>

የጋዜጠኛ ደምስ በለጠ አራተኛ አመት ሲታወስ...!

የጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠ አራተኛ አመት ሲታወስ…!

አማራ ድምጽ


አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠ ጀግና ታጋይ፣ ደፋር፣ አይሰበሬ፣ ለአመነበት ነገር ሟች፣ ባለ ታላቅ ርዕይ፣ እንቁ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ልጅ ነበር።

ሁለገቡ ደምስ ለአንድያ ነፍሱ ሳይሰስት በለጠ ስለ ሀገር እና ስለ ወገን መጨነቅ ብሎም በተግባር ለውጥ እንዲመጣ በሚል መልካሙን ሁሉ በመመኘት ከባድ ተጋድሎ ካደረጉት በታሪክ እና በትውልዱ ልብ አይረሴ ከሆኑ ጀግኖች መካከል አንዱ ነው!

በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ ተጠናክሮ የቀጠለውን በሴራ እና በሸፍጥ የተሞላ መዋቅራዊ የጅምላ ፍጅትን በመቃወም ይቆም ዘንድ ከፍተኛ ትግል አድርጓል፤ እስከ መጨረሻዋ ሰዓትም እየታገለም ነበር።

የአማራ ድምጽ ራዲዮ (አድራ)ም ሆነ አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ሲነሳ የሌሎች አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ አሻራ ጉልህ ስለመሆኑ በብዙዎች የተመሰከረለት ጀግና ነበር።

አማራው በጎሳ በተከፋፈለች እና ለረዥም ጊዜ የጎሳ ፖለቲካ በተቀነቀነባት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ ዝርዑ/የተበተነ ሆኖ በጥላቻ እና በሀሰት ትርክት ደዌ ለሚሰቃዩት የእሳቤ ድሃዎች/የአራጆች መጫዎቻ መሆን የለበትም፣ ራሱን ማደራጀት አለበት፤ መድኃኒቱም እሱ ነው ብሎ በማመንም ታግሏል።

አማራ ራሱን ከገጠመው የህልውና አደጋ ለመከላከል ብሎም ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ጫፍ ረገጥ የከረረ ጥላቻ ያጎበጣቸው የተደራጁ እና የቡድን መሳሪያ ከታጠቁ ጅምላ ጨፍጫፊዎች ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ይታደግ ዘንድ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መክሯል።

ኤርትራ ድረስ በመሄድ ጫካ የነበሩ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር (ኢሕአግ) ታጋዮችን አግኝቶ አነጋግሮ፣ አበረታቶ፣ ስለትግሉ መረጃ ሰብስቦ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በማስተላለፍ ጥሩ የተስፋ ስንቅ እንዲሰንቁ በማድረግ ወደ አሜሪካ መመለሱ ይታወሳል።

ሁለገቡ ጀግና፣ ደምስ በለጠ በአዲስ አበባ ለቤተሰብ ጥየቃ እና አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)ን ለማቋቋም ከ32 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ በመጣ በሶስተኛ ሳምንቱ ታህሳስ 13/2011 ዓ/ም ምንም እንኳ ዝርዝር መረጃ ባይወጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በምግብ ምረዛ በተወለደ በ56 ዓመቱ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

ልክ የዛሬ 4 ዓመት ታህሳስ 15/2011 በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ፣ዘመድ፣የሙያ አጋሮች፣ የልዩ ልዩ አደረጃጀት አመራሮች እና በሽህ የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በተገኘበት ነበር ስርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ስለከፈልክልን ክቡር መስዋዕትነት እናመሰግናለን፤ በመልካም ስራህ በትውልዱ ዘንድ ስትዘከር ትኖራለህ!

ክብር ለሀገር እና ለወገናቸው ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው ለሰጡ ጀግኖች ይሁን!

Filed in: Amharic