>

በኦሮሚያ ክልል በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ በአስቸኳይ ይቁም !! (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

በኦሮሚያ ክልል በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ በአስቸኳይ ይቁም !!

ቴዎድሮስ ሀይለማርያም

   1. የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥት

በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋና በሰሜን ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሸዋ የሚካሄደው የዘር ማፅዳት ያለከልካይ እየቀጠለ ነው። ከያቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጥቃቱ የሚፈፀመው በኦነግ/ሸኔ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል መደበኛ ኃይሎች ፣ ህዝባዊ ሚሊሻ ጭምር ነው።  የኦሮሚያ የክልልና የየአካባቢው መንግሥታዊ መዋቅርም የአማራ ነዋሪዎችን ከቀበሌ እስከ ወረዳና ዞን ድረስ አካባቢያቸውን ለቅቀው  እንዲወጡ  ከማስፈራራት ጀምሮ ፣  ለህዝቡ የደህንነት  ጥሪ ምላሽ ባለመስጠት ፣ በተቃራኒው የታጠቁ ኃይሎችን በግልፅ  በማገዝ ጭምር እየተሳተፉ ነው።

   2. የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች

የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች በመካከላችሁ  የተካረረውን አለመግባባትና የኃይል ግጭት በአማራ ደም ለመካስ የገባችሁበት  አረመኔያዊ ውድድር ነገ ተመልሶ  ለህዝባችሁ እንደሚተርፍ እወቁ።  ከገዥው ኦሮሞ ብልፅግና ጀምሮ ፣  ኦፌኮና ኦነግም ጭምር በተደጋጋሚ በግልፅ የጥላቻ ንግግሮችና  መግለጫዎች በማውጣት  ፣ በመሬት ላይም በየቅርንጫፎቻቸውና አባሎቻቸው የጥቃቱ አካል ከመሆን አልታቀቡም።  በተለይ የኦሮሞ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አማራን የማጥፋት  ዘመቻው ተሳታፊ  መሆኑ ግልፅ ነው።

   3. የኦሮሞ ህዝብ

ከቀደሙት ጥቃቶች በከፋ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ ከዳር ቆሞ ታዛቢነት ወደ ቀጥተኛ አማራን የማፅዳት ዘመቻ እየተሻገረ ነው። በወለጋ  ኪረሙ ፣ በደራና በምዕራብ ሸዋ  እንደታየው ህዝቡ ከዘረፋ ጀምሮ ነዋሪዎችን ለጥቃት በማመቻቸት እየተሳተፈ ነው።   የየአካባቢው የኃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጉዳዩን በዝምታ ይሁንታ ሰጥተዋል።   የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ ያላችሁ የእምነት ተቋማትና አባቶች  በጎቻችሁ በተኩላ ሲያልቁ ድምፃችሁን አላሰማችሁም።  የባለፈውን የወለጋ ጭፍጨፋ አጣራለሁ ያለው የኦሮሚያ መጅሊስ ራሱ የገባበት አይታወቅም። የኦሮሞ ምሁራንና ሌሎችም የሲቪክ ማህበራት ጥቃቱን ለማውገዝ እንኳን ባለመሞከራችሁ ይዋል ይደር እንጂ ከተጠያቂነት አታመልጡም።

   4. የፌዴራል መንግሥት 

የብልፅግና አገዛዝ በኦሮሞ ክልል የሚፈፀሙትን አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች  በቸልተኝነት እየተመለከተ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ በፓርላማ ነገሩን በማቃለልና በማጣጣል ፣ በሀገር መሪነት  የተጣለባቸውን ተቀዳሚ ኃላፊነት ሸሽተዋል። በዚህም የተነሳ ለጥቃቱ አስፈፃሚዎችና ፈፃሚዎች የእጅ አዙር ድጋፍ እንዳደረጉ ይቆጠራል። ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ፣ ምክር ቤቶችና ተቋማት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ህዝብን ለጥቃት አጋልጠዋል። በተለይ በህዝብ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን EBC ፣ አሚኮ ፣ ዋልታ ፣ ፋና ፣ ወዘተ በኦሮሞ ክልል የሚደረገውን መረን የለቀቀ የዘር ጥቃት በማፈን የዘር ማጥፋት ድጋፍ እያደረጉ ነው።

   5. የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች  

በአማራ ህዝብ የምትምሉ የምትገዘቱና የደም እንጀራ የምትበሉ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ፣ የህዝባችንን ሰቆቃና ችግሩን ዳር ቆሞ በማየት ከገዥው ያላነሰ ተጠያቂነት አለብን። የአማራ ክልልና አማራ ብልፅግና በተደጋጋሚ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው አማራ የሚደርስበትን ጥቃት ችላ በማለት ፣  እንዲያውም ከጭፍጨፋ ማግሰት የገዳዮች አለቆችን ካባ ለማልበስ በመሽቀዳደም ፣ ዛሬም በያካባቢው ለሚታረደው አማራ ኃላፊነት የለብንም ብለው ዝምታ ላይ ናቸው።  በተለይ ከተቃዋሚው ወገን የአማራ ህዝብ ድምፅ ለመሆንና ሰቆቃውን የማስቆም ትግሉን  ማስተባበርና መምራት የሚጠበቅበት አብን ፣  በውስጣዊው የብልፅግና ክንፍ በመታፈኑ  የቆመበትን ኃላፊነት እንዳይወጣ አድርጎታል። በሀገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ ያላችሁ  የአማራ ምሁራን ፣ የሲቪክ ማህበራትና ተቋማት በአንድነት ድምፃችንን ለማሰማት አለመቻላችን ህዝባችንን ታላቅ ዋጋ እያስከፈለውና ህልውናውን እየተፈታተነው ነው።

   6. መላው የኢትዮጵያ ህዝብ 

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዝምታውን መስበር ያለበት ወቅት አሁን ነው። በኢትዮጵያ  ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችና ተቋማት ፣ በኦሮሞ ክልል በአማሮች ላይ  የሚካሄደው የዘር ማፅዳትና የዘር ማጥፋት ድርጊት የሀገር ጉዳይ አድርገው አለመመልከታቸው አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። ነገ ይህ ጉዳይ በአማራ ላይ እንደማይቆምና ሁሉም ማህበረሰብና ክልል በየተራ እንደሚደርሰው ማሰብ አለበት። ጉዳዩ በአስቸኳይ ካልቆመ በመላ ሀገሪቱ ፅኑ የደህንነት ቀውስ ከማስከተሉም አልፎ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል እንደሚሆን አይጠረጠርም።

Filed in: Amharic