ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
25ቱ ግለሰቦች የቤተክርስቲያንን ሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ እስከአሁን ድረስ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው ቀጥለዋል
25ቱ ግለሰቦች ግን የሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ እስከአሁን ድረስ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው ቀጥለውና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን እግድ በመጣስ የአህጉረ ስብከትን ጽ/ቤት እየሰበሩ በመግባት በሌላቸው ሥልጣን ክህነት በመስጠት፣ በመዋቅራችን ላይ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን በመመደብ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው በመቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናችን የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 የሕግ ድንጋጌ መሠረት አስቸኳይ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ በማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና አስተዳደራዊ ጥሰት በመፈጸም ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሰዶ ዳጩ ወረዳ በሀሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሕገ-ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ሕገ-ወጥ አድራጐት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ፡-ሕገ-ወጥ ሹመቱ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፤ሕገ-ወጥ ሹመቱን ያከናወኑት 3ቱ የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳትና ተሹመናል ባዮችን 25 ግለሰቦች ከዲቁና ጀምሮ ያላቸውን ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር እና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት በማውገዝ መለየቱ ፤ምንም እንኳን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁሉንም አውግዞ የለየ ቢሆንም እናት ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ለሰላም በሯ ክፍት እንደመሆኑ መጠን የተወገዙት ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያኒቱን የሰላም ጥሪ ተቀብለውና የተከናወነው ድርጊት ሕገ-ወጥ መሆኑን አምነው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ለፈጸሙት ሕገ-ወጥ አድራጐት የሚሰጣቸውን ቀኖና ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆኑና ይህንንም ሐሳባቸውን በጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በማቅረብ ሪፖርት ካደረጉ የቤተ ክርስቲያናችን የሰላም በር ክፍት መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር 18 ቀን 2015ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መግለጹን እናስታውሳለን፡፡
በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሰላም በሩን ክፍት በማድረግ ትዕግስት የተሞላበት ጥረት ቢያደርግም የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከመቅረብ ይልቅ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው በመቀጠል ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር የሆኑትን አህጉረ ስብከት ጽ/ቤትና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መንበረ ጵጵስና ቁልፍ በመስበር የንብረትና የመዋቅር ወረራ በመፈጸም በሕገወጥ አድራጐታቸው በመቀጠላቸውና በተከፈተው የሰላም በር ተጠቅመው ለሰላም ዝግጁ ባለመሆናቸው ቤተ ክርስቲያናችን በሀገሪቱ ሕግ የተረጋገጠ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን ሕጋዊቱን ቤተ ክርስቲያን በሕገ-ወጥ መንገድ ተቋሞቿ የተያዙባት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ያለበትን ሕግን የማስከበር ኃላፊነት በመወጣት ተቋማዊ ክብራችንና ሕጋዊ ባለቤትነቷን እንዲያረጋግጥ ያደረገችውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በቅድሚያ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወከሉ ብፁዓን አባቶችን በማነጋገርና ለቀጣይ የውይይት አቅጣጫ በሰጡት አመራር ከቅዱስ ሲኖዶስ የተወከሉ ብፁዓን አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የቀድሞውን ሦስቱን ሊቃነ ጳጳሳት ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተደረገው ሰፊ ውይይት በ10 ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት መድረሱን እናስታውሳለን፡፡እናት ቤተ ክርስቲያን በተደረሰው ስምምነት መሠረት አሥሩን የስምምነት ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በመግለጫ አረጋግጣና በሮቿን ክፍት አድርጋ ለሰላም ከፍተኛ ጥረት በምታደርግበት ወቅት ሦስቱ የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ የመጡ ቢሆንም 25ቱ ግለሰቦች ግን የሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ እስከአሁን ድረስ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው ቀጥለውና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠውን እግድ በመጣስ የአህጉረ ስብከትን ጽ/ቤት እየሰበሩ በመግባት በሌላቸው ሥልጣን ክህነት በመስጠት፣ በመዋቅራችን ላይ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን በመመደብ በሕገ-ወጥ አድራጐታቸው በመቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለስብሰባ በመጥራት መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ሦስቱ የቀድሞ ብፁዓን አባቶች በአካል ቀርበው በሰጡት ቃል በተከናወነው ድርጊትና ድርጊቱን ተከትሎ በተፈጸሙት ክስተቶች ማዘናቸውንና በቀጣይ ሕገ-ወጥ ድርጊቱን እንደሚቃወሙና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶሱን መመሪያ አከብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱም የሦስቱን የቀድሞ አባቶች ሐሳብ በመቀበል ጉዳዩን አስመልክቶ በሰፊው ከተወያየ በኋላ የሚከተለውን የሰላም ጥሪ አስተላልፏል፡፡በዚህም መሠረት፡-ሦስቱ የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በስምምነቱ መሠረት ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ መጥተው በበዓታቸው ተወስነው እየኖሩ ስለሆነ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው እንዲደረግ፣ሃያ አምስቱን ግለሰቦችን በሚመለከት ምንም እንኳን በሕ-ወጥ አድራጐታቸው የቀጠሉ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገሪቱ ሰላም ካላት የጸና አቋም አንጻር አሁንም በድጋሚ ለመጨረሻ ጊዜ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት በተደረሱት 10 የስምምነት ነጥቦች መሠረት ከዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በጽሑፍ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉና በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀኖናቸውን ተቀብለው እንዲፈጽሙ፣ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለሰላም ስምምነቱ ላደረጉት አስተዋጽኦ ቤተ ክርስቲያናችን ምስጋናዋን እያቀረበች በቀጣይ በተደረሰው 10 የስምምነት ነጥቦች መሠረት ሕገ-ወጦቹ ግለሰቦች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለሕግ ተገዥ እንዲሆኑ የበኩላቸውን መንግሥታዊ ሚና እንዲወጡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን በድጋሚ ታስተላልፋለች፡፡በተደረሰው ስምምነት መሠረት በሕገ-ወጥ መንገድ አህጉረ ስብከትና መንበረ ጵጵስና ሰብረው የያዙ ግለሰቦችን በተመለከተ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ተገቢውን የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት ከቤተ ክርስቲያናችን ይዞታ በማስወጣት ለቤተ ክርስቲያናችን ሕጋዊ የሥራ ኃላፊዎች በማስረከብ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእለት ከእለት ተግባርና ሐዋርያዊ አገልግሎት ያለምንም የጸጥታ ሥጋት እንዲከናወን እንዲሁም በተደረሰው ስምምነት መሠረት እስከአሁን መፈታት ሲገባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎችና ምእመናን እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡ሃያ አምስቱን ግለሰቦች በሚመለከት ከኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በተደረገው ውይይት ክቡር ርእሰ መስተዳድሩ በተደረሰው 10ሩ ስምምነት ነጥቦች መሠረት ሃያ አምስቱንም ግለሰቦች አጠቃልዬ ወደ አዲስ አበባ አመጣቸዋለሁ በማለት በገቡት ቃል መሠረት በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦቹ በክልሉ መንግሥት አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ስለሰማን የክልሉ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ለፈጸመው አድራጐት ቤተ ክርስቲያናችን እያመሰገነች ያልገቡትንም ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ በተገባው ቃል መሠረት እንዲገቡ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፣ውግዘቱን በሚመለከት ውግዘቱን የማንሳት ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለመጋቢት 21 ቀን 2015ዓ.ም. ተጠቃለው ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲመጡ ጥሪ ተላልፏል፣
መጋቢት 6 ቀን 2015ዓ.ም.አዲስ አበባ ኢትዮጵያ