>

ዉሀ ለጠየቀ ጥይት?!?

ዉሀ ለጠየቀ ጥይት?!?

በወልቂጤ ከተማ 3 ሰዎች ተገደሉ    12 ሰዎች ከባድ  የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል …!

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ 

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የንፁህ ዉሃ ችግር እንዲቀረፍ ባዶ ጀሪካን ይዘዉ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው ቢያንስ ሶስት ሰዎች ህይወታቸዉ አልፏል።

በተጨማሪም 12 የሚሆኑ ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል። 

በወልቂጤ ከተማ ትላንት ከተፈጠረዉ ግጭት በኃላ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በከተማዋ የዉሃ አቅርቦት ችግርን አስመልክቶ ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘታቸው የዉሃ ልማት ቢሮ በመሄድ ድምፃቸዉን በማሰማት ላይ እያሉ በደቡብ ክልልና በከተማዋ የፀጥታ ኃይሎች በአስለቃሽ ጭስ እንዲበተኑ እና ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የካቲት 8/2015 ሁለት ግለሰቦች በጥይት ከተመቱ በኋላ ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰዱ ቢሆንም ወዲያውኑ ህይወታቸዉ ሲያልፍ ሌላ አንድ ግለሰብ በፀጥታ ኃይሎች በተከፈተዉ ተኩስ ወደ ህክምና ተቋም ሳይወሰድ በቦታው ህይወቱ አልፏል ተብሏል።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የሆስፒታሉ ነርስ “በዩኒቨርስቲዉ ሪፈራል ሆስፒታል በ12 ሰዎች ላይ የተለያዩ መጠን ያላቸዉ ጉዳቶች ሲደርሱም አሁን ላይ አራት ታካሚዎች በአስጊ ሁኔታዎች ዉስጥ ይገኛሉ፤ ሌሎቹ ግን ህክምና ተደርጎላቸዉ ወደ ቤታቸዉ ተመልሰዋል” በማለት ተናግራለች።

በስፍራዉ እንደነበረ የገለፀው ኑረዲን ጀምበል የተባለ ነዋሪ “አሁን ጥያቄያችን በቀጥታ ረጅም ርቅት ተጉዘን የምናገኘዉ እና ከአራት እስከ ስድስት ወራቶች ጠብቀን ዉሃ እንድናገኝ በመደረጋችን ከዛሬ ነገ ምላሽ ያገኛል ብለን ተስፋ ያደረግን ቢሆንም ሳይሆን ቀርቷል” ብሏል።

የአይን እማኙ “ባዶ ጄሪካን ይዘን ሰልፍ ወጥተናል” ነገር ግን “የተሰጠን ምላሽ ተኩስና በወጣቶች ላይ ድብደባ ነበር” ሲል ተናግሯል። 

የጉራጌ ዞን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የክልልነት ጥያቄያችን ይመለስልን በሚል የቤት ዉስጥ መቀመጥና የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸዉ የሚታወስ ሲሆን  የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በዉሃ እጦት ምክንያት ለችግር ተጋልጠናል በማለት ትላንት በተፈጠረዉ ግጭት ምክንያት በከተማዋ የንግድና የሰዉ እንቅሳሴ ከማለዳዉ ጀምሮ ተዘግቷል ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረገዉ ጥረት አለመሳካቱን በመግለጽ የዘገበው አዲስ ዘይቤ ነው።

Filed in: Amharic