98በመቶ ለሚሆን ህዝብ የጫካ ፕሮጀክት ሸክም እንጂ ቀና የሚያደርገው ፈጽሞ አይሆንም።!
ሸገር ታይምስ
”….ደግሞ ልትወጪ ነው ያ ቅዳሜ መጣ” ነው ያለው ጌትሽ ማሞ?! እንደተለመደው ከሶስትና አኣራት የማይበልጡ ቤቶችን ለማደስ ዶማ ይዘው ወጥተዋል። ምሽቱን በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በላያቸው ላይ ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ ተጥለዋል። የአሁኑ የሚከፋው ደግሞ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች በአከባቢው ፈጽሞ መገኘት የለባቸውም በሚል የተጀመረው እስከግድያ የሚደረስ እርምጃ ነው። ትላንት ሌሊት በሰበታ ቤታቸው የፈረሰባቸው ባልና ሚስት በፖሊስ ጥይት መገደላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። ሌላም አንዲ እናት በተመሳሳይ በመንግስት ሃይሎች በተውሰደ እርምጃ የተገደሉ ሲሆን የሶስቱም ሰዎች አስክሬን ሆስፒታል እንደሚገኝ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተል ጋዜጠኛ ለመረዳት ችዬአለሁ።
እንደሰማሁት አሁን የተጀመረው ቤት የሚፈርስባቸው ሰዎች በአዲስ አበባም ሆነ በዙሪያዋ ቤት መከራየት አይችሉም። የሚያከራያቸው ካለ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ይከፍላል። ወደ ሀገራችሁ ሂዱ! ነው እየተባሉ ያሉት። መሄጃ የለንም ብለው ወዳጅ ዘመድ ጋ የተጠጋ እግር በእግር ክትትል ተደርጎበት ይደበደባል፡ ይታሰራል፡ እንደነ አቶ መሀመድና ባለቤታቸው ከሆነ ደግሞ በጥይት ተደብድቦ ይገደላል። አይናችሁን ማየት አንፈልግም ዓይነት ፍጹም አረመኔያዊ ተግባር ነው መሀል ኢትዮጵያ ላይ እየሆነ ያለው። ሰውዬው ደግሞ አብራር አብዶን ያስናቁ ቲያትረኛ ወጥቷቸዋል። 10ሺዎችን በጎን ያፈናቅሉና ዶማ ይዘው ቅዳሜን ጠብቀው ሶስት ቤቶችን ሲያሳድሱ በካሜራ እይታ ውስጥ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ረጅም ሀተታ ለቀው ይሄዳሉ። እሳቸው ጋ አመራር እንዲህ ነው። ነገም ይቀጥላል። ሌላ ቅዳሜ ይመጣል። መቶ ሺዎች ይፈናቀላሉ። 10 ቤትች ይታደሳሉ። ይኸው ነው።
ይልቅስ የከፋው ግዙፉ መፈናቀል ከፊት እየመጣ ነው። ምናልባትም ይኸኛውም መፈናቀል በዓይነቱም በግዝፈቱም ወደር የማይገኝለት ይሆናል። የዓለምን ክብረወሰንን ይሰብራልም ተብሎ የሚጠበቅ ነው። አንድ ትሪሊየን የሚጠጋ ብር ይፈጃል የተባለውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅልፍ ያጡለት የቤተመንግስት ግንባታ ግማሽ ሚሊዮን የአዲስ አበባና ዙሪያዋን ነዋሪዎች እንደሚያፈናቅል እየተነገረ ነው። 500ሺህ ዜጎች በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ቤታቸው ይፈርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ከወዲሁ መጀመሩንም እየሰማሁ ነው። እናቶች ተጨንቀቃል። አባቶች መላ ቅጡ ጠፍቷቸዋል። ሰዉ የት እንደሚሄድ ግራ ገብቶት እንደእብድ መንገድ ላይ እያወራ ወዲህ ወዲያ ይንከላወሳል። የአቶ አቢይ አህመድ መንግስት ይዞ የመጣው ዱብ እዳ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው አይተውት ሰምተውት የሚያውቁት አይደለም። ይሄ መቼም ቁጣ ነው። ፈጣሪ የተቀየመው ነገር ቢኖር እንጂ እንዲህ ዓይነት ህዝብ የሚያስለቅስ፡ ሀገር ማቅ የሚያስለብስ አገዛዝ ምን ቢፈርድበት ነው የሰጠው?
የጫካ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለሟቸው ቅንጡ ፕሮጀክቶች ትልቁ ነው። የኢትዮጵያን ዓመታዊ በጀት ሁለት እጥፍ ይስተካከላል። ገንዘቡ ከየት ይመጣል የሚለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ሰጪዎች በቀር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው። ለምክር ቤቱ አያገባችሁም ብለዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ዮናስ ብሩ እንዲህ ዓይነት በህዝብ የተመረጠንና ሰይሞት ስልጣን የሰጠውን ምክር ቤት አያገባችሁም የሚል መሪ የትም ሀገር ኖሮም ተፈጥሮ አያውቅም ብለዋኛል ሰሞኑን። አቶ አያልቅበት እንደልቡ ናቸው። የህዝብ ንቀት እስከአፍንጫቸው ደርሶ በአፍጢማቸው ሊደፋቸው ደርሷል። ምንም ነገር አይቀበሉም። ማንንም አይሰሙም። ከእነመንግስቱ ብሃይለማርያምና መለስ ዜናዊም ብሰው ሁሉን ነገር ፈላጭ ቆራጭ ሆነው አርፈዋል። ሀገሪቱን የግል ንብረታቸው አድርገዋታል። ሚኒስትሮቻቸውን የግል አሸከሮቻቸው እንጂ በራሳቸው የቆሙ መንግስትን የሚወክሉ አድርገው አይመለከቷቸዋም። በዙሪያቸው ሰጋጅ፡ ምንጣፍ ጎታች ሰብስበዋል። በአጭሩ ሰው ጤፉ ናቸው። ሚሊዮኖች ቢፈናቀሉ፡ ሚሊዮኖች ቢገደሉ ስሜት አይሰጣቸውም። ይህን ሁሉ መዓት ሀገሪቱን ላይ ከምረውና ቆልለው፡ ፈካ ፈታ ብለው ሲታዩ እውን ይሄ የጤና ነውን የሚል ጥያቄን ያጭራል።
እንግዲህ ይህ የጫካ ፕሮጀክት አሁን ባለው ዋጋ 850ቢሊየን ብር ወይም 15ቢሊየን ዶላር የምሚፈጅ ነው። ስራው ተጀምሮ እስኪያልቅ ከአንድ ትሪሊየን ብር ሊሻገር እንደሚችል ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት። ይህን ብር ይዘን ሂሳቡን በተለያዩ ለኢትዮጵያውያን የህይወይትና ሞት ሽረት በሆኑ ጉዳዮች እንመንዝረው። በዶላር ያለውን ሂሳብ ወስደን ማለት ነው። 15 ቢሊየን ዶላር፥ ሶስት የህዳሴ ግድብን ይገነባል። 1ቢሊየን ዶላሩ 20 ሆስፒታሎችን በየክልሉ ማቆም ያስችላል። ሌላ 1 ቢሊየን ዶላሩ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ዩኒቨርስቲዎችን ያቋቁማል። 1 ቢሊየን ዶላር በትግራይ፡ በአማራና በአፋር ክልሎች የወደሙ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች መልሶ በተሻለ መልኩ ለመገንባት ያስችላል። 1 ቢሊየን ዶላር የኮይሻ ሀይድሮ ኤሊክትሪክ ፕሮጀክት ግንባታን እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። በ1 ቢሊየን ዶላር 3ነጥብ 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ይገዛል። ለ20 ሚሊየን የተራቡ ዜጎቻችን ከአምስት ወራት በላይ ቀለብ እንዲኖራቸው ያደርጋል። 1 ቢሊየን ዶላር 4ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ስኳር ለመግዛት ያስችለናል። 1 ቢሊየን ዶላር 2ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ ይገዛልናል። አርስ አደሮቻችን ተንበሸበሹ ማለት ነው። እንግዲህ እስከአሁን የተጠቀምነው 6 ቢሊየን ዶላሩን ብቻ ነው። 9 ቢሊየን ዶላር ይቀረናል። እንቀጥል ይሆን?
የአብይ አስተዳደር 2ቢሊየን ዶላር ገንዘብ እንዲሰጠው የገንዘብ ሚኒስትሩንና የብሄራዊ ባንክ ገዢውን አሜሪካን ድረስ ለአንድ ሳምንት አቆይቶአቸው ደጅ ሲጠኑ ከርመዋል። ባዶ እጃቸውን ቢመለሱም ያቺን ዶላር ለማግኘት ያደረጉት ተጋድሎ መቼም የሚዘነጋ አይደለም። የዶላር ጠኔ ውስጥ ሆኖ የሚሰቃየው መንግስት ነው እንግዲህ ከየት እንደሚሸመጠጥ ግልጽ ባልሆነ 15ቢሊየን ዶላር እነኋይት ሀውስንና በኪንግሃም ቤተመንግስቶችን የሚያስንቅ ግዙፍ ቤተመንግስት ለማስገንባት እየተዘጋጀ ያለው። 98 በመቶ ከመካከለኛ ገቢ በታች የሚኖር ህዝብ ባለባት፡ 30 ሚሊዮን የምግብ እርዳታ ጠባቂ የሆኑ ዜጎች በሚኖሩባት፡ 38 በመቶ የዋጋ ግሽበት በሚያሰቃያት፡ በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት ምጥ የሆነበት ሲሶ ያህል ህዝብ በሚርመሰመስባት ሀገረ ኢትዮጵያ ነው እንግዲህ አቶ አብይ አህመድ የሀገሪቱን የሁለት አመት በጀት በአንድ ቅንጡ ቤተመንግስት ላይ ለማባከን ቀበቶአአቸውን ታጥቀው የተነሱት።
ከገንዘቡ በላይ አፈር ከድሜ ያስጋጡት የሀገሪቱ ስርዓተ መንግስትና የህግ የበላይነት እጅግ የሚያሳስብ ነው። አያገባህም የተባለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፉን ሎጉሞ የሰውዬውን የእብደት አካሄድ ቆሞ እያየ ነው። እንደውም አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት ”አበጀህ የእኛ ልጅ” ዓይነት ውዳሴና ሙገሳ እያዥጎደጎዱ ናቸው። በኢትዮጵያ መሬት አንዲት ስንዝር መሬትና አንዲት ስባሪ ሳንቲም ያለምክር ቤቱ ፍቃድና እውቅና መነካት እንደሌለበት ቢታመንም ከህግ በላይ፡ ከሀገሪቱ በላይ ለመሆን በሚታትሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መዳፍ ውስጥ ተጨብጦ የቀለጠው ምክር ቤቱ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ መሆኑን አለመረዳቱ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን ፕሮጀክት ማስቆም ይገባዋል። ምንም አይጠቅምም። ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ የኑሮ ሰማይ እንደእንቅብ ለተደፋበት 98በመቶ ለሚሆን ህዝብ የጫካ ፕሮጀክት ሸክም ሆኖ ወገቡን የሚቀነጥስ እንጂ ቀና የሚያደርገው ፈጽሞ አይሆንም።