>
5:26 pm - Wednesday September 15, 6641

ብአዴን፤ የወንጀለኛው ኢሕአዴግ ዘላለማዊ አሽከር (ከይኄይስ እውነቱ)

ብአዴን፤ የወንጀለኛው ኢሕአዴግ ዘላለማዊ አሽከር

ከይኄይስ እውነቱ


ለወንድም ዘመድሁን /ዘመዴ/፤

ይህንን ወንድማዊ አስተያየት የምጽፍልህ በዕድሜ እንደሚቀድምህ ወንድም እና እንደ አንድ የተዋሕዶ ልጅነትህ ነው፡፡ ከዘመነ ወያኔ ጀምረህ ወያኔ ወለድ የሆነውንና ኢሕአዴግ የሚባለውን በወንጀል የተጨማለቀ ሰይጣናዊ ቡድን በመታገል የሕዝብ ድምጽ በመሆን እያደረግኸው ስላለው ትግል ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ልበ አምላክ ቅ.ዳዊት የቤትህ ቅንዐት አቃጠለኝ ብሎ እንደተናገረው፤ አንተ ደግሞ ይህች መከራዋ ማባሪያ የሌለውን – ዱርዬዎች እየተፈራረቁ ሲያዋርዷትና የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ እያደረጓት የሚገኙትን – ጥንታዊትና ታሪካዊት አገራችን ኢትዮጵያ እና የሕዝቧ ጉዳይ አንገብግቦህ እውነቱን (ባንተ ቋንቋ ‹ነጭ ነጯን›) ለሕዝብህ ለማሳወቅ እንደተነሣሕ ይገባኛል፡፡ ይህንኑ አጋጣሚ ተጠቅሜ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከልቤ ላመሰግንህ እወዳለሁ፡፡ 

አክብሮቴና ምስጋናዬ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የግል አስተያየትህንና አመለካከትህን ማንፀባረቅህ ማንም የሚሰጥህና የሚከለክልህ ነፃነትና መብትህ አለመሆኑን ብረዳም፤ በጽሑፍም ይሁን በቃል በሚቀርቡ ባንተ ሐሳቦች ወይም አስተያየቶች ወይም አቀራረብና የቋንቋ አጠቃቀም ሁሉ እስማማለሁ ማለት አይደለም፡፡ ዝግጅትህና መልእክትህ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ከመድረሱ እና ብዙዎችም ባንተ ላይ እምነት ጥለው አገራዊ መረጃ ከማቀበላቸው አኳያ በበጎ ወይም በአሉታዊ መልኩ ተጽእኖ ልታሳድር እንደምትችል እረዳለሁ፡፡ አሉታዊ ያልሁት መረጃው የተሳሳተ ከሆነ ወይም አስተያየትህ ካገራዊ ጥቅሙ ይልቅ ብዙዎችን ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚመራ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡

ከፍ ብሎ የተመለከተውን በመግቢያነት ካልሁ፤ አሁን ወዳሰብሁት ርእሰ ጉዳይ በቀጥታ እገባለሁ፡፡ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ጠንቅ የሆኑና የኢሕአዴግ ፍንካች የሆኑ ሁለት አሸባሪ ድርጅቶች (ሕዝባችንን በገፍ ካስፈጁና ባገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት ካደረሱ በኋላ) – ወያኔ ሕወሓት እና ኦሕዴድ/ኦነግ – ፈጽመናል የሚሉትን የለበጣ ‹ሰላም ስምምነት› ተከትሎ ወደፊት በጋራ ሊፈጽሙት ላለው ጥፋት በየቦታው ‹ምክረ አይሁድ› ለመፈጸም በስብሰባ እንደተጠመዱ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚሁ የጥፋት ዝግጅት የነዚህ አሸባሪ ድርጅቶች ዘላለማዊው አሽከር የሆነውና የራሱ ሐሳብ ኖሮት የማያውቀው ብአዴን እና ሌሎችም ጭፍራ ድርጅቶች ተልእኮ ተሰጥቷቸው ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡ የወያኔን እና የወራሹን ኦሕዴድ/ኦነግ ባሕርይና አሠራር ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው (ፖለቲካ ተለዋዋጭ ቢሆንም እንኳን – እኛ አገር ውስጥ እየተካሄድ ያለውን ‹ፖለቲካ› ካልነው) በእነዚህ ሽብርተኞች እና በጭፍሮቻቸው የሚደረጉ ማናቸውም ድርጊቶች በጥርጣሬ ሳይሆን ካለማመን መጀመር ይኖርበታል፡፡ ከበቂ በላይ ተግባራዊ ምስክሮችና የሕይወት ተሞክሮዎች አሉንና፡፡ አንተም ዘመዴ ብአዴን የዐምሐራ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት መሆኑን እና ከዚህ ድርጅትና አመራሩ ምንም እንደማይጠበቅ ደጋግመህ ዝግጅት ማቅረብህን አስታውሳለሁ፡፡

ወንድማችን ዘመድሁን ‹‹የባሕርዳሩ ስብሰባ›› በሚል ርእስ በባሕርዳር የተደረገውን ስብሰባ አስመልክቶ የሚከተለውን ብሏል፤

‹‹…ሲጠቃለል፦ የትናንቱ የባህርዳር ስብሰባ ዐማራ አንድ ሁኖ የታየበት ስብሰባ መሆኑን ነው ታማኟ ወፌ የነገረችኝ። ዐማራ ክርስቲያን እስላም ሳይል፣ ጎንደር ጎጃም፣ ወሎ ሸዋ ብሎ በጎጥ ሳይከፋፈል። እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በዐማራዊ ወኔና ጀግንነት፣ ለሽመልስ ሳያጎበድዱ በድፍረት፣ በኃይልና በሥልጣን ሲሞግቱ ነው የዋሉት። ደግሞም ግዴታቸውም ነው። ከዚህ ውጪም ሌላ አማራጭ የላቸውም። ዐማራን ውሽልሽል ካቢኔ አያድነውም። ዐማራን የሚያድነው ዐማራነቱና እንዲህ ነቅቶ የፖለቲካ እና ኅልውናውን ለይቶ አንድነቱ ላይ አተኩሮ ከነፍጡ ጋር የተነሣ እንደሆን ብቻ ነው። ያኔ አይደለም ለራሱ ለምሥራቅ አፍሪካም ይተርፋል።››

በመቀጠልም፤ ‹‹እንደኔ እንደኔ ዐማራ አሁን አመራሮቹን ቀርቦ ማገዝ ያለበት ጊዜ ነው ባይ ነኝ። ብአዴንን በመስደብና በመግደል ነፃነቱን አታገኙምም ባይ ነኝ። በንስሀ አባት፣ በኡስታዝ በሼክ፣ በቤተዘመድ፣ በጓደኛ በዕድር፣ በእቁብ፣ በማኅበር ካቢኔዎቹን ቀርባችሁ ስለህልውናችሁ ብትወያዩ መልካም ነው። ››

ከፍ ብዬ ከጽሑፉ የወሰድኋቸውን ሐሳቦች/አስተያየቶች ሕዝብን ያዘናጋሉ ወይም በተበታተነም መልኩ የሚደረገውን ትግል አቅጣጫ ያስታሉ ብዬ ስለማምን፤ በትችትም ይሁን በምክር መልክ የሚከተለውን አስተያየት ለመሠንዘር እወዳለሁ፡፡

1ኛ/ ጽሑፉ ብአዴንን የዐምሐራው ተወካይ አስመስሎ አቅርቧል፡፡ ወያኔ በተከለው የጐሣ ሥርዓት የሚያምንና ለዚህ በተግባር ተባባሪ የሆነ ሁሉ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጠላት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የየትኛውም ነገድ ወይም ጐሣ አባል ነኝ ቢል ከፖለቲካ ነጋዴነት የዘለለ ትርጕም አይኖረውም፡፡ አዎ ወያኔ ‹ክልል› ብሎ በፈጠረው የጐሣ አገዛዝ ውስጥ ዐምሐራ የሚባል ግዛት ተፈጥሮ እነ ዐቢይና ሽመልስ በሪሞት ኮንትሮል የሚቆጣጠሩት ብአዴን የሚባለው የወያኔ ቅጥቅጥ በቅጥረኝነት የተሰየመበት ግዛት መኖሩን ዘንግቼው አይደለም፡፡ ባለፉት 32 የግፍና ሰቈቃ ዓመታት የዐምሐራ ሕዝብ ካገዛዙም ሆነ ከዛ ውጭ÷ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የራሱ ተወካይና አስተዳደር ኖሮት አያውቅም፡፡ ‹‹ከክልልህ ውጭ ማን ሂድ አለህ፤ ባለህበትም እንዳደረጉህ ዐርፈህ ተቀመጥ›› ተብሎ ባንድ ከአእምሮው በተለየ ሰካራም ብአዴን የተዘለፈ ሕዝብ ነው፡፡ ለእኔ ዐምሐራዊነት የደም ጉዳይ አይደለም፡፡ እነዚህ ጉዶች የማይወክሉት ከሆነ ደግሞ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ አንድ ሆኖ ቀርቧል የሚለው ትርጕም የለውም፡፡ ባጭሩ ዐምሐራ በክልል የሚታጠር ማንነት የለውም፡፡

2ኛ/ እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ የሚባለው አጋንንታዊ ቡድን ፍንክትካቾች የለየላቸው ነውረኞች ስብስብ መሆኑን ላንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል፡፡ በተለይም በጭራቁ ዐቢይ የሚመራው ኦነጋዊ ኦሕዴድ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ማናቸውንም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ በሆነበት በአሽከሮቹ ድራማ ማሠራት ለሱ የሚከብደው ይመስልሃል? እላይ እንደገለጽሁት ብአዴን ማሰቢያ ጭንቅላት በሌላቸው ነውረኞች የተሞላ ቡድን ነው፡፡ ከዚህ ቆሻሻ ቡድን የታቹ የላዩ ብዬ የምመርጠው የለኝም፡፡ እውነተኛ ለኢትዮጵያና ለዐምሐራ ሕዝብ የቆሙ ወገኖች ካሉ ከድርጅቱ ወጥተው ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቁና አሸባሪዎቹን በመታገል ያግዙት፡፡ የዚህ በድን ድርጅት ጭንቅላት ቀድሞ ወያኔ÷ አሁን ደግሞ ኦሕዴድ መሆኑን መሳት የለብንም፡፡ ተናገሩ የተባለውም የዐደባባይ ምሥጢር እንጂ እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእነርሱ ንግግር (እውነት ቢሆን እንኳን) የሚቀር ነገር ያለ ይመስልሃል? እነዚህ ነውረኞች ነገ የሚሠሩትን ታየዋለህ፡፡ 

3ኛ/ የዐምሐራው ሕዝብ ብአዴንን ከመቃብር ጠባቂነት ወደ ከርሠ መቃብር ማውረድ እንጂ በጅምላ አስጨፍጫፊውን የሚያግዝበት አንዳች ምክንያት የለውም፡፡ እነዚህ ቆሻሾች የሠሩት ግፍና በደል ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ በተለይም በየትኛውም ደረጃ ያሉ አመራሮችን ማጥፋት ቢያንስ በግፍና በገፍ ላለቁት ወገኖቻችን የፍትሕ ርምጃ ተደርጎ ሊታይ ይገባዋል፡፡ እንደውም እነርሱን በጎጠኝነት የሚያስታምም ካለ በእኩይ ተግባራቸው አባሪ ተባባሪ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡

4ኛ/ በንግግርህና በጽሑፍህ ሁሉ የታዘብሁትና ለወደፊቱ መስተካከል አለበት ብዬ የማምነበት አንድ ዐቢይ ጉዳይ ስለ ዐምሐራው ሕዝብም ሆነ ስለ ሌላ ጐሣ ስታወራ ራስህን ሦስተኛ ሰው ወይም ውጭ አድርገህ ነው፡፡ ያደመቅሁባቸውን አባባሎች እስቲ አንተው ታዘባቸው፡፡ 

‹‹እንደኔ እንደኔ ዐማራ አሁን አመራሮቹን ቀርቦ ማገዝ ያለበት ጊዜ ነው ባይ ነኝ። ብአዴንን በመስደብና በመግደል ነፃነቱን አታገኙምም ባይ ነኝ። በንስሀ አባት፣ በኡስታዝ በሼክ፣ በቤተዘመድ፣ በጓደኛ በዕድር፣ በእቁብ፣ በማኅበር ካቢኔዎቹን ቀርባችሁ ስለህልውናችሁ ብትወያዩ መልካም ነው። ››

ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እታገላለሁ ከሚል ወንድም በተለይም ከተዋሕዶ ልጅ ይሄ በፍጹም አይጠበቅም፡፡ በክርስትናው እምነት እኮ ሁላችን የአንድ የክርስቶስ ዘር ነን፡፡ አንዳንዴ ሳናስተውለው በወንጀል ሥርዓቱ የጐሣ ቅኝት እንወሰዳለን፡፡ ይህ አስተሳሰብ ይመስለኛል አንዱ ማኅበረሰብ የጐሣ ሥርዓቱ ተጠቂ ሲሆን ሌላው አይመለከተኝም (የዐምሐራው፣ የትግሬው ጉዳይ ነው) በሚል መዓቱ ደጃፉ እስኪመጣ እየተጠባበቀ የሚገኘው፡፡ ዛሬ ትርጕም አልባ የሆነውን ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚል ዝባዝንኬ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የንግግሩ ማሟሻ አድርጎታል፡፡ የወንጀል ሥርዓቶቹ ሥልጣናቸውንና ጐሠኛነቱን ለማጽናት ሲሉ በተቆጣጠሩት የሕዝብ መገናኛ ብዙኃኖች ዕለት ዕለት የሚያደነቊሩን እነዚህን በመሳሰሉ የጐሣ ሥርዓቱ የፈጠራቸው ኮተቶች በመሆኑ በሰዉም መፍረድ ይከብዳል፤ በተለይም በወንጀል ሥርዓቶቹ ጊዜ በተፈጠረው አዲሱ ትውልድ፡፡

ተረፈ-ነገር፤

በነገራችን ላይ ጉራጌ፣ ወላይታ ወዘተ. የምንለው እኮ ማኅበረሰብ-ፈጠር አስተሳሰብ እንጂ ከውልደት ያገኘነው ማንነት አይደለም፡፡ ከቋንቋና አብሮ ከመኖር የመጣ ባህል ያለፈ የጎላ ነገር የለውም፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረው እግዚአብሔር የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ‹‹ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር፡፡›› ነው የሚለው ቅዱስ ቃሉ (ዘፍ.1÷26)፡፡ አገራችን ውስጥ የበቀሉት የጐሠኛነት ጭራቆች አዳምና ሔዋንን የአንዱ ጐሣ አባል ከማድረግ ወደ ኋላ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ የሚገርመኝ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠበቃ ነኝ የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በሚገኙበት የነገድ ወይም ጐሣ ማንነት እኮራለሁ ሲሉ ስሰማ በእጅጉን ይገርመኛል፡፡ የጐሣ ማንት አይኮራምም፤ አያሳፍርምም፡፡ ምኑ ነው የሚያኮራው? ጥሮ ግሮ÷ ለፍቶ፣ ደጋ ወጥቶ ቆላ ወርዶ ያገኘው አይመስልም? ይሄም ሌላ የጐሠኛነት መገለጫ ነው፡፡ ወገኔ! የሚያኮራውስ ብሔራዊ ማንነት ነው፡፡ ለምን ብትለኝ እንደ የአገሩ ተጨባጭ ሁናቴ በሺህም ሆነ በብዙ መቶ ዓመታት እልህ አስጨራሽ ድካምና ጥረት – በፍቅር÷ በጸብ፣ በሰላም÷በጦርነት፣ በንግድ÷በፍልሰት፣ በትምሕርት÷በሕይወት ልምድ፣ በጋብቻ÷በጉዲፈቻ (በማር ልጅነት)፣ በባህል÷በልማድ፣ በእምነት÷በትውፊት፣ በሌሎችም ማኅበራዊ መስተጋብሮች – የተገነባ፣ የሚገነባና በማያቋርጥ የመገንባት ሂደት የሚቀጥል፣ ባንድነት የሚያስተሳስር፣ የአንድ አገር ባላገር የሚያደርግ፣ ወደ ሠለጠነ ዜግነት ከፍ የሚያደርግ፣ ወገኔ÷አለኝታዬ÷ጥላ ከለላየዬ÷ጋሻ መከታዬ የሚያሰኝ፣ በጋራ መልክዐ ምድር እና ሰንደቅ የሚገመድ የጋራ ማንነት ነውና፡፡ በዚህ የጋራ ማንነት ግንባታ ውስጥ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም የራሱ ድርሻ አለው፡፡ እኔ የለሁበትም የእነ እገሌ ነው በሚል ሕዝብን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የጭካኔ ጥግ ድረስ መሄድ፣ ተሠርቶ ያደረን አገር ማፍረስ፣ የሕዝቡን የጋራ እምነት÷ባህል÷እሤቶች÷ተቋማት ከሥር ለመንቀል የሚደረጉ የጥፋት ተግባሮች ሁሉ የማይጠገን ጉዳት ቢያደርሱም፣ ተምኔታዊ ወይም የቅዠት ‹አገሮችን› (‹ኦሮሚያ›ንም ሆነ ‹የትግራይ ሪፐብሊክን›) ሊገነቡ አይችሉም፡፡ 

በዓለማችን የሚገኙ አገሮች ብሔራዊ ማንነት ግንባታ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ የእኛን ብቻ የተለየ አድርጎ ለመሣል የሚደረገው አመለካከት የጐሠኞች ትርክት ነው፡፡ በብዙ መሥዋዕትነት አገራችንን በነፃነት ላቆዩልን የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ክብር ምስጋና ይድረሳቸውና እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የእኛ ከመነሻውም ከልዩነታችን አንድነታችንና የጋራ የሆኑ እሤቶቻችን ያመዝናሉ፡፡ ኢሕአዴጋውያን እንደሚተርቱት ከተለያዩ አገሮችና ከተለያየ ሕዝብ ወደ አንድነት የመጣን አይደለንም፡፡ የሀገረ-መንግሥትነት እና የአንድ ሕዝብነት ታሪካችን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ከጥንቱም በደም÷በጋብቻ÷በማኅበራዊ ሕይወት የተዋሐደና የተሳሰረ ሕዝብ ነው፡፡ ድንገት የተከሠተ ሳይሆን ሺህ ዓመታትን የዘለቀ ነው፡፡ ዛሬ በሥልጣኔ ማማ ላይ ሆና ‹የዓለም ፖሊስ› የሆነችው አሜሪካን (የተባበሩት የአሜሪካን ግዛቶች) ብንመልከት በዘር (በቀለም) እና በጐሣ ውጥንቅጧ የጠፋ አገር ነች ፡፡ በብዙ ማኅበራዊ ችግሮች ብትታመስም ዜጎቿ (ነጩ፣ ጥቁሩ፣ ላቲኖው፣ ስፓኒሹ፣ እስያው ወዘተ.) በአሜሪካዊነቱ የማይኮራ ዜጋ አይገኝም፡፡ መቼ ይሆን እኛ ወደ ቀልባችን የምንመለሰው?

Filed in: Amharic