>
5:21 pm - Friday July 21, 8800

ሆን ብሎ በተልእኮ የተሰነቀረ ወይስ የአገዛዙን ሞገስ ለማግኘት የተደረገ ንግግር (ከይኄይስ እውነቱ)

ሆን ብሎ በተልእኮ የተሰነቀረ ወይስ የአገዛዙን ሞገስ ለማግኘት የተደረገ ንግግር

ከይኄይስ እውነቱ


‹‹…በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አለ ብላ ታምናለች [የኢኦተ] ቤተ ክርስቲያን፤ ድጋፍም እየሰጠች ነው ያለችው፡፡ …›› – አቶ አያሌው ቢታኒ 

ምንጭ፤https://youtu.be/Fz-YG1Q91z0 (ከ4፡38 ደቂቃ ጀምሮ ማዳመጥ ይቻላል፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን የተላለፈ፡፡)

በመግቢያችን ላይ የተጻፈውን ቃል የተናገረው አቶ አያሌው ቢታኒ የተባለ የሕግ ባለሙያ እንደሆነ በኢኦተቤተክርስቲያን ቴሌቪዥን ሲነገር የሰማሁት ግለሰብ ሲሆን፣ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያለው ድርሻ ምን ይሁን በግልጽ ዐላውቅም፡፡ ወይም በቤተክርስቲያኒቱ ልጅነት/በምእመንነት ወይም በተቆርቋሪነት የተጋበዘ እንደሆነም መረጃው የለኝም፡፡ ለማንኛውም ንግግሩ የተላለፈበት ዓውድ አንድ ቤተክርስቲያናችንን ያወከ፣ አንደበቱ ያልታረመ፣ በእምነት ሽፋን የሚንቀሳቀስ፣ ከእምነት ይልቅ የፖለቲካ ተልእኮ ያለው፣ የወንጀል ሥርዓቱ የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖትን ለማጥፋት ባለው ተልእኮ ውስጥ ቀላል የማይባል ድርሻ ያለው፣ ያገር አፍራሹ ዐቢይ አፍቃሬ የሆነና ለተልእኮውም የሕዝብ ገንዘብ የሚበተንለት፤ የቤተክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት፣ ሥርዓት፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ ባህል፣ ታሪክ ባጠቃላይ የተዋሕዶ ሃይማኖትን ማንቋሸሽ የሙሉ ጊዜ ሥራው ያደረገ ዮናታን የሚባል ‹መናፍቅ› አስመልክቶ ቤተክርስቲያን ልትወሰድ ባሰበችው አቋምና ርምጃ ላይ በተጠራ ጉባኤ ላይ ከተደረገ መግለጫ መካከል የተወሰደ ነው፡፡ 

1ኛ/ የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ከግለሰብ ጋር እሰጣ ገባ ለመግባት ወይም በመልካም ንግግሮች ውስጥ እንከን ነቅሦ ማውጣትም ሆነ የግለሰብን ሰብእና ለመንካት ያለመ አይደለም፡፡ ባንፃሩም አገር በብልግናው ስለሚያውቀው ‹መናፍቅ› ለማውሳትም አይደለም፡፡ ይልቁንም በርካታ አድርባዮች በንግግራቸው ወይም በጽሑፋቸው ውስጥ በማር የተለወሰ ሬት ማቅረብን እንደ አንድ ማሳሳቻ/ማደናገሪያ ስልት እየተጠቀሙበት በመሆኑ፣ ሆን ተብለው የሚፈጸሙትን ካለማወቅ ወይም ከየዋህነት ከሚፈጸሙት መለየትና በጥንቃቄ መመርመር ስለሚገባ ነው፡፡ 

    በዚህ ረገድ አቶ አያሌው ቢታኒ ቤተክርስቲያናችንን በምን  ደረጃ ወክሎ ይሆን በጉባኤው ላይ የቤተክርስቲያኒቱ አቋም አድርጎ  ‹‹…በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አለ ብላ ታምናለች ቤተ ክርስቲያን፤ ድጋፍም እየሰጠች ነው ያለችው፡፡…›› ለማለት የበቃው? የቤተክርስቲያኒቱ ‹አባቶችም› አቋም በግለሰቡ የተገለጸው ነው? ወይስ አቅራቢው ነገር አማረልኝ በማለት በንግግር ሞቅታ የተነገረ? ወይስ ዜጎችን በነገድና በሃይማኖት ማንነታቸው ለይቶ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም የቆየንና እየፈጸመ ያለን፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይህንን ዘግናኝ አገራዊ ጥፋት የሚመራ የወንጀል ሥርዓት የቤተክርስቲያኒቷን አቤቱታ እንዲሰማ የቀረበ ገጸ በረከት? አቶ አያሌው የተናገረውን ያምንበታል? የማያምንበት ከሆነ ቀጥታ ወደ ፍሬ ጉዳዩ ገብቶ መናገር እየቻለ ማን አስገድዶት ነው በቤተክርስቲያናችን ሠርገው የገቡ የወንጀል ሥርዓቱ ወኪሎችን የነ ‹በላይን› እና መሰሎቻቸውን አቋም ለማስተጋባት የደፈረው? የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አጽራረ ቤተክርስቲያንን አጥፊዋን ትደግፋለች እያለን ነው አያሌው፤ ‹አባቶች› በተገኙበትና ቀንደኛ ‹መናፍቅን› አውግዞ ተገቢውን ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ በተጠራ ጉባኤ ምን እያለን ነው? ዛሬ ኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ እንኳን በሕዝብ የተመረጠ፣ እስከነ አካቴው ‹መንግሥት› የሚባል አካል አለ ወይ? የመንግሥትን ተፈጥሮና ባሕርይ እንዲሁም መሠረታዊ ተግባራት የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ይህንን ዓይነቱን የስንፍና ንግግር አይደፍርም ነበር፡፡ ቢያንስ የሚያስገድድ ሁናቴ በሌለበት ዝም ብሎ ማለፍ አይቻልም ነበር ወይ?

2ኛ/ ሌላው የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ‹መናፍቁ› ላይ ማናቸውንም ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ቆርጣ መነሳቷ ተገቢ ሆኖ ሳለ፤ ምእመኖቿ ዕለት ዕለት በተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይነታቸውና በነገድ ማንነታቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምባቸው አሁን በተንቀሳቀሱበት መጠን ከማውገዝ ጀምሮ ምን ዓይነት ተጨባጭ ርምጃዎች ወስደዋል? በጅምላ እየተጨፈጨፉ በጅምላ በግሬደር እየተዛቁ ስለሚቀበሩ ወገኖቻችንን ምእመኖቿን በማስተባበር ምን አደረገች? ሥርዓተ ፍትሐትና ተገቢ ቀብር እንኳን እንዲያገኙ አድርጋለች? የተጎጂ ቤተሰቦችን ከማፅናናት ጀምሮ ከወደቁበትና ከተበተኑበት ምድረ በዳ አንስቶ ለማቋቋም ምን ርምጃ ወሰደች? አገዛዙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ከሆነበት ቤተክርስቲያኒቷና ምእመኖቿ ላይ እያደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ጥፋት እንዲታቀብ በነውጥ ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ ምን አደረገች? የወያኔ/ሕወሓት ሆነ የወራሹ ኦሕዴድ/ኦነግ የወንጀል ሥርዓቶች የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖትና እና የዐምሐራ ሕዝብ ደመኛ ጠላቶቻችን ናቸው ብለው ላለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት በግልጽም በኅቡዕም፣ በዐደባባይም በጓዳም፣ በቃልም በመጣፍም በድርጊትም የማያበራ ቅስቀሳ እያደረጉና ጥፋት እየፈጸሙ መልሶ ዐላውያኑን (ከሃዲ አገዛዞችን)፣ መምዕላዮቹን (ፈላጭ ቆራጮችን) መማፃን ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ኧረ ሕዝብ ይታዘባል!!! እውን ቤተክርስቲያኒቷ እየተጨፈጨፉ ካሉ ምእመናን ምጽዋት የመጠየቅ የሞራል ብቃት አላት? እውን እውነተኛ አባቶች ካላችሁ የኖላዊነት (መንጋውን የመጠበቅ) ተግባራችሁን ባግባቡ ተወጥታችኋል? ልጆች ምእመናን የድርሻቸውን እንዲወጡ በቅድሚያ በሕይወት የመኖር ዋስትና ሊያገኙ አይገባቸውም? ሕይወታቸው በጭራቆች እየተነጠቀ፣ ቤት ንብረታቸው እየወደመ ለአውሬ ተጥለው እያሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ምንድን ነው? በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረ ሕንፃ እግዚአብሔር ከመፍረሱ የበለጠ የሚያሳስበን ምንድን ነው? የወንጀል ሥርዓቱ የሚፈልገው ሁከትና ብጥብጥ ስለሆነ በሚል ማስፈራሪያ ዐርፈን እንቀመጥ ነው መልእክቱ? ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ ሰው ወይም ተቋም ካልሆነ በቀር ሕግ፣ ዳኝነት፣ ፍትሕ አለ ወይ? በኢትዮጵያ ምድር ያለ ፍርድ ንጹሐንን መግደል አረመኔው ደርግ ካስተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ በመጠንም በዓይነትም ድርጊቱ እጅግ እየከፋ መጣ እንጂ የታገሠ ነገር አለ? እባካችሁ ግብዝነቱን እንተወው፡፡ በሰውም በአምላክም ዘንድ የትም አያደርሰን፡፡  ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት የሆኑት ዐቢይና ሺመልስ ተናብበው ለሚፈጽሙት ጥፋት ሽፋን የሚሰጡና ጥብቅና የሚቆሙ ሁሉ አጽራረ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ 

3ኛ/ በሦስተኛነት ላነሣ የምፈልገው ‹‹የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› ስለሚባለው ተቋም ነው፡፡ ይህ ድርጅት ዓላማው ምንድን ነው? ገለልተኛ ተቋም ነው? አገዛዙ በየቤተ እምነቱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ አመራሮችን በሚያነሣበትና በሚሰይምበት ሁናቴ ይህ የ‹እምነት ያልሆነ› ድርጅት አስፈላጊ ነው ወይ? የራሱን ቤተ እምነት ለማስጠበቅ ያልታመነ ስብስብ በጋራ ምን የሚፈይደው ተግባር ይኖራል? በወንጀል ሥርዓቱ ውስጥ የአገዛዙ ቅጥያና መጠቀሚያ ከመሆን ያለፈ ሚና ይኖረዋል ወይ? በእንደዚህ ዓይነት ተቋም ውስጥ አሁን ‹ችግር› ተፈጠረ ሲባል ራሳችንን እናገላለን ብሎ ከመዛት ከመነሻውስ ማኅበርተኛ መሆን ያስፈልጋል? ተቋሙ ፋይዳ አለው ተብሎ የሚታሰብ ከሆነም በቅድሚያ የወንጀል ሥርዓቱ እስነ ጐሣ ፖለቲካ ዝግንትሉ መወገድ አይኖርበትም? 

የአገር ዋልታና ካስማ የሆነች የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ያህል ታላቅ የሃይማኖት ተቋምን አቋም አስመልክቶ የሚተላለፍ ማናቸውም መልእክት በቅድሚያ በሚመለከተውና አግባብነት ባለው ኃላፊና ሲቀጥልም በጥበብና በማስተዋል ሊነገር ይገባል፡፡

Filed in: Amharic