>

በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየተፈጸም ያለው አፈናና እንግልት በአስቸኳይ ይቁም...!  (አለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ)

በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየተፈጸም ያለው አፈናና እንግልት በአስቸኳይ ይቁም…!

 አለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ) 


   የፈራሹ የደቡብ ክልል አመራሮች የጉራጌ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ በመመለስ ፋንታ በበርካታ የጉራጌ አመራሮች፣ የጉራጌ አባቶችና እናቶች፣እና የጉራጌ ወጣቶች ላይ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ገፈፉ ፣እስር፣ ድብደባና እንግልት እየፈጸሙ መሆኑ ተገልጧል፡፡

ቀድሞ በዞኑ በሕገ ወጥ መንገድ ከተሰማራው የኮማንድ ፖስት በተጨማሪ ሌላ ልዩ ኮማንድ ፖስት ወደ ዞኑ ተልኮ ከ200 በላይ ወጣቶችን አታሎ ለስብሰባ እንዲጠሩ በማድረግ ማሰሩ እና መግረፉ ተመላክቷል፡፡

ኢዜማን ወክለው በእዣ ወረዳ የደቡብ እና የዞኑ ም/ቤት አባል ሆነው የተመረጡት አቶ ታረቀኝ ደግፌም ሕዳር 17 ቀን 2015 ዓ/ም ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እና ያለመከሰስ መብታቸው በም/ቤቱ ሳይነሳ መታሰራቸው ተገልጧል፡፡

አቶ ሰንብት ነስሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ታሰረዋል ያለው አለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ) በአቶ ታረቀኝ እስርን አስመልክቶ ያቀረበው መግለጫ አግራሞትን የሚጭር ሆኖ አግኝተነዋል ሲል ወቅሷል፡፡

ሲጀመር አባሉ የታሰሩት የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ እንዲመለስ በመሞገታቸው ሆኖ ሳለ ይህንን ጥያቄያቸውን በመግለጫው ባላየ አልፎታል ሲልም የወቀሰው ማህበሩ “አባላት ከየትኛውም አይነት ህገ ወጥ ፀረ ሰላም ተግባር እራሳቸውን እንዲያርቁ ለማስገንዘብ እንወዳለን” ሲልም አሳስቧል፡፡

ኢዜማም ይሁን ሌሎች የጉራጌ ዞንን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቢያንስ የሕዝብ እንደራሴዎች ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን እንዲደግፉ፣ ባይደግፉ እንኳን የሕዝብ ጥያቄን ከማንኳሰስ እንዲቆጠቡ እንመክራለን ብሏል።

አለም አቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ) ሲቀጥልም:_

የብልጽግና መራሹ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ እንደ ቀይ መስመር ከነገርን ነጥቦች ውስጥ አንዱ ማንኛውም ሰው ያለ ሕግ አግባብ አይያዝም፣ አይታሰርም፣ ወዘተ የሚል ነበር፡፡

ይህ ግን ለፈራሹ የደቡብ ክልል አመራሮች የሚሰራ አይደለም፡፡ የፈራሹ የደቡብ ክልል አመራሮች ከጉራጌ ሕዝብ ጋር እልህ ተያይዘዋል፡፡ ሕዝቡን እኛ ያልንህን ካልፈጸምክ ውጤቱ ይኸውልህ እያሉት ነው፡፡

በመሰረቱ የፈራሹ የደቡብ ክልል አመራሮች ቀድሞውኑም ቢሆን የፈረሰው የሕወሃት ኢህአዴግ አመራሮች ስብሰብ ነው፡፡ አመራሮቹ የሚመሩት ድርጅት ስም እንጂ እነሱ አልተለወጡም፡፡

ለዚህም ነው በጉራጌ ሕዝብ ላይ ከ30 ዓመት ጀምሮ እየተሴረበት የነበረው የጉራጌን ሕልውና የማጥፋት ሴራ ይበልጥ አጠናክረው እያስቀጠሉ ያሉት በማለት በመግለጫው አስፍሯል፡፡

በመጨረሻም የሚከተሉትን አምስት ነጥቦች በማንሳት ጥሪ አድርጓል፦

1) የማዕከላዊ መንግስት እና የብልጽግና ፓርቲ የፈራሹ የደቡብ ክልል አመራሮች የጉራጌ ሕዝብን ሕልውና ከማጥፋታቸው በፊት የጉራጌ ዞን ሕዝብ ጉዳይ በማ ዕከል ደረጃ ተመርቶ እና ከሕዝብ ጋር ውይይት ተደርጎበት እልባት እንዲያገኝ፤

2) የጉራጌ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ በሕጉ መሰረት በሪፍረንደም እንዲወሰን እንዲደረግ፤

3) ከሕግ ውጪ የታሰሩ ወገኖቻችን ባስቸኳይ እንዲፈቱ፣እንግልትና ወካባ እንዲቆም፤ ከስራ ምድባቸው የተፈናቀሉ አመራሮች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፤

4) በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የታወጀው የኮማንድ ፖስት ባስቸኳይ ከዞኑ እንዲወጣ፣

5) በጉራጌ ሕዝቦች ላይ እንግልት እና አፈና እየፈጸሙ ያሉ የደቡብ ክልል እመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

የፌዴራል የፍትህና የሰብዓዊ መብት ተቋማትም በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየተፈጸም ያለው በደል እንዲቆም የበኩላቸውን እንዲወጡ አበክረን እንጠይቃለን፡፡ ይህንን እንግልት በየሚዲያዎቻቸው በመዘገብ ከሕዝብ እና ከፍትህ ጎን የቆሙ የሚዲያ ተቋማት እና ጦማሪዎች በሕዝባችን ስም ስናመሰግን በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

ሪፍረንደም ለጉራጌ ሕዝቦች የክልልነት ጥያቄ !

Filed in: Amharic