>

« አንቺ ጎንደሬ፤ እንዳገርሽ እንዳገሬ »

ሰላም ጤና ከጎንደር! 

ጦቢያን በታሪክ ቴሌግራም

24 በረራ ነው ወደ ጎንደር ያለው ሲሉ ነበር። የዛሬ እና ትናንት ጭምር ይሁን የዛሬ ብቻ እንጃ ግን ቆሜ ሦስት አውሮፕላኖች ወደ ጎንደር በተመሳሳይ ሰዐት ሲጭኑ ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ የአየር መንገዱ ሲስተም በሙሉ ለ30 ደቂቃ ክራሽ አደረገ። ግን ኋላ እንደምንም አርገው ጭነው ላኩነ።

ወደ ወሎ ስንሄድ ብዙ ጊዜ ጋሽ አበራ ሞላን ወይንም ሐጂ ሙፍቲን ነበር የማገኘው። ወደ ጎንደር ፍቅራዲስ ናት ዛሬ አብራን የምትጓዝ። ጎንደር ስንገባ እሷን አይተው “እኔ አልገባኝም” የምትልበትን ዘፈኗን በሞንታርቦ ለቀው ተቀብለዋታል። አለፍ ስትል “ራያ አባ ስበር” ተከፈተ።

አጼ ቴዎድሮስ አየር መንገዱ አዘዞ ነው ያለው። (ፎቶ እዩ) በር ላይ እስክስ እያሉ ያማሩ ጎንደሬዎች ይጠብቁና አበባ ይሰጣሉ፤ ታክሲዎች ከዛ ፒያሳ ለመግባት ከ750 — 500 ብር ይጠሩና ልባችሁን ያወልቁታል። ባጃጅ 500 ይላል። ነዳጅ በብላክ 1 ሊትር 150 ብር ነው አሉ። የላሊበላዎቹ ትዝ ብለውኝ እንዲህ ከምከፍል በእግሬ እሄዳለሁ ብዬ መንገድ ስጀምር ሚኒባስ አግኝቼ የ20 ደቂቃ መንግድ 200 ብር ለመክፈል ተስማምቼ ገባሁ። ችግሩ ሌሎች 11 ሰዎች እስኪገቡ መጠበቅ ነበረብኝ። (ይሄ የተጻፈው በከፊል ሰው እየጠበቅኩ ነው።) ይሄኛው ሹፌር ግን “ነዳጅ 68 ብር ነው ግን 70 በዪው ሁለት ብር አይመልሱ” ብሎ እወነቱን ነገሮኛል። ጋቢና ሹፌሩ ጎን ሄጄ ቁጭ ብዬ ሬድዮ የለም ወይ ስለው ስልኩን ሬድዮ ከፍቶ እንዳይደብረኝ ሰጥቶኝ ሰው ላምጣ ብሎ ሄደ። ደግነት  (ሰርቃ ምትሄድበት የላትም ብሎም ይሆናል) 

ብርሃኑ ነጋ ገብቶ የዩኒቨርስቲ መምህራንን በከተራ ዕለት ጥዋት ሰብስቧል። እዛ ያሉ ወዳጆቼ እስኪመጡ የጎንደር ከተማን ሰፈሮች ዘርዝረልኝ ብዬ ሹፌሩን ሳስቸግር ነበር። እኚው: አዘዞ፣ ዳሽን፣ አምባሰል፣ ሽንታ፣ ቡልኮ፣ ፒያሳ፣ አውቶፓርኮ፣ ፋሲለደስ፣ ኮሎጅ፣ ማራኪ፣ ሸዋ ዳቦ (18 ቀበሌ)፣ ሪጋታ፣ ደሳለኝ፣ ግብርና፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ መዋኛ፣ የምሥራች፣ በጁረን፣ መስቀል አደባባይ፣ ፋሲል ግምብ፣ ጃን ተከል፣ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ አሮጌ መናኸሪያ፣ ቅዳሜ ገበያ፣ አዲስ አለም (የከብት ገበያ)፣ መስጊድ፣ ሸዋ ዳቦ፣ ገንፎ ቁጭ (አሁን አየር ጤና)፣ አዘዞ ካምፕ፣ ባህር ዳር መገንጠያ፣ አይራ ደም ባንክ፣ መዘጋጃ፣ አይራ ሆስፒታል፣ ፋሲል ኢንጂነሪንግ ዩኒ፣ አማኑኤል፣ አቡነ ሀራ፣ በጌምድር ት/ቤት፣ ፈንጠር (ሽፍታ ነው ወደዚያ አካባቢ ያለው ብሏል — ማንም አያስፈርሰንም ብሎ ፈንጠር ብሎ ሰው የሰፈረበት መሰል)፣ ህዳር 11 ት/ቤት፣ ጊዮርጊስ አደባባይ (ድሮ መስጊድ ሰፈር)፣ መምህራን ኮሌጅ፣ ተምቦላ ሰፈር፣ ቡሎኬት ሰፈር፣ ጎመን ጌ፣ ደረስጌ ማርያም ከዚያም ወደ ጎርጎራ መስመር፣ ግራር ጌ፣ መድዬ፣ ጭሎ፣ ቆሎ ድባ፣ ጃንጓ ማርያም፣ ጯሂት፣ ከዛ ጎርጎራ።

ሐምሌ 5 ጎዳናም አለ — በኮሎኔል ደመቀ related events ሳቢያ የተሠየመ። 🙂

መሃል ላይ ከ44ቱ አንዱን አዘዞ ተክልዬን አለፍን። ደህና ፎቶ የለኝም እንዳላሳያችሁ።

ጎንደር ከተማ ውስጥ ከፋሲል ግምብ የበለጠ ሕንጻ (ፎቅ) መሥራት አይቻልም። ይሄን ሁሉ እየነገረኝ መሃል ላይ “ሁለት ዐመት ልዩ ኃይል ነበርኩ፣ በኮሚቴ በሆስፒታል ተመለስኩ” አለኝ። የት ነበር ምድብህ ስለው “ጋሸና፥ ኸቆሰልኩ ወዲያ ኩል መስክ” ብሎ ወደ ላስታ ሀገራችን ከች አለ። “ገነተ ማርያም፣ ላሊበላ፣ ሀገር ወደዛ ነው። ለጦርነት የተፈጠረ እኮ ነው የሚመስለው ጋራው“ ብሏል ጎንደሬው ። የፍስሐ ሀገር እያልኩ ወረድኩ።

ላሁን በቃኝ። መልካም ከተራ

Filed in: Amharic