>

የበሻሻው ተወካይ '' ---አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን - የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?...'' (ፊልጶስ)

የበሻሻው  ተወካይ ” —አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን—የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?—-”

ልጶስ


ደጋግሜ ለመስማት ሞከርኩ፤ እየመለስኩና እየከለስኩ ሰማውት።  የማየውና የምሰማው  ሁሉ ህልም  መሰለኝ።   በህልሜ ቢሆን ተመኘሁ። ግን ሃቅ ነው፤ መጋቢት 19 ቀን 1915 ላይ በቀጥታ በተሊቪዥን  ለመላው ኢትዮጵያዊ የታይና የተደመጠ።
 ” —አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን—የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?—-‘ የሚል የበሻሻው ተወካይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ የአብይ አህመድ ድምጽ፤ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አስተጋባ።

 ምንም እንኳን በጎሳ በተቧደን  የይስሙላ የምክር ቤት የመንጋ-ስብስብ ፤ ለአገርና ለህዝብ ልዮነትን እንጅ አንድነትን፤ እልቂትን እንጅ ሰላም፤ ኋላቀርነትን እንጅ ብልጽግናና እንደማያመጣ የታወቀና፤ ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ምስክር ቢሆንም፤  የምክር ቤት አባል  ከሆኑት ከአቶ ክርስቲያን  ታደለ    የተጠየቀው ጥያቄ  የሳቸው ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል።

በ’ርግጥ ራሳቸው ጠያቂውም   በመንግሥት መዋቅር ስር ያሉና   ለተፈጸመውና ለሚፈጸመውም ወንጀል ሁሉ አብረው ያቦኩ፣ ዲሞክራሲ ያለ ለማስመሰል በተቃውሚነት የተሰልፋ ስለሆነ ፤ እሳቸውም ሆነ ፓርቲያቸው  ከብልጽግና ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠውና ‘ከሰምቶ አዳሪው” ምክር ቤት  ለቀው ፤ከህዝብ ጎን ተሰልፈው ጠ/ ሚ አብይ አህመድ ተገደው ከሥልጣን ሊለቁብትና አገርን ለመታደግ  የሚያስችል  ህዝባዊ ትግል ቢያካሄዱ ይመረጥ ነበር።  ነገር ግን  ከላይ እንዳነሳውት የጎሳ ተወካዮች ለሥልጣን እንጅ ለህዝብ ጥቅምና ለአገር አንድነት አልቆሙም። ከመጀመሪያውም በጎሳና በመንደር አይቧደኑም።

የበሻሻው ተወካይ  ጠ/ሚ አብይ እንኳን እስከ አሁን በአገርና በህዝብ ላይ የፈጸሙት ወንጀል ለግዜ ፍርድ ትተን፤ በይፋና ለመላው ዓለም የተናገሩት የዕለቱ ንግግራቸው ፤ ” —አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን—የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?—-” የሚለው ብቻ  ከሥልጣናቸው እንዲባረሩና  በህግ ፊት እንዲቆሙ ባደረጋቸው ነበር። ግን ጠቅላዩ እንደ አሉት ”–ምን ኃይል አለ?—”  

የጠቅላዩን ትዕቢት፣ ንቀት፣ ማን አለብኝነት፣ራስን ከህግና ከፈጣሪ በላይ የመቁጠር  ግብዝነት የውስጥ ማንነታቸውን  በገሃዱ ዓለም አሳይቶናል። ታሪክም ሰርተዋል፤  የሚመራው ”አገርና ህዝብ  ለማፍረስ ከልካይ የለኝም ”– የሚለው ንግግራቸው  በዓለማችን የመጀምሪው ባለታሪክ  ”የአገር መሪ” ያደርጋቸዋል።

  በአጠቃላይ በህዝብ ላይ  ለአልፋት ዓምስት ዓመትት  በመንግሥታቸዊ መዋቅራቸው የፈጸሙት ዘር ማጽዳት፣ ግፍና በደል አልበቃምና፤  አንድ ሽማግሌ አባት እንዳሉት፤”እኛ ርሃቡን ስንችለው ገዥዎቻችን  ግን ጥጋቡ አልችለው አሉ፡”

 እናም  የጥጋባቸው ጥጋብ፣ የንቀታቸው ንቀት፤ ኢትዮጵያን  ” ትላንት ያልነበረች፤ ወደፊትም የማትኖር፣ በኪሳቸው  ውስጥ ያለች   ጥሬ ሳንቲም ” አደረጓት።  በ’ርግጥ ለአንድ ዜጋ አገር በዚህ ደረጃ ስተፈረጅ ከማይትና ከመገዛት የበለጠ የሚያምና  የቁም ሞት አለ?

 ጠ/ ሚ አብይ አህመድ ትላንት በህዝብ ትግልና  ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነትና ታሪካዊነት እየማሉና እየተገዘቱ  ወደ  መምበሩ እንደመጡ ዘነጉት። ”እናቶች ጸልዩልኝ!” እያሉ እንዳልተማጽኑ ሁሉ ዛሬ ”ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያስቆመኝ ኃይል አለ ወይ—” እያሉ  በትዕቢት መደንፋት ጀመሩ። ወደ ኋላ ለማሰብና ታሪክን ለማስታዎስ ቢችሉ ኑሮ ” ትዕቢተኞችና በህዝብ ላይ የተሳለቁ”  የት እንደደረሱ በተረዱ ነበር።
—ይዘገያል እንጅ ግዜ ውል አይስትም
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም።—-

ታዲያ የጠ/ሚ አብይን የትላንትና እና  የዛሬ  ማንነት ሁለትና ሶስት እሥስታዊ ማንነት ሳይ፤  የአንድ  ህልመኛ ታሪክን አስታወሰኝ፤
”–ሰውየው ህልማ ያያል፤ ህልመኛው ሰውየ ለሊቱን ሙሉ ያየው ህልም ሰለረበሸው በጠዋቱ ተነስቶ  ወደ ታወቁት ህልም ፈች ሄደ።፡

ህልመኛውም ለህልም ፈችው ያየውን ህልምና የለቀቀበትን ፈርሃት ማስረዳት ጀመረ።”

”የሚያስፈራ ህልም ነው ያየሁት፤ ሁለት ዓይኔ ጠፍቶ፣ ሁለቱም ጆሮየ ደንቁሮ፣  አልሰማ፣ አላይ ፣ ማሰብም ሆነ ማገናዘብ አቅቶኝ፣ ከሙት- ሬሳ ጋር እየታገልኩ፣ ሙሉ ለሊት ስሰቃይ ነው ያደርኩት። ምን ኣይነት ስቃይ ሊመጠባኝ ይሆን? ” በማለት ህልም ፈችውን ጠየቀ።

ህልም ፈችውም ፈገግ ብለው ”በጣም ጥሩ ህልም ነው ያየኽው። ልትደሰት ይገባሃል።” አሉት።

ህልመኛው ” እየቀለዱ ነው አይደል? ወይስ ሊያጽናኑኝ ነው?” አላቸው።

”አየህ ! ያየህው ህልም የሚያሳየው፣  በቅርቡ ገዥ ትሆናለህ። ሥልጣን ትይዛለህ።” አሉት።

ቀጥለውም ” አየህ!  የዘመናችን  ገዥዎች  ዓይን አላቸው ግን አያዩም። ጀሮ አላቸው ይነገራቸዋል፤ ግን  አይሰሙም፤ አያዳምጡም ። ጭንቅላት አላቸው ግን ህሊና የላቸውም። የፈለገውን ያህል ቢሞት፣ ቢገደል ምናቸውም አይደልም። በህልምህ ያየህው ፍርሃትህም ድፍረትህ ነው፤ ጭንቀትህም ጥጋብህ ነው። እናም  የህልምህ ፍቹ የሚያሳየው በቅርቡ ትልቅ ባለሰልጣን እንደምትሆን ነው። የዘመናችን
ን ገዥዎች ትቀላቀላለህ።” በማለት አሰናበቱት።

በ’ርግጥም  ከጠ/ ሚኒስትራችን ጀምሮ  ያሉ ገዥዎቻችን የሚያይም ሆነ የሚሰማ ጀሮና የሚያገናዝብ ህሊና ቢኖራቸው ከዚህ ደራጃ ባልደረስን ነበር። ማን ነበር ” በኢትዮጵያ ወስጥ ባለሥልጣንና ቱጃር ለመሆን ከፈለክ፤ ደደብና ደፋር ሁን።” ያለው።

በዕለቱ ጠ/ሚሩ ” —አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን—የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?—- የሚለው ንግግራቸው ፤ ከተጠቅምንበት  ቢያንስ ሁለት መልዕክቶችን ያስተላልፋል፤

አንደኛው  በአገራችን ህግና ሥርዕት የሚባል እንደሌለ፣
 ጎሳን መከለያ አደርገው አገር እያፈረሱ መሆኑንና ።
ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ  ወደ አንድነትና  ከጎሰኝነት ነጻ የሆነ  ሁሉንም ዜጋ የሚያቅፍ  ትግል ለህልውናው እንዲያደርግ ጥሪ የሚያስተላልፍ ነው።

በአጠቃላይ መልኩ የአገራችን ሁኔታ ሲታይ መንግሥት ክልልሎቹን መቆጣጠርና ማስተዳደር ተስኖት፤ ማዕከላዊነት እየጠፋ ነው። ይህ ደግሞ  ” ኢትዮጵያን በኛ የበላይነት ካልገዛናት እናፈርሳታለን—” ለሚሉት የሚፈልጉትና ጡንቻቸውን የሚያሳዮበት፣ ብሎም የ’ርስ -በርስ ጦርነት በማቀጣጠል፤ በህዝብ ደም ለመነገድ መንገዱን ይጠርግላቸዋል። ይህ ትላንት ወያኔ፤ ዛሬ ደግም ጠ/ ሚሩና ግብረ አበሮቻቸው ማጠፊያው ሲያጥራቸው ወደ ፍጹም ጎሰኝነት እየሄዱበት ያለው መንገድ ነው።  ለዚህ ሃቅ ማስረጃ ደግሞ ሰሞኑን ስልጣን የያዙበትን አምስተኛ ዓመት ለማክበር  በኢትዮጵያ ህዝብ ስም በጠ/ሚስተርነት መሰየማቸውን እንኳን ዘንግተው ፤ መጣሁበት የሚሉትን  ጎሳ ብቻ ነጥለው ለድጋፍ መጥራታቸውና በተቃራኒው ደግሞ ወደ ስልጣን ሲወጡ ሙሉ ድጋፍ የሰጣቸውን አካባቢ ያለ ግዜው ትጥቅ ለማስፈታት የሂዱበት መንገድ  እውነታውን ይነግረናል።

እንግዲህ ያለው ነባራዊ ሁኔታ አገናዝበን ለወቅቱ የሚመጥን  ትግል ማደርግና መደራጀት፤ ብሎም አገርና ህዝብን መታደግ
የእያንዳንዳችን ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።   ምክንያቱም ትግሉ የመኖርና ያለመኖር ነውና። በተግባር እያሳዩን፤ በአንደበታቸው  እየነገሩን ያለው ”  ” —አገር ለማፍረስ ከፈልግን ማን ሊከለክለን—የሚያቆመንስ ምን ኃይል አለ?—-” የሚል ነው።

እናፈርሳለን  የሚሉት ራሳቸው እንደሚፈርሱ ማሳየት ደግሞ ከእኛ ከትዮጵያዊያን እንጅ ከማንም አይጠበቅም።  በአንድ ወቅት  ሊቀ-ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ ንእንደከተቡት፤”– ደርግ ገዝቶ ሂደ፤ ወያኔ እየገዛ ነው፤ እሱም ይሂዳል።  —እግዚአብሄርና ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ይኖራሉ።—–”

እኛም እንላለን፤  ብልጽግናም እየገዛ ነው፤  ግን እሱም ይሄዳል፤ እግዚአብሄርና ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ይኖራሉ።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

ፊልጶስ
መጋቢት /2015

Filed in: Amharic