>

ይድረስ ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ (ከአባ ጌድዮን - ዘደብረ ሊባኖስ)

ከአባ ጌድዮን – ዘደብረ ሊባኖስ
(በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ፤ በቅድስቴ ሥላሴ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ መምህር)


ይድረስ ለሀገር መሪዎች እና ፖለቲከኞች፤
ይድረስ ተምረናል ለምትሉ ምሁራን፤
ይድረስ ለሀገር ሽማግሌዎች፤
ይድረስ ለሃይማኖት መሪዎች፤
ይድረስ ሕሊና አለኝ ለምትሉ ባለሕሊናዎች በሙሉ፤


ምነው ሀገሬ ካለፈ ታሪክ መማር አቃታት?  ምነው ሀገሬ ከታሪክ ተምራ ሯሷን ማስከበር ተሳናት? ወዳጆቼ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ተወያይቶ ችግር መፍታት ባለመቻሉ ምክንያት በተከሰተው አስከፊ ጦርነት ብዙኃን ደኃ እናቶችን ያለ ጧሪ ያለቀባሪ ያስቀረ እልቂት አስከተለ።

ከዚህ የሀገራችን ክፉ ታሪክ መማር ባለመቻላችን ወርደን እርስ በእርስ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጋር ጦርነት በመጋጠማችን የደሀን ልጅ ሙጥጥ አድርጎ የበላ ሌላ አስከፊ የጦርነት ታሪክ አሳለፍን። አሁንም ቢሆን የወልቃይትና የራያ አላማጣ ጉዳይ በሠላም እስካልተፈታና ዘላቂ እልባት እስካልተደረገበት የተዳፈነ እሳት ወይም ድንገት ሊፈነዳ የሚችል የተጠመደ ቦንብ ነው።

ችግሩ በዘላቂ መፍትሔ እልባት ሳያገኝና ጦርነቱ ሳይውል ሳያድር እንዲሁም የወዳደቁት እንኳን በቅጡ ተለቅሞ አስከሬናቸው አፈር ሳይለብስ፤ ያለፈው አልበቃ ብሎን ሰሞኑን በኦሮሚያና በአማራ ክልል መካከል ጎራ ለይቶ መተነኳኮስ ተጀምሯል።  የጦርነት ነጋሪቱም ዕለቱን በሚያፈጥኑና ችግሩን በሚያባብሱ አሉታዊ ድርጊቶች ታጅቦ ሲጎሰም በዓይንም በጆሮም ይታያል፤ ይሰማል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም ነገሩ ሲጀመር በዚህ መልኩ ነበር። ሄዶ ሄዶ ወደጦርነት ሲገባ ያስከተለው መዘዝ የደሀን ልጅ ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላት ባሻገር በብዙ ብድር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ዶግ አመድ ሆነዋል። ቢያንስ ወደሠላሳ ዓመት ወደኋላ የሚጎትት ኪሳራ በክልሎች ተመዝግቧል። መንግሥት ካዝናው ተራቁቶ በውጪ ምንዛሪ እጦት የሕዝብ ኑሮ ተመሠቃቅሏል። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነስቶ መቃቃርና ማኅበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል። በእርግጠኝነት ከዚህ አደጋ ለመውጣት በርካታ የጭንቅ ዓመታት ከፊት ተጋርጠዋል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው አደጋ መከራው እያናወዘን እንደጦስ ዶሮ በክፉ አዙሪት በኢኮኖሚ ችግር በጭንቅላታችን ተፈጥፍጠን የሚያነሳን የውጭ እጅ ለማገኝት በክፉ መቃተት ላይ በምንገኝበት በዚህ ክፉ ሰዓት ዳግም ከማንወጣበት ሌላ ማጥ ለመዘፈቅ እየተንደረደርን እንገኛለን።
በኦሮሚያና በአማራ ክልል መካከል ግጭቱ ብሶ ወደጦርነት ከተገባ እመኑኝ እንዳለፉት ችግሮች በቀላሉ ማገገም አይደለም ተመልሶ ሀገር መሆን የማይታሠብ ይሆናል። በጭራሽ አሸናፊ የሌለውና በቀላሉ የማይቋጭ መሆኑን ለመገመት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። ምንአልባት ከዚህ እልቂት ዕድለኛ ሆነህ ከተረፍክ ቀና ስትል የምታየው ሠላም አስከባሪ በሚል ስም በገዛ ሀገርህ ከዚህ አትለፍ የሚል ቋንቋው የማይሰማ ወይ ነጭ ወይ ጥቁር ወታደር ነው።

በእርግጥ በሀገራችን ከእኔ የሚሻሉ ምሁራን፥ የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች፤ እንዲሁም በሳልና ሀገር ወዳድ ፖለቲከኞች ብሎም ለሕሊናችሁ የምትኖሩ አርቆ አስተዋዮች እንዳላችሁ ጥርጥር የለኝም። ቢያንስ ያለፈው ተሞክሮም ቢሆን ያሁኑ ዳር ዳር ነገሮች ያለመከሰት ዕድላቸው ተመናምኖ ባለበት በዚህ ሰዓት ዝምታው ሀገራችን አይናችን እያየ ትውደም ብሎ እንደመስማማት የሚቆጠር መሆኑን ቢያንስ የሁለቱም ክልሎች ምሁራን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችና ከባለሕሊናሞች የሚሰወራቸው ነው ብሎ መገመት ይከብዳል።
ወገኔ ዝምታው እስከመቼ ነው?መንግሥት ከሁሉም የበለጠ ኃላፊነት ስለተሸከመ እባክህ ይህ ድርጊት ሀገር ያጠፋል እባክህ ይህ አካሔድ ሀገር ይጎዳል ብሎ መጋፈጥና ፊትለፊት መሞገት እና ከአባባሽ ድርጊቶች እንዲመለስ የማድረግ ኃላፊነት የኛ አይደለምን? ወገኖቼ አሁን እንደልብ መንግሥትን የምንሳደበው ቢያንስ ተረጋግተን ቁጭ ያልንበት ሥፍራ ስላለን ነው። ነገር ግን በዚሁ መልኩ መቀጠል የምንችል ይመስላችኋል?! የተሳሳተውን ተዉ የሚል እንዴት ጠፋ?  የሚሰማስ የሚሰማስ አካል እንዴት ጠፋ?!

እባካችሁ የሚመለከታችሁ አካላት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ ሀገር ያሳጣል እንጂ አይገነባም። ስለዚህ እባካችሁ ስለእግዚአብሔር ብላችሁ ዳግም የንጹሐን ደም አይፍሰስ። እስካሁን የፈሰሰው ብቻ ለሀገራችን የመርገም እንጅ የበረከት አይደለም።
እባካችሁ የተማርን ነን ባዮች ምሁራን፥ እባካችሁ የሀገር ሽማግሌዎች ነን ባዮች፥ እባካችሁ የሃይማኖት መሪዎች ነን ባዮች፥ እባካችሁ ባለመልካም ሕሊና የሆናችሁ ፖለቲከኞችና ሀገር ወዳድ ዜጎች የጨው ገደል ሲናድ ብልጥ ያለቅሳል ሞኝ ይስቃል ነውና የተራራቁትን አቀራርቡ።

በእርግጥ ችግር መፍታት ማቀራረብም ይሁን ማስማማት ቀላል አይደለም ብዙ ዋጋም እንደሚያስከፍል አውቃለሁ። ነገር ግን እስካሁን ኢትዮጵያ እዚህ ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ነው። ዋጋውን የከፈሉት ደግሞ የደሀ ልጆች ደም ገብረው ነው። አሁን እንኳ ተራው የእናንተ ይሁንና እስኪ ዋጋ ክፈሉ።

እባካችሁ!!
እባካችሁ!!
እባካችሁ!!

(ይድረስ ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህን መልእክት ለሌሎችም ማዳረስ ሀገራዊና ሕሊናዊ ግዴታ ነውና ሀገሬን/ኢትዮጵያን የምትሉ ሁሉ ሼር አድርጉት!!)


Filed in: Amharic