>

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን የበዓላት በኵር - ዓድዋ (ከይኄይስ እውነቱ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን

የበዓላት በኵር

ዓድዋ

ከይኄይስ እውነቱ

ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን መቼ ነው ብለው ሲጠይቁን በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው የዓድዋ ድል በዓል ብለን በኩራት በአፍም፣ በመጣፍም፣ በተግባርም መንገር፣ ማስተማር ይኖርብናል፡፡

ሐሙስ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያውያን፣ የአፍሪቃውያን እና የጥቁር ሕዝቦች ባጠቃላይ የኩራት፣ የነፃነት፣ የአልበገር ባይነት፣ የሰው ልጆች እኩልነት በተግባር የተመሰከረበት፤ አፍሪቃን ባሪያ የማድረግ ሕልም የተጨናገፈበት፣ ኮሎኒያሊዝምና ፋሺዝም ባንድነት ድል የተነሱበት 127ኛ ዓመት ጎልቶ ደምቆ የሚከበርበትና የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ 

ይህንን ታላቅ ዕለት ስናስብ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው፣ በደማቸው አኩሪ ታሪክ ጽፈው አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድና ኢትዮጵያ የምትባል የነፃነት ምድር ከሙሉ ክብሯና ኩራቷ ጋር ያስረከቡንን ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችንን ለአፍታ ሳንዘነጋ ነው፡፡ በዚህ የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ጀግንነትን ከእምነት፣ ቆራጥነትን ከፍቅርና ርኅራሄ፣ ጥበብን ከብልሃት አስተባብረው መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንድ አንድ ሕይወት ኗሪ ያስተባበሩትና የመሩት እምዬ ምንይልክና ብርሃን ዘኢትዮጵያ ጣይቱ የዓድዋ ፈርጥ ናቸው፡፡ ዐፄ ምንይልክና እቴጌ ጣይቱ የሌሉበት ዓድዋ በኢትዮጵያ ታሪክ አልተመዘገበም፡፡

በቀደምት አባቶቻንና እናቶቻችን የአገር ፍቅር፣ የጀግንነት፣ የሰንደቅ ዓላማን ክብር፣ የኢትዮጵያዊነትን የልዕልና መንፈስ ያሠረፀች እምየ ቅድስት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደግሞ ልዩ ባለውለታ ናት፡፡ ወንድማችን መምህር ፋንታሁን ዋቄ ከ5ት ዓመታቱ የአርበኞች የነፃነት ተጋድሎ ጋር አያይዞ፣ 

‹‹የኢኦተቤ አፍሪካን ባርያ ለማድረግ፣[የተነሡትን][የቅኝ ገዥዎችን]… ፍልስፍና ፊት ለፊት ያሸነፈችና የዓለምን ሕዝብ እንደገና ከእንቅልፍ የቀሰቀሰች፣ የሰው ልጅ ሰው ነው የሚለውን ፍልስፍና ያፀናች፣ በትምህርት ብቻ ሳይሆን ጀግና አፍርታ ታቦት ይዛ ጦር ሜዳ ተገኝታ ሰው አይበላለጥም ብላ የእግዚአብሔርን ትምህርት ባንደበት ብቻ ሳይሆን በደምና ባጥንት ያስመሰከረች የጀግኖች እናት ነች፡፡››

በማለት የአገር ነፃነት በማስከበር ረገድ በፀረ-ኮሎኒያሊዝምና በፀረ-ፋሺስት ተጋድሎ የነበራትን ጉልህ ድርሻና ባለውለታነቷን በሚገባ ገልጾታል፡፡ መሠረትና ጉልላቷ ደግሞ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ የክብር ባለቤትን ቅዱስ÷ ውዱስ፣ ስቡሕ እያልን ሁሌም እናመሰግነዋለን፡፡

ከዚህ ቀደም ዓድዋን ባዘከርሁበት ጽሑፌ የብሔራዊ በዓላት ሁሉ በኵር (ቀዳሚ፣ፊታውራሪ) መሆኑን ገልጬአለሁ፡፡ ካገር ህልውናና ነፃነት አልፎ ዓለም አቀፍ ፋይዳ ያለው በዓል በኵር ያልሆነ የትኛው በዓል ይሁን? የበዓላት በኵር መሆኑን የምንስማማ ከሆነ  ደግሞ ብሔራዊ ቀናችን ነው፡፡ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን መቼ ነው ብለው ሲጠይቁን በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው የዓድዋ ድል በዓል ብለን በኩራት በአፍም፣ በመጣፍም፣ በተግባርም መንገር፣ ማስተማር ይኖርብናል፡፡ መንግሥት ቢኖረን ኖሮ አይደለም የኢትዮጵያ በሔራዊ ቀን የአፈሪቃውያን የነፃነት ቀን ሆኖ በአፍሪቃ ኅብረት ደረጃ በየዓመቱ ይከበር ነበር፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ዘረኛ አገዛዝ ሲወገድ የዓድዋ ብሔራዊ ቀንነት በሕግ ጭምር ይረጋገጣል፡፡ 

 ስለ ዓድዋ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጸሐፍት ብዙ የተባለ ቢሆንም፤ የታሪክ ምሁራን፣ ደራሲዎች፣ የኪነ ጥበብ፣ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች የዓድዋን ብሔራዊ ቀንነት አድምቃችሁ በድርሳናችሁ፣ በፈጠራ ሥራችሁ፣ በዜማችሁና በብሩሻችሁ ለዛሬውም ለመጪውም ትውልድ እንድታሳዩና እንድታስተላልፉ አደራ እላለሁ፡፡

ወታደራዊው ደርግና ከዛም በኋላ በኢትዮጵያችን በጉልበት የሠለጠኑት የጐሠኞች አገዛዞች ከነሱ አስቀድሞ የነበሩትን ሥርዓቶች በትጥቅ ትግል አስወግደው ሥልጣን የያዙበትን ዕለት ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ አገራዊ በዓል ለማድረግ ሙከራ ቢያደርጉም ከካድሬዎቻቸው ጋር አብሮ ከማቅራራት ባለፈ የሕዝብ ሳይሆኑ በጊዜው ጊዜ ወደ ታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ተጥለዋል፡፡ የዘረኞቹም ዕጣ ፈንታ ይኸው መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው አገዛዞች ኢትዮጵያችንን በዓለም ፊት ያዋረዱና አንገታችንን እንድንደፋ ያደረጉ ናቸው፡፡ ዕብደትና ድንቊርናን አስተባብሮ የያዘው በአረሚው ዓቢይ የጐሣ አለቃነት የሚዘወረው የኦነግ-ኦሕዴድ አገዛዝ ደግሞ ኢትዮጵያን በማዋረድ በታሪካችን አቻ የማይገኝለት የአጋንንት ቡድን ነው፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ፣ እሤቶች፣ ቅርሶች፣ ብሔራዊ መለያ ተቋማት፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሠራው አጋንንታዊ የኦነግ-ኦሕዴድ የጐሠኞች ቡድን ላለፉት 5 የሰቈቃ ዓመታት በጦርነትም ያለ ጦርነትም በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአረመኔነት ከመፍጀቱ፣ ዐሥር ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ከማፈናቀሉ፣ አገዛዝ ወለድ በሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ዐሥር ሚሊዮኖችን ለረሃብና ጠኔ ከመዳረጉና ዜጎችን በኑሮ ውድነት ከመጥበሱ በተጨማሪ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያኖች ብሔራዊ ቀናቸውን – የዓድዋን ድል መታሰቢያ – እንዳያከብሩ ለኦነጋዊ ሠራዊቱ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ በተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ ላገር ሉዐላዊነትና ለሕዝብ ደኅንነት የሚቆረቆሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ብናውቅም፤ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋሙ እንደ ተቋም በተለይም አመራሩ የጭራቁ ዓቢይና አገዛዙ ጠባቂ እንጂ የኢትዮጵያ አለመሆናቸውን ደግመው ደጋግመው በተግባር አሳይተውናል፡፡ ዓድዋን የሚጠላ መከላከያ የኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊም ቢሆን እንኳን ዓድዋ ለአንድ ተቋም የሚሰጥ ታሪክና በዓል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቀን ኢትዮጵያኖች ባሉበት ሁሉ በነፃነት ማክበር፣ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ማዘከር ማንም ወሮበላ የሚሰጠውና የሚነሳው መብት አይደለም፡፡ በሕዝባዊ በዓላት ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨውነት፣ ሕግና ሥርዓት አክባሪነት ባለጌ አገዛዞችን የሚያስተምር እንጂ ነቀፌታ የሚቀርበበት አለመሆኑን ለዓመታት አይተናል፡፡ 

ኦነጋዊው የጐሠኞች አገዛዝ ላለፉት 3/4 ዓመታት ዳር ዳር ሲል ቆይቶ ኢትዮጵያን ለማፍረሰ የመጨረሻ ሙከራ ያደረገውን የኢኦተቤክ ከነካ/ድፍረቱን ካሳየና ቅጥረኛነቱን/ባንዳዊ ማንነቱን ኢትዮጵያውያን ካወቁት በኋላ በይፋ ዓድዋ እንዳይከበር ኦነጋዊ ሠራዊቱን በማሰማራት፣ ዜጎች የእምዬ ምንይልክ እና የብርሃን ዘኢትዮጵያ ጣይቱ ምስል ያለበትን ልብስ እንዳይለብሱ፣ የዓድዋ ጀግኖች የተሠዉለትን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይዙ፣ መደብሮችን በሕገወጥ መንገድ በማሸግ፣ ዜጎችን በማሰርና በማንገላታት የለየለት ዕብደቱን እያሳየን ነው፡፡ በዚህም ጭራቁ ዓቢይና ቡድኑ አዋልደ ፋሽት መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡ 

የዐፄ ምንይልክና የእቴጌ ጣይቱ ልጆች እስላም ክርስቲያን ሳንል ዓድዋን በምንይልክ ዐደባባይ እንዳለፉት 2/3 ዓመታት በድምቀት እናከብረዋለን፡፡ ባገር ቤት ያለን ኢትዮጵያውያን፤ በባህላዊ ልብሳችን አሸብርቀን ምንይልክ ዐደባባይ እንገኛኝ፡፡ ኑ! የብሔራዊ በዓላትን በኵር ዓድዋን ከፍ ከፍ እናድርጋት፤ እናክብራት፤ እንዘምርላት፤ እንቀኝላት፤ እናወድሳት፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያኖች፤ እንኳን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን (NATIONAL DAY OF ETHIOPIA) ክብረ በዓል – ለዓድዋ ድል መታሰቢያ – በሕይወትና በጤና አደረሳችሁ፡፡

Filed in: Amharic