>

መርገመ ቴድሮስ (መስፍን አረጋ)

መርገመ ቴድሮስ

መስፍን አረጋ

እንደ ፋሲካ በግ፣ ሙክትና ሰንጋ

ቅርጫ ተቃርጠውሽ፣ የመሳፍንት መንጋ

መኳንንት ባላባት ሴታውል አንበልጋ(1) ፣

እየቦጠቦጡ በቆላ በደጋ

ሲግጡሽ አይቸ በጠባ በነጋ፣

እንዳተሞችብኝ፣ እንዳትሄጅ ባልጋ

ስለባባሁልሽ፣ ሆዴ ስለሰጋ፣

ፈልቅቄ በማውጣት ከነሱ መንጋጋ

ልታደግ ወስኘ የቀረሽን ሥጋ፣

በዚህ ውሳኔየ ቆርጨ እንድተጋ

ሚስት ገረድ ሁና ሳትለይ ከኔጋ

እንድታበራታኝ፣ እንድታረጋጋ፣

አምላክ የሰጠኝን ትልቂቱን ፀጋ፣

ይዤ ተዋበችን የኔይቱን ለግላጋ

በርሐ ገባሁን ፈንኘ(2) ልዋጋ፡፡

በመሳፍንት ዶማ፣ ዐንካሴ፣ ደንጎራ(3)

የፈራረሰውን የአንድነት ጎራ፣

ዳግመኛ ልክበው ስነሳ ከቋራ፣

እንቅፋቴ ሁሉ ጠፍቶ እስከሚጠራ

እባብና ዘንዶ፣ ጊንጥና ዳሞትራ(4)

ይነድፈኛል ብየ ቅንጣትም ሳልፈራ፣

ገብርየና ገልሞን አስከትየ ጭፍራ

ጠቅልን ኮልኩየ በርሬ እንዳሞራ

ፈጠኘ ደርሸ ከቀጠሮው ስፍራ፣

ጦርነት ገጥሜ በለበን ውጅግራ(5)

እያርበደበድኩኝ የጎጠኛን አውራ

ድል እመታሁኝ በተራ፣ በተራ

እያስተነፈስኩኝ የያንዳንዱን ጉራ፣

እንጨት ሳይቆረጥ ቤት እንዳይሠራ(6)

ሳልወድ በግዴ አንጀቴ እየራራ

ማጥፋት ነበረብኝ ያን ሁሉ ደንቀራ፡፡

ይሄን በማድረጌ ጸንተሽ እንድትኖሪ

ለወዳጅ ለጠላት እንድትጠነክሪ፣

ኢትዮጵያ ተብለሽ በስም ስትጠሪ

ክፉ እሚያስብሽን እንድታሸብሪ፣   

ሲገባሽ በክብር ስሜን ልትጠሪ

አንችን እንዳስከበርኩ እኔን ልታከብሪ፣

በተቃራኒው ግን በሱ ተጻራሪ

ሁነሽ ምሳጋናቢስ ውልታ እማትቆጥሪ፣

አሳድመሽበኝ ባንዳና መሠሪ

እናቴን ጨምረሽ ስላልሽኝ ብራሪ

ድኻ ፣ ምናምንቴ፣ ኮሶ ሻጭ ቸርቻሪ

ቀማኛ፣ ወንበዴ፣ ሽፍታ፣ አሸባሪ

ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ጽንፈኛ አክራሪ፣

ከልቤ አዝኘብሽ፣ ገጥሜ ባዝማሪ

ረግሜሻለሁ ይይልሽ ፈጣሪ፡፡  

ያደረ ለሆዱ፣ ለነጭ ፍርፋሪ

ከሃዲ፣ ጡት ነካሽ፣ ከጠላት መካሪ

እንግዴ ልጅ፣ ጭንጋፍ፣ ድባኖ(8) ፣ እራሪ፣

ክብረቢስ፣ ልክስክስ፣ ርካሽ፣ ቅራሪ፣

አተላ፣ አንቡላ፣ ፋንድያ፣ እዳሪ፣

አታላይ ቀጣፊ፣ ዋሾ አጭበርባሪ

የስልጣን ጥመኛ ሸፍጠኛ መሰሪ

ከዘርሽ አይጥፋ ይሁንብሽ መሪ፡፡

በንደዚህ ዓይነቱ ጸያፍ አስነዋሪ

ግምትምት ብለሽ፣ በራስሽ ስታፊሪ

አንገትሽን ደፍተሸ፣ ስታቀሪቅሪ፣

በጎጥ ተከፋፍለሽ ስትነቋቆሪ

በሰይፍ በገዠራ ስትመታተሪ

የልጆችሽን ደም ስታንዠረዥሪ፣ 

ሬሳ እየገፋሽ በመንገድ ቆፋሪ

ከውሻ አሳንሰሽ ጅምላ ስትቀብሪ፣ 

ያኔ ተጸጽተሸ እያልሽ ኡኡ እሪ

ውለታየን ቆጥረሽ እንድትዘረዝሪ፡፡

በቁም ተማርኬ በነጭ ፊታውራሪ

ለተተኪው ትውልድ ዋና አስተዳዳሪ

አልሆንም በማለት ፍራት አስተማሪ፣

ጀርባየን ሳላሳይ ለንግሊዝ ወራሪ

እንደጠበኩ ክብሬን አንጡራየን(9) ቀሪ፣

ፎክሬ አቅራርቸ በሰንጎ ደርዳሪ

ጎርሸ ጥይቴን፣ የሽጉጤን አብሪ

ያረፍኩበትን ቀን እንደታጠኩ ሱሪ

ሁልጊዜ በያመት እንድትዘክሪ፡፡ 

እፍረት ባይኖርሽም፣ ይሉኝታም ባታቂ

እስኪ መልሽልኝ፣ ባጭር ተጠየቂ?

በጥቁር መዲና ባዲስ አበባ ላይ

በተሰየመልኝ ኢምንት አደባባይ

የሚያልፈው ጎዳና ተንጣሎ የሚታይ፣

ጥቁርን በሚንቀው በዘረኛው እኩይ

እንዴት ይሰየማል በንግሊዙ ጠቅላይ?

መርገመ ቴድሮስን አልበላውም ዳዋ(10)

ጦቢያን ሊያራቁታት ሊያደርጋት አሸዋ፣

አባቱ ጠጥቶ በሰላቶ ጽዋ

ዜናዊ አበቀለ መለስን ባድዋ፣

ቅጠሉ መረራ መርዘኛ ግራዋ

በግንዱ ጠምጥሞ ሐረገ ዋልዋ

አድጎ ተንሰራፍተ የደረሰ ሺዋ(11) ፡፡ 

ቀጠለና ደግሞ ፈዋሽ መስሎ ቀርቦ

ዐብይ ተተካ የመለስ ተስቦ፡፡

መደመር እያለ ቃሉን ብቻ ክቦ

በጎጥ የሚቀንስ በክልል ቀንብቦ

እኛን የሚያከሳ ኬኛን አደልቦ፡፡

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ

አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ

ደባ እየፈጸመ የሚሰብክ ደቦ(12)፡፡

እንዴት ቢረግማት ነው ቴውድሮስ አምርሮ

ጦቢያ ያበቀለች ጭራቅ በአጋሮ? 

ምንስ ቢከፋ ነው የቴወድሮስ መርገም

ጦቢያን የሚገዛት ኦነጋዊ እርጉም?

የቃላት መፍቻ

  1. አንበልጋ፡ ፈሪ፣ ሥራ ፈት፣ ሴታውል፡፡
  2. ፈነነ፡ ወዶ ዘመተ፡፡  ፋኖ ማለት ደግሞ ወዶ ዘማች ማለት ነው፡፡
  3. ዐንካሴ፡ በቀጭን በትር ጫፍ ባንድ በኩል የተዋደደ ሹል ብረት፣ ያንካሴ የወላሴ እንዲሉ፡፡   ደንጎራ ማለት ደግሞ ከጫፉ ማረሻ የመሰለ መቆፈርያ የተዋደደበት አጣና ማለት ነው፡፡  
  4. ዳሞትራ (black widow)፡ የሚናደፍ መርዛማ፣ ባለጠጉር ክሰልማ ሸረሪት፡፡
  5. ለበን፡ ዘጠኝ ጎራሽ ነፍጥ፣ ጠመንጃ፡፡  አጭር ለበን፣ ረዥም ለበን እንዲሉ፡፡  ውጅግራ ወይም ውዥግራ (fushigi) ደግሞ ሌላ ዓይነት ነፍጥ ነው፡፡
  6. አብናቶቻችን (ማለትም አባቶቻችን እና እናቶቻችን፣ forebears) እንደሚሉት፣ እንጨት ሳይቆረጥ ቤት አይሠራም፡፡  ስለዚህም ሀገር የሚባል የፈራረሰ የጋራ ቤት ሲሠራ፣ አያሌ እንጨት እየተቆረጠና እየተፈለጠ፣ እየተጠረበና እየተላገ መስዋት ይሆን ዘንድ የግድ ነው፡፡  ቤቱ የበለጠ የፈራረሰ ከሆነ ደግሞ፣ መስዋእትነቱም በዚያው ልክ የከፋ ይሆናል፡፡  ስለዚህም፣ ይህ መስዋዕትነት ሌላ ምንም ሳይሆን የግድ መሠራት ያለበት የጋራ ቤት ሲሠራ የሚያስከትለው አይቀሬ መዘዝ (inevitable consequence) ወይም ተጓዳኝ ጉዳት (collateral damage) ነው ማለት ነው፡፡  
  7. ድባኖ፡ አጭር፣ የደበነ፣ ዝንብ አከል፡፡
  8. አንጡራ (ኦሮምኛ)፡ ሰው ለፍቶ፣ ደክሞ፣ ጥሮ፣ ግሮ ያገኘው ሐብት፣ንብረት፡፡
  9. ዳዋ፡ ጥሻ፣ ሣር፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ክረምት አፈራሽ፡፡  መናኝ ዳዋ ለብሶ፣ ጤዛ ልሶ፣ ዲንጋ ተንተርሶ ይኖራል  እንዲሁም ዐይጥ በበላ ዳዋ ተመታ አንዲሉ፡፡ 
  10. ሺዋ (ሺሕ፣ ሺኋ)፡ የሴት ስም፡፡  የግሼ ባላባት ያገባት የቤታማራ (ወሎ) ባላባት ሴት ልጅ፡፡  ብዙ ልጆች ስለወለደች፣ አባቷ ልጀ ሺኋ (ሺ የሆንሽው ልጀ) አላት፡፡  በዚህ ምክኒያት የልጆቿ አገር ሺዋ ተባለ፡፡  አለቃ ደሰታ ተክለወልድ፣ ዐዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 1217፡፡ 
  11. ደቦ፡ ብዙ ሰው ተሰባስቦ በሕብረት የሚሠራው ሥራ፡፡  ሌላኛው ስሙ ጅጊ ነው፡፡  

መስፍን አረጋ 

mesfin.arega@gmail.com                   

Filed in: Amharic