>

የዲሞክራሲ ትግሉ አርበኛ የፅናት ተምሳሌቱ እስክንድር ነጋ በእገታ ላይ ይገኛል (ባልደራስ መግለጫ)

የዲሞክራሲ ትግሉ አርበኛ የፅናት ተምሳሌቱ እስክንድር ነጋ በእገታ ላይ ይገኛል

ባልደራስ መግለጫ  

ከቤተሰቡና ከግል ምቾቱ በላይ ለሃገሩ እና ለህዝቡ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ቋሚ ባህሪው የሆነው ታላቁ እስክንድር ነጋ በኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥት ያላቋረጠ ውትወታ፣ በቡሬ ዳሞት ወረዳ አካባቢው በተሰማሩ ሆድ አደሮች ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታወቀ። የፅናት የመጨረሻው ተምሳሌት የሆነው፣ የባልደራስ ፓርቲ መስራችና መሪ በመሆን እስከ ሐምሌ 16 /2014 ዓ.ም- ድረስ ያገለገለው እስክንድር ነጋ የካቲት 17 /2015 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ አካባቢ በመተላለፍ ላይ እንዳለ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ሊያዝ መቻሉን ከአንዳንድ የአካባቢው መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

እስክንድር በተያዘ ጊዜ አመሻሽ ላይ ስለነበር በእለቱ በቡሬ ከተማ ማረሚያ ቤት እንዲያድር ተደርጎ የዚያኑ እለት ሌሊት ዜናው ለምእራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር እና ለዞኑ የፖሊስ መምሪያ ብሎም ለባህርዳር የክልሉ አስተዳደር እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በጠዋት ወደ ባህርዳር እንዲላክ በመጠየቁ፣ በፓትሮል ታጅቦ ወደ ባህርዳር እንዲሄድ መደረጉን ለመረዳት ተችሏል። በባህርዳር ከተማ ሳያድር በክልሉ የፀጥታ እና ደህንነት አማካሪ ትእዛዝ፣ በሌሎች የአማራ ክልል ባለሥልጣኖች ዝም ባይነት ከባህርዳር ታጅቦ ወደ አዲስ አበባ በመኪና እየተጓጓዘ እያለ ደጀን ሲደርስ ወጣቱ፣ የአካባቢው ህዝብ እና አንዳንድ የክልሉ የፀጥታ አካላት የእስክንድርን ለብልፅግና መንግሥት ተላልፎ መሰጠት በመቃወማቸው ደጀን ላይ በህዝቡ ግፊት ጉዞው መገታቱን ከአካባቢው የተገኘ መረጃ አረጋግጧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት እስክንድርን ለኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥት አሳልፎ በመስጠትና ባለመስጠት መካከል እየዋለሉ ይገኛሉ፡፡ 

አቶ እስክንድር ነጋ በቡሬ የወረዳ ከተማ አካባቢ እንዳለ ጥቆማ የደረሳቸው የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች  አለበት ወደተባለው ቦታ በአስቸኳይ በማቅናት ይዘውና በፓትሮል መኪና ላይ ጭነው ወደ ቡሪካ ከተማ ማረሚያ ቤት በወሰዱት ጊዜ ከሚያነባቸው መፅሐፍት እና ከመፅሐፍ ቅዱስ በስተቀር በእጁ ላይ ምንም የተለየ ነገር እንዳልተገኘ ከማረሚያ ቤቱ አካባቢ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

ከስምንት ወራት በፊት አቶ እስክንድር ነጋ ከባልደራስ ፓርቲ መሪነት እና አባልነት የለቀቀበትን ሁኔታ ባለቤቱ ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል በ18/06/15 ለሚዲያ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ላይ ባለቤታቸው  ባልደራስን እና አዲስ አበባን ትቶ ለመሄድ የተገደደው የኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥት በሕይወቱ ላይ አደጋ ለማድረስ ተጨባጭ የሆነ እቅድ እንደነበረው ስለተገነዘበ እና ሁኔታዎች መሻሻል እስኪያሳዩ ድረስ እራሱን ከከተማ አርቆ የጥሞና ጊዜ በመውሰድ ኑሮውን በገጠር ለመግፋት በመወሰኑ እንደሆነ ገልፃለች።

የህሊና እስረኛው እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሰፍን የሚችለው በሰላማዊ ትግልና በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው ብሎ የሚያምን፣ ከሰላማዊ ትግል ጋር የቆረበ የዲሞክራሲ ትግል አርበኛ ነው።

አቶ እስክንድር ነጋ በቡሬ ዳሞት ወረዳ ከመያዙ በፊት በኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በኩል  ይህንን ወይም ያንን ህገ ወጥ ተግባር ስለፈፀመ በህግ ይፈለጋል የሚል ክስ አልቀረበበትም፤ የፍርድ ቤት መጥሪያ አልተቆረጠበትም፤ የማደኛ ትእዛዝ አልወጣበትም፡፡  ስለሆነም በነፃነት በአመቸው የሀገሩ አካባቢ የመንቀሳቀስ መብቱ ያልተገፈፈ ነፃ ዜጋ ስለነበር እንቅስቃሴውን የሚገታበት ምክንያት አልነበረውም። የኦሮሙማው የብልፅግና መንግሥት አሁን በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ የተለመደ የሃሰት ክሱን እንደሚደረድር ቢገመትም፣ ለእስክንድር በሃሰት መታሰር አዲስ ሳይሆን፣ ለበርካታ ጊዜ በመደጋገም የተፈፀመበት እና አሁንም እየተፈፀመበት ያለ የመንግሥት ቋሚ ተግባር ነው።

እስክንድርን ለእስራት ያበቃው ምክንያት በአንድ በኩል የኦሮሙማው መንግሥት ተሸፋፍኖት የነበረው የኢትዮጵያዊነት ገፀ ባህሪ ከትወና ያላለፈ መሆኑ ገሃድ በመውጣቱ እና በአደባባይ በመጋለጡ፣ የብልፅግና የፖለቲካ ተቀባይነት ጀምበር እየጠለቀች በመሄድ ላይ መሆኗ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የእስክንድር በሃቅ ላይ የተመሰረተ የዲሞክራሲ ታጋይነቱ በህዝብ ህሊና ውስጥ  በከፍተኛ የፖለቲካ ተቀባይነት ማማ ላይ ያስቀመጠው መሆኑን ብልፅግና በመገንዘቡ፣ ይህ ግንዛቤ የፈጠረበት ፍራቻ እያየለ በመምጣቱ ነው። የእውነተኛውና የሀቀኛው የዲሞክራሲ ታጋይ እስክንድር ነጋ እስር ፍፁም ህገ ወጥ ስለሆነ ለመብቱ መከበር ሲታገልለት እና ከባድ መስዋእትነት ሲከፍልለት በርካታ ዓመታትን በእስር እና በእንግልት ማሳለፉን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የአዲስ አበባ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አንድነት እንደታገለው ሁሉ  ለእስክንድርም  በአንድነት ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊያሰማና ከእገታው እንዲለቀቅ ሊጠይቅ ይገባል። እንዲሁም የአማራ ክልል ህዝብ የጀመረውን ትግል በመቀጠል እስክንድር ከአፈናው ተላቆ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ፣ ትግሉን ይበልጥ አበርትቶ ዳር እንዲያደርሰው እንጠይቃለን፡፡   

የዓለምአቀፍ ማህበረሰብ እና በብልፅግና መንግሥት ላይ ከባድ ተፅእኖ በማሳረፍ የታወቀው፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው የምእራቡ ዓለም መንግሥታት በተለይም የአሜሪካን መንግሥት  እስክንድር በነፃ ሀሳብን በማሰራጨት ባደረገው አስተዋፅኦ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆኑን፣  የሰላማዊ እና የዲሞክራሲያዊ ትግል ቀንዲል መሆኑን በመገንዘብ፣  ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የኤምባሲ ተወካዮቻቸው አማካይነት፣ የዓለም አቀፍ እና የሃገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተወካዮች እስክንድር የታገተበት ሁኔታ ህገ ወጥ መሆኑን ተረድተው እሚገኝበት ቦታ ድረስ ሄደው በመጎብኘት የተያዘበት ሁኔታ ሰብዓዊነት ያልተለየው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

በዚሁ አጋጣሚ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች የሆኑት ስንታየሁ ቸኮልና ታዲዮስ ታንቱ ጉዳያቸው ያለአግባብ መጓተቱ ቀርቶ የህግ ሂደቱ በተፋጠነ ሁኔታ እየታየ ፍትሃዊ ፍርድ እንዲያገኙ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጠው እና ግፊት እንዲደረግ ፓርቲያችን ያሳስባል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

የብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም.

Filed in: Amharic