>

የአብይ አህመድ ሽንገላና መሰሪ ተንኮል (ግርማ ካሳ)

የአብይ  አህመድ ሽንገላና  መሰሪ ተንኮል

 ግርማ ካሳ

አብይ አህመድ ብጹህ አባታችን ፓትሪያርክ አቡነ ማቴያስን፣ ፓትሪያርክ  ብሎ ለመጥራት እንኳን አልፈለገም፡፡ ያው የሽንገላ ውዳሴ በማቅረብ፣ ለሌሎች የሲኖዶስ አባላት፣  ከአቡን ማቴያስ ተማሩ ለማለት ነው የሞከረው፡፡ ይህ እጅግ በጣም አደገኛ፣ ሰውዬው እጅግ በጣም መሰሪ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ተመልከቱ፣ የሲኖዶሱ ሰብሳቢ፣ የኦርቶዶስክ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቴያስ ናቸው፡፡ መፈንቀለ ሲኖዶስን አስመልክቶ በይፋ ሶስት ጊዜ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች ሲያሳልፍ  እርሳቸው በመሩት  ስብሰባና ሱባዬ ውሳኔዎችን ያሳለፈው፡፡ 

እዚህ ጋር አብይ አህመድ ግን ፓትሪይርኩን ከሲኖዶሱ ለመለየት ነው የሞከረው፡፡ ሲኖዶሱን ለመከፋፈል በሚል ነው ይህ አይነት ርካሽ ሰይጣናዊ አባባሎችን የተጠቀመው፡፡

ትላንት ህወሃቶችን ጁንታና የቀን ጅብ ሲላቸው ነበር፡፡ ትላንት የትግራይ ህዝብ under siege በማድረግ፣ በከበባ ውስጥ በማስገባት፣ ለመከራና ለስቃይ እንዲዳረግ ሲያደርግ ነበር፡፡ ትላንት የትግራይ ህዝብ ቄሱ  ሳይቀር ተነሳብን ብሎ ህዝብን በጅምላ ሲወነጀል ነበር፡፡ ትላንት በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ተጋሩን በማንነታቸው ብቻ በአዲስ አበባ አፍኖ ሲያስር ነበር፡፡ ትላንት ፓትሪያርክ አቡን ማቴያስ እንዳይናገሩ አግዶ፣ የቁም እስረኛ አድርጓቸው ነበር፡፡ ትላንት በነ አቶ ዳንኤል ክብረት በኩል በተጋሩ ላይ እርግማንና ዛቻ ሲያወርድ ነበር፡፡ ትላንት በአገር ላይ  ራሱ ለፈጠራቸው ችግርችና  ቀውሶች ተጋሩ ላይ ጣቱን ሲቀስር ነበር፡፡  ትላንት እርሱ በሚመራት አገር ከ600 ሺህ ተጋሩ ሕይወታቸው እንደ ቀላል ነገር እንዲረግፍ ያደረገ ነው፡፡

አሁንም ደግሞ ከህወሃቶች ጋር ሲስማማ: ህወሃቶች ለስልጣኔ ያስፈልጉኛል ብሎ ሲያስብ፣ የነርሱን ታማኝነት ሲያገኝ: ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆይ፣ የርስዎን አመራር እንቀበላለን፣ በእግሮችዎት ስር እንቀመጣለን” የሚለውን የህወሃቶች ቃል ሲሰማ፣  ለርሱ አሁን ያለ ተጋሩ ሰው የለም፡፡  ፓትሪያርኩን ማወደስና ማሞካሸትም ጀምሯል፡፡ ከህወሃት መሪዎች ጋር ታንጎ እየደነሰ ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ አቡነ ማቴያስን አስመልክቶ ያለኝ አመለካከት ተቀይሮ የማያውቅ ነው፡፡ በጣም የማከበራቸው፣ የምወዳቸው እጅ በጣም ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ አብይ ሳይመጣ በፊት፣ አቡና ጳውሎስ ከሞቱ በኋላ፣ ቤተ ክርስቲያኗ አንድ እንድትሆን ያደረጉት ስራ አስደናቂ ነው፤፡ በርሳቸውም ጥረት ነው የተከፈለችው ቤተ ክርስትያን አንድ የሆነችው፡፡ ያኔ ሲያደርጉት የነበረውን በመግልጽ በርካታ ጊዜ አድናቆቴን ጽፊያለሁ፡፡ ማንበብ የሚፈልግ መልሶ ከስድስት ፣ ሰባት አመታት በፊት የተጻፉት ሄዶ ማየት ይችላል፡፡

ሁሉም ነገር ካለቀና ከተጠናቀቀ በኋላ ነው አብይ የመጣው፡፡ የመጨረሻ ዝግጅቶች ላይ በመገኘትም ፣ ከአምስት አመታት በላይ የተደረገ ጥረት፣ በአንድ ሳምንት የተደረግ ይመስል፣ credit ለመውሰድ የሞከረው፡፡ እርሱ ያልሰራዉን፣ ሌሎች የሰሩትን ነው እንግዲህ እየጠቀሰ ለኦርቶዶስክ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ነገር አድርጊያለሁ እያለ እየተመጻደቀ ያለው፡፡

Filed in: Amharic