>

'' ትግራይንና ኦሮሚያን የማዋለድ'' አዲሱ የፓለቲካ አሰላለፍ

” ትግራይንና ኦሮሚያን የማዋለድ” አዲሱ የፓለቲካ አሰላለፍ

ፊልጶስ

መቼም ቢሆን እያንዳንዱ ትግል መነሻና መዳረሻ አለው።  ይህ ሲባል ሁሉም ትግል ግቡን ይመታል ማለት አይደልም።

የአንድ ህዝብ ወይም ቡድን ሰናይም ይሁን እኩይ ትግሉ ለግብ የሚበቃው፤ በትግሉ አራማጆች የዓላማ አንድነትና ጽናት፣ ለመሰዋትነት ዝግጁነት፣ ብሎም ውጫዊና ውስጣዊ ድጋፍን ማዕከል ሲያደርግ ነው።

 በተለይም ለአለፋት ሃምሳ ዓመታት አገራችን የተለያዮ የፓለቲካና የጎሳ ቡድኖች ለተለያየም ሆነ ለአንድ ዓይነት ግብ ትግል  አድርገዋል። ‘ዓላማችን ያሉትን ለመስፈጽም በጎሳ ስም፣ በሶሻሊዝም ስም፣ በአገር አንደንት ስም፣ ወዘተ—– ህዝብን  የትግላቸው ማገዶ አድርገዋል። አንድደዋል። ‘ርስ-በርሳቸውም ተራርደዋል።  ይህ ብቻ አይደለም በአገራችን ሰባአዊነትና አገራዎ አመለካከት እንዲጠፋና በምትኩ የሰው ልጅ የወገኑን ንበርትና ሃብት መውረስ ብቻ ሳይሆን፤ በሃሰት ትርክት፣ በባዕዳን ርዕዮት-ዓለምና በጥላቻ በነበዘ እዕምሮ፤ ምድር ዓይታውና ሰምታው የማታውቀው የጭካኔ ዓይነት እስከዚች ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይፈጸማል። ምንም ይበሉ ምንም፤ ምንም ያደርጉ-ምን፤  መጣንበት በሚሉት ጎሳ ስም፤ አዳዲስ እጀንዳ አየፈጠሩ፤  የሁሉም ”ታጋዮች” ግብ   ሥልጣንና ገንዘብ  መሆኑ ትላንትም ሆነ ዛሬ የምናየው መራራ ሃቅ ነው።

በየግዜው የተነሱትን የገዥዎቻችን የስልጣን ”አራራ” ፤ የጎሳ ቡድኖችን ጭካኔና አርመኔነት ስናስብ ደግም፤  በ’ርግጥ ከሰው ልጅ አብራክ’፤ ከዚያ ከኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ አብራክ  ለመፈጠራቸው እድንጠራጠርም ያደርገናል።

አሁን ያለውን አጥፍቶ የመጥፋት የጎሳ-ፓለቲካ አሰላለፍ፣ የሚፈጸመውን ግፍና የኑሮ ውድነት ስናይ ደግሞ  መጸሃፍ እንደሚለው”—ከዛሬ ትላንት ይሻል ነበር።—” ለማለት መገደድ ብቻ አይደልም፤  ነገን ስናስበው ”ምነው ባልተፈጠርን ” እስከማለት ደርሰናል።

—–ጨልሟል -ጨልሟል ፣ የ’ኛ ቀን ጨላልሟል

አይነ-ስውር እንኳን ውጩን ማየት ፈርቷል።——

በአገራችን ያለውን  የወቅቱን የፓለቲካ አሰላለፍና አዲስ አገር ለማዋለድ  በጎሳ ስም የሚደረገውን ”የደም ንግድ”  ለማሳየት፤ ከደርግ መንግሥት መወገድ በኋላ 1983 የነበረውን ምን እንደሚመስል ለግንዛቤ ያህል ከዚህ ላይ በአጭሩ እናንሳው፤

1/ ሻአቢያ፤ ጀበሃን አስወግዶ ሙሉ- በሙሉ በሚባል መልኩ የኤርትራ ብቸኛ ታጋይ ለመሆን  ሲበቃ፤ እውነቱን ለታሪክና ለትውልድ እናስቀምጥ ከተባላ ዋና የትግል ግቡ  በንጉሡ ዘመን የፈረሰውን የፌደራላዊ አስተዳደር መመለስ ነበር። ለትግሉ መነሻ የሆነውም ይህው ሲሆን፤ በሂደት ግን በአረቦችና በምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገቢነትና አመራር ሰጭነት፤ ” አማሃራይ- ኢትዮጵያ ”፤ የኤርትራ ቀንደኛ ጠላት፤ ኤርትራም ”የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት” አንደሆነች  ተድርጎ፤ ለህዝብ በመሰብክና በማስተማር፤ ደራሲ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ በተሰኘው መጸሃፋ እንዳለው ”— ጭንቅላቱ ውጭ፤ እግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ–። ”  ያደረገ ትግል  የኢትዮጵያን  ለማዳከምና    ደርግን ለመጣል በቃ።

 የደርግ ውድቀት ኢትዮጵያን ያለባለቤት ስለ አስቀረትና  በወያኔ እጅ ከመውደቋም በላይ፤ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ትልቅ የምስራች ስለነበር፤  ሻአቢያ የኢትዮጵያዊነት እትብት የተቀበረባትን ኤርትራን ለመገንጠል በቃ። እውነት እንደ ሃሰት፤ ሃሰትም እንደ እውነት ተቆጥሮ ፤ የክህደት ታሪክ ” በአሸናፊዎች” ለመጻፍ ተሞከር። ”አፍሪካዊት ሲንጋፓር ” እናደርግሃለን የተብለው የኤርትራ ህዝብም  ያተረፈው ነገር ቢኖር  ጦርነት፣ ስደት፣ ድህነትና በሰባአዊ ዕጦት መሰቃየት ነው።

ይሁን እንጅ ተፈጥሮና ታሪክ የማይለያየን በመሆናችን አሁንም በዚህ ሰዓት ሻአቢያ በኢትዮጵያ የፓለቲካ አሰላለፍ ውስጥ አንደኛውና ጉልህ ሚና ይዞ ይገኛል።

2/ ወያኔ (ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ) ፤ የትግሉ መነሻ ” እንደ ሻአቢያ ሁሉ ”አማሃራን ” የትግራይ ህዝብ ጠላት  አድርጎ  ”በማኒፈስቶ” ደርጃ አውጥቶ መታገያ ያደረገና አሁንም እየተጠቀመበት ያለ ነው። ትግሉን የጀመሩት  ብዙዎቹ  የወያኔ መስራቾች  የባንዳ ልጆች ፤ አፍቅሮ-ጣሊያን  ሲሆኑ፤ ዋና ግባቸው ”የትግራይ ሪፑብሊክ” መመስረት ነው። እጅግ ቋቅ የሚለው ደግሞ ”የትግራይ ሪፑብሊክ”  የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እንደ ሆነ ተደርጎ መነገሩ ነው።

1983 ከሻአቢያ ጋር ኢትዮጵያን ሲቆጣጥሩ፤ ቅድሚያ የሰጡት ግን ኤሪትራን ማስገንጠልና በሁለት እግሯ እንድትቆም ማደረግ ሲሆን፣ ለግዜውም ቢሆን ዋና ግባቸው የሆነውን ትግራይን የመገንጥል ዓላማ በይደር ትተው፤  ”ኢትዮጵያን ተቆጣጠርን፤  አማሃራን ”አከርካሪውን” ስለሰበርነዋል፤  በሂደትም ኢትዮጵያዊነትን አፈራርሰን፣ጽንፈኛ ኦሮሞን ከጎናችን አድርገን፤ ትግራይን በመገንባት ኃያል እናደርጋታለን–   ”  በሚል አቅደው፤ አገሪቱን መዝረፍ ላይ ተሰማሩ። በሁለተኛ ደረጃ  እቅዳቸውም ፤ኢትዮጵያን በበላይነት መግዛት ካቃተን ሙሉ ኃይላችን ይዘን ”ኦሮሞና አማራ ላይ የማይጠፋ እሳት ለኩሰን፤ እነሱ ሲባሉ ” በምንፈልገው ሰዓት መገንጠል እንችላለ።”’ በሚል  የተቀመረው  የፓለቲካ ቁማር እንደ ታሰበው ሳይሆን አሁን ካለበት ደረጃ ደርሰ።

3/ ኦነግ /ኦሮሞ ነጻ አውጭ/ ፤ መነሻውም ሆነ መድረሻው ”ከኢትዮጵያዊያን ቅኝ ገዥዎች” ነጻ መውጣትና ”አማራ” አንደኛ ጠላት ሲሆን፤ መታገያ ስልቱም  የተቀደውም  ከሻአቢያና ከወያኔ ሲሆን፤ የትግሉ አጋሮች ጀርመን እና ስካንዲቪያን አገሮች ይገኙበታ። ኦሮሚያ የምትባል አገር መመስረትን ግብ አድርጎ ፤ በ1983 ዓ፡ም ከወያኔ ጋር   መገንጠልን የሚፈቅደውን የጎሳ -ህገ-መንግሥትንና ክልል አብሮ በማርቀቅና በማጽደቅ የተሳተፈ ቡድን ቢሆንም፤ በኋላ ላይ ከወያኔ ጋር የፈጸመው ጋብቻ ፈረሰና ወደ ጫካና ወደ ባህር -ማዶ፣  እንዲሁም ወደ ኤርትራ ተሰደደ።

ሃያ ሰባት ዓመት  በወያኔ ፈላጭ ቆራጭነትና ራሱ ወያኔ ጠፍጥፎ በሰራቸውና   የጎሳ ስም በሰጣቸው አጃቢዎቹ  አማካኝነት የኢትያጵያን ህዝብ ቁም ስቅሉን አሳዩት።  ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፤ እንዲሁም ስለ ፍትህና እኩልነት  መታገል ቀርቶ ማውራትም የህይወት ዋጋ የሚያስከፍል ሆነ።  በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ጥላቻ ተሰበከ። አማራ የሚባለው ማህበረስብና ኢትዮጵያዊነት የህዝቡ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ነው ተብሎ በፍኖተ-ካርታ  ደረጃ  ተቀርጾ፤ ለአዲሱ ትውልድ በትምህርት ገበታ ላይ ዋለ።  

በወያኔ ”አማራ” ተብሎ ስምና ክልል የተሰጠው ህዝብም በያለበት እንደ  አውሬ ታደነ። ”መጤ” እየተባላ ተሳደደ።  ከአብራኩ የወጡ ” አማራ ነኝ” የሚሉ ባለሥልጣናት ቢኖሩም፤ ለሆዳቸው ያደሩ  ነበሩ ፤ አሁንም ናቸው። የገዥዎቻቸውን  ጉዳይ ማሰፈጸም  ብቻ ሳይበቃቸው፤ ለአለቆቻቸው ታማኝ መሆናቸውን ለማሳየት  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ አብረው ዘመቱ።

ይሁን እንጅ በተለይም 1997 ምርጫ በኋላ የኦሮሞም ህዝብ የወያኔን የበላይነት በመቃዎሙ በግፍ ታሰረ። ተገደል። የኋላ- ኋላ  ”የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስና ህዝብም ከወልቃይት እስከ ወለጋ፤ ከጎንደር እስከ እምቦ ሲያምጽ፤  በውጭ ያለውም ዜጋ ተቃውሞን ሲያጠናከር፤ ወያኔ ራሱ በጎሳ ያደራጃቸውና ጥላቻንና ጸረ- ኢትዮጵያዊነትን   ያሰለጠናቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ ኦህዴድና ብአዴን የሴራ ትግል አድረገው ፤ የህዝብን ትግል ጠልፈው ወያኔን 1910 ዓም ወደ መቀሌ ሸኙት።

 በመጨረሻም  በወያኔ ጡጦ ያደገው ኦህዴድ በሚስጥር ከኦነግ ጋር በመጣመር  የበላይነቱን አረጋግጦ፤  በጠ/ሚ አብይ አህመድ መሪነት፡ ብልጽግና በሚል ስም፤ ከትግራይ ውጭ፤ በሌላው የኢትዮጵያ  ክፍል ፤ ወያኔ በስልጣን ዘመኑ እንዳደረገው ሁሉ፤ እነሱም በተራቸው በመከረኛ የኦሮሞ ህዝብ ስም ፤ ነገር ግን በመንግሥታቸው ኢትዮጵያዊነትን እየሰብኩ በተግባር  ኦሮሚያ የምትባል አገር ለመገንባት ደፋ ቀና ሲሉ ከወያኔ ጋር ጦርነት ገቡ።

ጦርንቱ በመንግሥት  ”ህግ በማስከበር” በሚል ስም ተካሄዶ፤ በተለይም ፣ በትግራይ፣ በጎንደርን፣ በወሎን፣ በሸዋና በአፋር ህዝብ ላይ ብዙ ግፍና በደል ተፈጽሞ፤ ህዝብ እንደ ቅጠል እረግፎ፤ ማህበራዊ ተቋማት ወደመውና ተዘርፈው፤ተበዳዩ ህዝብ ፍትህ ሳያገኝ፤ ማንም ተጠያቂ ሳይኖር፤ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ መፍትሄ ሳይሰጠው ፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተካሄደ ስምምነት መሰረት ”ወያኔ ትጥቅ የፈታል፡ በማዕከላውይ መንግስት የበላይነት በትግራይ ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግሥት ይመስረታል።” የተባለው ሁሉ አንዱም ሳይተገበር፤ ”ሰላም” ወረደ  ተባለ።

 የአዲስ አበባው መንግሥትና የመቀሌው ወያኔ ”ድሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ እንጅ ያጣላን፡ እኛ እኮ አንድ ነበርን።” በሚል ግንኙነታቸውን በማጠናከር ላይ ሲሆኑ፤ ይህም በአገራችን ፓለቲካ አዲስ አሰላለፍ የፈጠረ ሲሆን አሰላለፋም በተለይ  በአሜሪካ  የሚዘውር መሆኑን በገሃድ የሚታይ ነው። ለዚህም ሰሞኑን ኢትያጵያን አሰመልክተው ያወጡትን መግለጫ ማየት በቂ ነው።

 ወደድንም-ጠላንም አሜሪካ ደግሞ  በተለይም ወልቃይት ለትግራይ ተመልሶ፡  ቅድሚያ ትግራይን  ቀጥላም ኦሮሚያን  እንደ አገር የማዋለድ እቅዷን ሳትተገብርና  በተቻለ ፍጥነት ኢሳያስን ከሥልጣን ሳታባርር፤ ኢትዮጵያን ያለ ኢትዮጵያዊያን ሳታስቀር እንቅልፋን አትተኛም።  

በ’ርግጥ  የአሜሪካም ሆነ የወያኔ ወይም የኦነጋዊ ብልጽግና  ፍላጎት እውን የሚሆነው እንደ ትላንቱ ዛሬም ለኢትዮጵያና ለትዮጵያዊነት እንታገላለን  የምንል ዜጎቿ   ከፊት ለፊታችን የመጣውን  አደጋ ካልተገነዘብን እና ለ’ነሱ አሳልፈን አገራችን ከሰጠን ነው።

ብዙ ሰዎች  አሁን ያለው የወያኔና የብልጽግና ግንኙነት   በሰላም ስም  እንዴት ሊፈጠር ቻለ ብለው ይጠይቃሉ። መረዳት ያለብን በወያኔና በኦነጋዊ -ብልጽግና መሃከል  የዓላማ ልዮነት የለም። ያለውና የነበረው ልዮነት  የኃይል አሰላለፍ ነው።  ጠ/ ሚ አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እንድነት ስም  በህዝብ  መሰዋአትነት  ወያኔን ካሸነፋ በኃላ፤ እስከመጨረሻው  ቢቀጥሉና ወያኔ ከጨዋታ ውጭ ቢሆን፣ ቀጣዩ የህዝብ ትግል  ወደ ኦነጋዊ ብልጽግና እንድሚሆን ተገንዘበዋል። በተልይም የአንድነት ኃይሉና  ወያኔን ለመምታት የጠሩት ”ፋኖ” የተባለው  የታጠቀ ኃይል  ከወያኔ ጋር ሆነው  መምታት እንዳለባቸው ተረድተውል።  በያዙት የዘረኝነትና በኦሮሞ ስም ኢትዮጵያዊነትን እያጠፋ   በተረኝነትና በባላይነት  መግዛት እንደማይችሉ ተገንዝበዋል።  ከዚህ በፊት እንዳልኩት ”ሜካፓቸው ለቋል። ማስካቸው ወልቋል።”

ስለዚህም አሁን ከወያኔ ጋርና ከመሰል የስልጣን ተቀናቃኞች   የጎሳ አራማጆች፤  እንደ እነ አቶ ጀዋር መሃመድ ካሉት ጋርም ቢሆን    መተባበርና ”ኦሮሚያን” በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ለመመስረት መጣር አለባቸው።  ያለያ  የሥልጣን ዕድሚያቸው ”የማለዳ ጤዛ” ይሆናልና።

ወያኔም  ከውጭም ሆነ ”ፌዴራሊስት” ከሚላቸው በሚያገኘው ድጋፍ፤  በተለይም ወልቃይትን በማስመለስና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ከኢትዮጵያ ጋር በማጋጨት፣ ወደ  ቀጣይ ምዕርፍ ” የትግራይ ሪፕብሊክ”  ለመሸጋገር፤ ከኦነጋዊ ብልጽግና ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት እንዳለበት ተረድቷል።

ከዚህ ላይ  መገንዘብ ያለብን የአሁን  የፓለቲካ አሰላለፍ እንደ 1983 ሁሉ ኢትዮጵያን የሚዘውሯት ፤ ኢትዮጵያን የሚጠሉ የጎሳ ፓለቲካ አራማጆች ሲሆኑ ፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የተሰለፈ  የፓለቲካ ድርጅት ፤የኦነጋዊ ብልጽግናን መንግሥትም ሆነ  ፤ የተግራይ ነጻ አውጭ -ወያኔን የሚገዳደር  ኃይል የለም።  ነገር ግን  ትላንትም ሆነ ዛሬ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብሎም ለአንድነቱ የተሰለፈና የሚታገል  ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ፤ ከመሃል እስከ ዳር ያለው የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ነው።  

ይሁን እንጂ ህዝብንም እስከ አላደራጁትና ታግለው እስከ አላታገሉት ድረስ፤  ነፍሳቸውን ይማረውና ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እንደሚሉን ፤ ”—-  የኢትዮጵያ ህዝባዊ ትግል  ገዥዎችን መንቀል እንጅ ፤ ኢትዮጵያዊንትንና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መትከል እስከ አሁን አልቻለም።—”

የጎሳ ገዥዎቻችን  በምድር ላይ   ታይቶና ተሰምቶ  ለማይታወቅ አሁን ላለንበት መከራና ድህነት፤ ብሎም የህልውና ጥያቄ ውስጥ አድርሰውናል። ማርቲን ሉተር ኪንግ  ” አንተ ካልተጎነብስክላቸው እነሱ ከአንተ ጀርባ  ላይ አይወጡም።” እንዳለው ፤  ለጎሳ ፓለቲከኞችም ሆነ ለውጭ ጠላቶቻች መፈንጫና አገር አልባ ለመሆን የተቃረብነው በ’ኛ ድክመት የመሆኑን መራራ ሃቅ እንቀበል። ለዚህም ነው፤

”—-ኧረ— ምረር-ምረር፣ ምረር እንደ ቅል፣

      ባይመር እኮነው ዱባ እሚቀቀል ።—–”የሚባለው።

 ነገ ሳይሆነ ዛሬ ጠላቶቻችን ካዘጋጁልን  የጎሳና የመንደር አስተሳሰብና መናቆር  ወጥተን ከተደራጀንና ከታገልን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነታችን የማንታደግበት ምንም ምክንያታዊ  ኃይል የለም። ኢትዮጵያ ሺ ዘመናትን አልፋ ከዚህ የደረሰችው፤ ሺ መከራዎችን ተሻግራ ነው። የተሻገረችው ደግሞ ሞትን በናቁና ክብርን ባሰቀደሙ የልጆቿ መሰዋአትነት  ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

ፊልጶስ

E-mail: philiposmw@gmail.com


Filed in: Amharic