበሩም፡፡ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ይኼንን ክስ ሲያቀርብ አቡነ ቴዎፍሎስ የትኞቹን ዘመዶቻቸውን እንደሾሙ ያቀረቡት ማስረጃ የለም። ይኼ ደረቅ ውንጀላ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የቀረበባቸው ክስ በመንግስት ላይ ያሴራሉ የሚል ነው፡፡ ይሄ ክስ መሰረተ ቢስ ነው፡፡ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ በጠቅላላው አቡኑ በመንግስት ላይ ያሴራሉ ከማለት ውጭ መቼ እና እንዴት እንዳሴሩ ያቀረቡት ማስረጃ የለም፡፡ ይሄንን አስመልክቶ በወቅቱ ከኃይለሥላሴ ባለስልጣናት ጋር በታላቁ ቤተ መንግስት እስር ቤት ለስምንት ዓመታት ያኽል ታስሮ የተፈታው አበራ ጀምበሬ “የእስር ቤቱ አበሳ በታላቁ ቤተ መንግስት (1966-1974)” ሲል ባሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 141 ጀምሮ ያዬውን ሃቅ አስቀምጧል፡፡ አበራ ጀምበሬ በዚህ መጽሐፍ ገጽ 144 ላይ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊያሳስራቸው የቻለው አቋማቸው ከደርግ ፖሊሲ ጋር የማይስማማ በመሆኑ እና የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከበር ያላቸው የማይታጠፍ አቋም እንደሆነ ጽፏል፡፡

የአበራ ጀምበሬን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ መስፍን በቀለ “ስኳዶቹ- ገዳይ ጓዶች” በተሰኘው መፅሐፉ የወቅቱ የዘመቻና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ሻለቃ (በኋላ ኮሎኔል) ዳንኤል አስፋው አቡኑ መጋቢት 10 ቀን 1968 ዓ/ም ለደርጉ መንግስት የፃፉትን ማመልከቻ ተቀብሎ ያልፃፉትን እንደፃፉ አድርጎ፣ በደብዳቤውም አቡኑ አዲሱን መንግስት እንደሚወነጅሉ አድርጎ ለደርግ ቋሚ ኮሚቴ የሕዝብ ደህንንት ጥበቃ ኃላፊዎች ደብዳቤ እንደፃፈ አስፍሯል።የአቡነ ቴዎፍሎስ ማመልከቻ ከሥርዓት ውጭ መታሰራቸውን እና የመንግስት አካኼድ የቤተ ክርስቲያንን ሕግ የሚፃረር መሆኑን የሚያሳኝ ነበር። አቶ መስፍን በቀለ ለአቡነ ቴዎፍሎስ መገደል የኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ተንኮል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ በዚሁ መጽሐፉ ላይ ይጠቅሳል፡፡

ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ በአቡኑ ላይ ያቀረበው  ሌላው ክስ ደግሞ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ እጃቸው አለበት የሚል ነው፡፡አቡነ ቴዎፍሎስ በጣሊያን ወረራ ወቅት አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያኖች ሲገደሉ እጃቸው ያለበት ስለመሆኑ የቀረበ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ አቡነ ጴጥሮስን እንዲገደሉ ለማድረግ የሚያነሳሳ ምንም ምክንያት የላቸውም። ምክንያት ቢኖራቸው እንኳ ያንን ለማድረግ አቅም የላቸውም። አቡኑ ከጣሊያን ወታደሮች ጋር የሚያገናኝ አንዳች ነገር የለም። ኮሎሌል ፍሰሐ ደስታ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ ያቀረቡት ሌላው ክስ “ለዲያቆናት እና ቀሳውስት የደመወዝ ጭማሬ ከልክለዋል፣ በዚህም ቅሬታ ቀርቦባቸዋል” የሚል ነው፡፡ይኼ በጣም አስቂኝ ቀልድ ነው፡፡ደርግ ራሱ መንግስትና ሐይማት የተለያዩ ናቸው ባለበት አፉ በቤተክርስቲያን የውስጥ አሰራር የሚገባበት ምክንያት አግባብ አይደለም፡፡ቅሬታ ቀርቧል ቢባል እንኳን አቡኑን ለመግደል የሚያደርስ አልነበረም። 

ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ የአቡነ ቴዎፍሎስን አሟሟት በተመለከተ ግርምንትን በሚያጭር መልኩ “…ፓትርያርኩ ለብቻቸው ታስረውበት ከነበረው የእድሚራል እስክንድርያ መኖሪያ ቤት (ብሔራዊ ቤተ መንግስት ውስጥ) አምልጠው እንደገና በመያዛቸው ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ በ1971ዓ/ም በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ከሌሎች ስምንት ሰዎች ጋር ተገድለው አስክሬናቸው ራስ አስራት ካሳ ግቢ መገኘቱ ተረጋግጧል” ይላል፡፡ ይኼ ታሪክ ይቅር የማይለው ወሸት ነው፡፡

እውነታው ሌላ ነው፡፡አበራ ጀምበሬ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ ፓትርያርኩን ከእስር ቤት አስወጥተው የወሰዱበትን ድባብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡”ፓትርያርኩ በሦስት መንፈሳዊ ልጆቻቸው ግራ ቀኝ ታጅበው፣ ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው፣ ካባቸውን ደርበው፣ አክሊል እንደደፉ፣ አርዌ ብረት እንደያዙ፣ ነጠላ ጫማ እንደተጫመቱ ሲሄዱ ፅዋ መስዋዕትነትን ለመቀበልና ሕይወታቸውን ለቆሙለት ዓላማ አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጁ እንጅ ምንም ዓይነት ሥጋት የሚታይባቸው አልነበሩም”ይላል። የአበራ ጀምበሬን ሃሳብ የሚያጠናክርልን ሌላ ማስረጃ አቶ መስፍን በቀለ “ስኳዶቹ- ገዳይ ጓዶች” ሲል 2011 ዓ/ም ያሳተሙት መፅሐፍ ነው፡፡ይኼ መጽሐፍ በገጽ 56 ላይ እንዲህ ይላል።

“…የሞቱን ውሳኔ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ስላሴ እንዲያስፈፅሙ ታዘዙ።… ኮሎኔል ተስፋዬ የአቡነ ቴዎፍሎስን የሞት ፍርድ ውሳኔ ባስቸኳይ እንዲፈፀምና መፈፀሙም በፍጥነት እንዲገለፅላቸው የማእከላዊ ምርመራ ድርጀት ሹም ለነበሩት ለሻለቃ (አሁን ብ/ጄኔራል) ለገሰ በላይነህ ትእዛዝ ሰጡ።ሻለቃ ለገሰም ውለው ሳያድሩ በጓድ ዘሪሁን አጋፋሪ በሚታዘዙ ወታደሮች ግድያው በልኡል አስራት ካሳ ግቢ እንዲፈፀም ጓድ ዘሪሁን አጋፋሪን አዘዙ። ጓድ ዘሪሁንም በታዘዙት ዕለት አቡነ ቴዎፍሎስን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በሚያዟቸው ወታደሮች አማካኝነት ግድያውን አስፈፀሙ። የቀብሩ ሥርዓትም በልዑሉ ግቢ ውስጥ ወዲያው ተከናወነ።”

የአቡነ ቴዎፍሎስ አፅም የት እና እንዴት ተገኘ?

የደርግ መንግስት ከተወገደ በኋላ በ1984 ዓ/ም የአቡኑን አፅም የሚፈልግ በአቡነ ባርናባስ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር፡፡ይኽ በእንዲኽ እንዳለ በአንድ ዕለት አማረ ደጀኔ የሚባል በደርግ ሰዓት ወታደር የነበረ ሰው የጡረታ መብቱን ለማስከበር ወደ ኮሎኔል አስራት አየለ (ኮሎኔል አየለ በኢህአዴግ የመጀመሪዎቹ ዓመታት የደህንነት ባለሙያ የነበረ ሰው ነው) ቢሮ ይመጣል፡፡በዚያን ጊዜ ኮሎኔል አስራት አየለ ወታደሩን   (አማረ ደጀኔን) ደህንነቱ የሚጠበቅለት መሆኑን ነግሮ በልዑል አስራት ካሳ ግቢ ውስጥ በደርግ ወታደሮች የተገደሉት ሰዎችን አስክሬን የተቀበረበትን ቦታ እንዲያሳይ ይጠይቀዋል፡፡ አማረ ደጀኔ ፍቃደኛ በመሆኑ ቀድሞ ተቋቁሞ ለነበረው ኮሚቴ እና ለአቡነ ቴዎፍሎስ ቤተሰቦች ተደውሎ አፅሙ በቁፋሮ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራስን መቻል ከፍተኛ ሥራ የሰሩ፣ ሐዋርያዊ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደረጉ፣ የኢትዮጵያንን ቤተ ክርስቲያን ከዓለም አብያተ ክርስቲያን ጋር ለማቀራረብ የተጉ፣የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትን ያጸኑ አባት ነሐሴ 4 ቀን 1984 ዓ/ም ሥርዓተ ፍትኅት ተደርጎ አፅማቸው በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴደራል በክብር አረፈ።

በታሪክ ድርሳናት የተመዘገበው እውነታ ይኼ ሆኖ እያለ ዶክተር ደረጀ ዘለቀ እና መሰሎቹ የአቡነ ቴዎፍሎስን ማንነት በመቀየር ብሎን ያልተገባ ክስ በማቅረብ ታሪካቸውን ጥላሸት ለመቀባት በከንቱ ቢደክሙም እኛ ልጆች የታሪክ ድርሳናትን ፈትሸን እውነታውን ለሕዝብ ከማድረስ አንቆጠብም።

Filed in: Amharic