ወደር የለሹ ያሜሪቃ መንግሥት ተመጻዳቂነት፤ ካማራ (Amhara) እና ዊገር (Uyghur) አንፃር
“Somoza may be a son of a bitch, but he’s our son of a bitch”
President F. D. Roosevelt (about the brutal dictator of Nicaragua)
“ሳሞዛ ውሻ ቢሆንም፣ የኛ ውሻ ነው፡፡”
ፕሬዚደንት ሩዝቬልት (አረመኔውን የኒካራጓ አምባገነን በተመለከተ)
መስፍን አረጋ
ላሜሪቃ መንግሥት ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች በራሳቸው ግቦች ሳይሆኑ የግብ መምቻ መሣርያወች መሆናቸው አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ገሃድ ሚስጥር (open secret) ነው፡፡ መሣርያነታቸው ደግሞ ያሜሪቃን ፈላጭ ቆራጭነት በጽኑ የሚቃወሙትን ወይም በጽኑ የሚታገሉትን አገር ወዳድ መሪወች ስም በማጥፋት ለመደብለስ (ዳቢሎስ ለማስመሰል፣ demonize) እና የገዛ ሕዝባቸው እንዲነሳሳባቸው ለመቀስቀስ ነው፡፡ ባጭሩ ለመናገር ያሜሪቃ መንግሥትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ከትርጉማቸው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የቱልቀዳ (ፕሮፓጋንዳ፣ propaganda) መሣርያወች ናቸው፡፡
ባንድ ወቅት ያሜሪቃ ፕሬዚዳነት የነበረው ፍራንክሊን ሩዘቬልት በግልጽ እንደተናገረው፣ ያሜሪቃ ውሻ የሆነ መሪ የፈለገውን ያህል አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ ቢሆንም፣ ባሜሪቃ ውሻነቱ እስከቀጠለ ድረስ ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ አሜሪቃ አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ታደርግለታለች እንጅ ልትቀጣው ቀርቶ አትቆጣውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያሜሪቃን ጥቅም የሚጻረር መሪ የፈልገውን ያህል ዲሞክራት ቢሆንም፣ አሜሪቃ ግን ግለሰቡን ፀርዲሞክራሲ ለማስባል በሐሰት ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ትከፍትበታለች፡፡ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ አሜሪቃ ወደር የሌላት ተመጻዳቂ (hypocrite) ናት የምትባለውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡ ላሜሪቃ ወደርየለሽ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ተመጻዳቂነት በደንብ የሚታወቁ ምሳሌወች ተዘርዝረው የማያልቁ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ አማሮችን (Amhara) እና የቻይና ዊገሮችን (Uyghurs) ምሳሌ መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡
በ1980ውቹ ውስጥ፣ ቻይና ያሜሪካ ፋብሪካ (US manufacturing center) በመሆን ሶቬት ሕብረትን (USSR) የምትናከስ ያሜሪቃ ውሻ ነበረችበት፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ ያሜሪቃ መንግሥት ለቻይና ዊገሮች (Uyghurs) ማሰብ ቀርቶ ከነመፈጠራቸው የሚያቅ አይመስልም ነበር፣ ስማቸውን ደግሞ በክፉም ሆነ በበጎ አንድም ቀን አንስቶ አያውቅም ነበር፡፡ ያሜሪቃ ታላላቅ ኩባንያወች ወደ ቻይና እየጎረፉ፣ የቻይና ወዛደሮችን (ዊገሮችን ጨምሮ) ጉልበታቸውን በነጻ በሚባል ደረጃ እየበዘበዙ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ትርፎችን ሲያግበሰበሱ፣ ስለዚህ ዘመናዊ ባርነት (modern slavery) ያሜሪቃ መንግሥት ማውሳት ቀርቶ አላነሳም ነበር፣ መቃወም ቀርቶ አላጉረመረመም ነበር፡፡
አሁን ላይ ግን፣ ቻይና ታምራዊ በሚባል ደረጃ ባጭር ጊዜ ውስጥ አድጋና ተመንድጋ ያሜሪቃን ልዕልኃያልነት መገዳደር (challenge) ስለጀመረች፣ የቻይና ኮሚኒስት መንግሥት በቻይና ዊገሮች ላይ ከፍተኛ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ ነው በማለት ያሜሪቃ መንግሥት የቻይናን መንግሥት በየዕለቱ መውቀስና መክሰስ ጀመረ፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ያሜሪቃ ታላላቅ ኩባንያወች ወደ ቻይና ሲጎርፉ የቻይና መንግሥት ኮሚኒስት ያልነበረ ይመስል፣ ያሜሪቃ መንግሥት አሁን ላይ ስለቻይና ኮሚኒስት መንግሥት (communist government) የሚያወሳው፣ ኮሚኒስት (communist) የሚለውን ከፍተኛ አጽንኦት በመስጠት ሆነ፡፡ ቻይና ያሜሪቃ ውሻ በነበረችበት ጊዜ ላሜሪቃ መንግሥት ይታየው የነበረው ያሜሪቃ ውሻ መሆኗ እንጅ ኮሚኒስትነቷ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ላሜሪቃ መንግሥት የሚታየው ኮሚኒስትነቷ ብቻ ሆነ፡፡ በዊገሮች ላይ ትሠራለች የሚለውን ግፍ የሚያቆራኘው ደግሞ ከኮሚኒስትነቷ ጋር ሆነ፡፡
“We, the Foreign Ministers of Canada and the United Kingdom, and the United States Secretary of State, are united in our deep and ongoing concern regarding China’s human rights violations and abuses in Xinjiang. China’s extensive program of repression includes severe restrictions on religious freedoms, the use of forced labor, mass detention in internment camps, forced sterilizations, and the concerted destruction of Uyghur heritage.” (US State Department, Joint Statement on Xinjiang, March 2021).
“እኛ ያሜሪቃ፣ የእንግሊዝ እና የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቻይና በሺንጃንግ (Xinjiang) ዊገሮች (Uyghurs) ላይ የምትፈጽመው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከፍተኛ ግፍ በጅጉ ያሳስበናል፡፡ የቻይና ግፎች የዊገሮቸን የሐይማኖት ነጻነት በከፍተኛ ደረጃ መገደብን፣ ዊገሮችን በባርነት ማሠራትን፣ በጅምላ ማሠርን እና በግዳጅ ማምከንን (forced sterilzation) እንዲሁም የዊገሮችን ታሪካዊ ቅርሶች በቅንጅት ማውደምን ይጨምራሉ” (ያሜሪቃ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሺንጃንግ ላይ የጋራ መግለጫ፣ መጋቢት 2013)
የቻይና መንግሥት ዊገሮችን አስገደዶ ያመክናል እያለ ያሜሪቃ መንግሥት የሚያወግዘው በግዳጅ ማምከንን በመርሕ ደረጃ ስለሚቃወም ሳይሆን፣ ያሜሪቃን የበላይነት የምትገዳደረውን ቻይናን የሚያወግዝበት ምክኒያት ስለሆነለት ብቻና ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያማ የቻይና መንግሥት ዊገሮችን አስገድዶ አምክኗል ተብሎ ከሚከሰስበት እጅግ በከፋና ሊስተባበሉ በማይቻሉ አያሌ መርጃወች በተደገፈ ሁኔታ እልፍ አእላፍ አማሮችን ያመከነው የመለስ ዜናዊ መንግሥት ዋና ደጋፊ ያሜሪቃ መንግሥት ባልሆነ ነበር፡፡ መለስ ዜናዊ ግን አሜሪቃ ስትጠራው አቤት፣ ስትለከው ወዴት የሚል፣ ላስ ያለችውን የሚልስ፣ ንከስ ያለችውን የሚነክስ ያሜሪቃ ታማኝ ውሻ ስለነበር፣ ፀርዲሞክራሲ አምባገነን ከመሆኑም በላይ የለየለት ዘር ጨፍጫፊ መሆኑ ላሜሪቃ አይታያትም ነበር፣ ቢታያትም አይታ እንዳላየች ታልፍለት ነበር፡፡
ራሱ የመለስ ዜናዊ መንግሥት በራሱ ፓራላማ ላይ በይፋ ባመነው መሠረት፣ በ 2000 ዓ.ም ባደረገው የሕዝብ ቆጠራ ላይ 2.5 ሚሊዮን (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ) አማሮች ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ የመለስ ዜናዊ መንግሥት ቁጥርን እንዳስፈላጊነቱ ባያሌ እጥፍ የሚጨምርና የሚቀንስ የቁጥር ሌባ መሆኑ የታወቅ ስለሆነ ደግሞ፣ ደብዛቸው የጠፋው አማሮች ቁጥር ወያኔ ካመነው ቢያንስ ሁለት እጥፍ (አምስት ሚሊዮን) ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ እውነተኛው ቁጥር ይቅርብን ብለን ወያኔ ያመነውን (ሁልት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ) ብቻ ብንወስድ እንኳን፣ የመለስ ዜናዊ ወያኔ መንግሥት ባማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ፣ የሩዋንዳውን ጭፍጨፋ በእጥፍ የሚያስከነዳ፣ የአዶልፍ ሂትለር ናዚ መንግሥት በይሁዳወች ላይ ከፈጸመው ጭፍጨፋ ቀጥሎ ያለማችን ትልቁ ጭፍጨፋ ይሆናል፡፡
መለስ ዜናዊ ይሄን ባፍሪቃ ውስጥ ወደር የሌለውን ጭፍጨፋ ባማራ ሕዝብ ላይ ሊፈጽም የቻለው ግን ያሜሪቃ መንግሥት ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ፕሮፓጋንዳዊና ፋይናንሳዊ ድጋፍ ስላደረገለትና መንግሥቱን ቀጥ አድርጎ ስላቆመለት ብቻና ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ቻይና ዊገሮችን ጨፈጨፈች እያለ የሚከሰው ያሜሪቃ መንግሥት፣ ባማራ ሕዝብ ጭፍጨፋ በቀጥታ የተሳተፈ፣ ጊዜው ሲደርስ ያማራ ሕዝብ ፍርድ ቤት የሚያቆመውና አስፈላጊውን ካሳ ከነወለዱ የሚያስከፈለው ጨፍጫፊ መንግሥት ነው፡፡ ያማራ ሕዝብ የመለስ ዜናዊ ቀንደኛ ደጋፊወች የነበሩትን እነ ኸርማን ኮኸንን (Herman Cohen)፣ ሱዛን ራይስን (Suzan Rice)፣ ጌይል ስሚዝን (Gayle Smith) እና የመሳስሉትን የሚያያቸው የይሁዳ ሕዝብ የአዶልፍ ሂትለር ቀንደኛ ናዚወችን በሚመለከትበት ዓይን ነው፡፡
ያሜሪቃ መንግሥት ባማራ ሕዝብ ጭፍጨፋ ላይ በቀጥታ የተሳተፈ ጨፍጫፊ መንግሥት መሆኑ ሳያንሰው፣ በተጨፈጨፈው ባማራ ሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት የሚሰድ ጭካኝ መንግሥት ነው፡፡ ባማራ ሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት የሰደደው ደግሞ ያማራን ሴቶች በማምከን (sterilize) ከፍተኛ ሚና የተጫወተውን የምክነት ዶክተር (sterilzation doctor) የሆነውን ቴድሮስ አድሃኖምን (Tedros Adhanom) ያለም ጤና ጥበቃ (World Health Organization) ዋና ዳይሬክተር (director general) በማድረግ ነው፡፡ ያሜሪቃ መንግሥት ባንድ በኩል የዊገር ሕዝብ ጨፍጫፊወች ናቸው የሚላቸውን እያወገዘ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያማራ ሕዝብ ጨፍጫፊወች መሆናቸው ሊስተባበል የማይችለውን ወንጀለኞች ለከፍተኛ ሹመት የሚያበቃ ወንጀልኛ ብቻ ሳይሆን ተመጻዳቂ መንግሥት ነው፡፡
የቻይና መንግሥት የዊገሮችን ዲሚክራሲያዊ መብቶች ረግጧል እያለ ያሜሪቃ መንግሥት የቻይናን መንግሥት ሳያሰልስ ይከሳል፡፡ በሌላ በኩል ግን የ1997ቱን ምርጫ ውጤት በመቃወም ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመግለጽ የወጡትን አዲሳቤወች የመለሰ ዚናዊ አጋዚ ሠራዊት እንደ ቅጠል ሲያረግፋቸው፣ ያሜሪቃ መንግሥት መለስ ዜናዊን ተቃውሞውን በፍጥነት አቆምክ በማለት በከፍተኛ ደረጃ አመስግኖ፣ የመለስ ዜናዊን ቅጥፈት ውነት በማለት ጭፍጨፋውን ባደገኛ ቦዘኔ አማሮች (lumpen Amhara protesters) ላይ አምሃኝቶ፣ ከሂትለር ኤስኤስ (SS) ቢብስ እንጅ ለማይተናነሰው ለመለስ ዚናዊ አጋዚ ሠራዊት ተጨማሪ ማሰልጠኛ (additional training) በሚል ሰበብ ተጨማሪ ቢሊዮኖችን ለመለስ ዜናዊ መንግሥት ፈሰስ አድርጎለታል፡፡ ያሜሪቃ መንግሥት ባንድ በኩል የዊገርን ሕዝብ ዲሞክራሲ መብቶች ይረግጣሉ የሚላቸውን እያወገዘ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያማራን ሕዝበ ዲሞክራሲ መብቶች የሚረግጡትን በሁሉም ረገዶች በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፍ ወንጀልኛ ብቻ ሳይሆን ተመጻዳቂ መንግሥት ነው፡፡
የቻይና መንግሥት ዊገሮችን በገፍ እያፈናቀለ በምትካቸው ሃኖችን (Hans) በማስፈር ሺንጃንግን (Xingiang) የሃን ለማድረግ ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክት (state project) ነድፎ በከፍተኛ ደረጃ ይንቀሳቀሳል እያለ ያሜሪቃ መንግሥት የቻይናን መንግሥት ያወግዛል፡፡ በሌላ በኩል ግን የመለስ ዜናዊ ወያኔ መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክት ነድፎ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የወልቃይትና የራያ አማሮችን በገፍ አፈናቅሎ፣ በምትካቸው ወያኔወችን በገፍ ሊያሰፍር የቻለው አስፈላጊውን ወጭ ምዕራባዊ መንግሥታት (በተለይም ደግሞ ያሜሪቃ መንግሥት) ሙሉ በሙሉ ስለሸፈኑለት ነበር፡፡
በተለይም ደግሞ ወልቃይት ካማራ የፀዳቸው ወያኔና ያሜሪቃ መንግሥት ተቀናጅተው ባካሄዱት መግፋትና መሳብ (push-pull effect) ነበር፣ ወያኔ ሰይፉን (sword) እያብለጨለጨ አማሮችን ከወልቃይት ሲገፋ፣ ያሜሪቃ መንግሥት ደግሞ ግሪን ካርዱን (Green Card) እያቁለጨለጨ አማሮችን ወደ ሱዳን በመሳብ፡፡ ይህ ወያኔና ያሜሪቃ መንግሥት በቅንጀት ያካሂዱት የዲሞግራፊ ቅየራ (engineered demographic change) ውጤቱ እጅግ አመርቂ ከመሆኑ የተነሳ፣ ዛሬ ላይ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በውሳኔ ሕዝብ (referendum) እልባት እንዲያገኝ የሚወተውቱት አማሮች ሳይሆኑ ወያኔና ያሜሪቃ መንግሥት ናቸው፡፡
“We … urge the Government of Ethiopia to withdraw Amhara regional forces from the Tigray region and ensure that effective control of western Tigray is returned to the Transitional Government of Tigray.” (Press Statement, Anthony J. Blinken, May 15, 2021)
“ያማራ ክልል ኃይሎችን ከምዕራብ ትግራይ እንዲያስወጣና፣ ምዕራብ ትግራይን ለትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲመልስ የኢትዮጵያን መንግሥት አጥብቀን እንጠይቃለን” (ዕለታዊ መግለጫ፣ አንቶኒ ብሊንክን፣ ግንቦት 7፣ 2013 ዓ.ም)
ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ፣ በጦቢያ ምድር ላይ የነገሠው ያሜሪቃ ውሻ ጭራቅ አሕመድ ነው፡፡ ጭራቅ አሕመድ ስለ ነጻነት ምንነት ምንም ባማያውቅበት በልጅነት እድሜው ኦሮሞን ካማራ ነጻ ለመውጣት ጫካ የገባ፣ የኦነግ የልጅ ወታደር (child soldier of OLF) ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በይፋ ያልተበሠረለት (undeclared) የኦነግ ሉባ (ዋና አለቃ) ሁኗል፡፡ የኦነግ ይፋዊ ዐላማ ደግሞ አማራን ቢቻል ጨርሶ በማጥፋት ባይቻል ደግሞ እጅግ አምንምኖ በጦቢያ ላይ ሊጫወት የሚችለውን ፖለቲካዊ ሚና ኢምንት በማድረግ፣ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሞን አፄጌ (Oromo empire) መገንባት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ጭራቅ አሕመድ ባምስት ዓመት የስልጣን ዘመኑ ያሳካው፣ መለስ ዜናዊ በሃያ አምስት ዓመት የስልጣን ዘመኑ ካሳካው ያለ ምንም ማጋነን ከመቶ ሃያምስት እጥፍ በላይ ይበልጣል፡፡
ያሜሪቃ መንግሥት ባልተርጋገጡ ዘገባወች (unconfirmed reports) እና ባሉባልታወች (innuendos) ላይ ብቻ ተመርኩዞ፣ የቻይና መንግሥት ዊገሮችን በግፍና በገፍ ጨፍጨፏል እያለ ዘወትር ይከሳል፡፡ ሊስተባበሉ የማይችሉ ማስረጃወች ያሏቸውን፣ በምስሎችና በቪድዮወች የተደገፉትን፣ የጭራቅ አሕመድ ኦነጋዊ መንግሥት ባማራ ሕዝብ ላይ የፈጸማቸውን እጅግ ዘግናኝና እጅግ ከፍተኛ ጭፍጨፋወች ግን ያሜሪቃ መንግሥት ማውገዝ ቀርቶ አይጠቅሳቸውም፡፡ ለምሳሌ ያህል ቶሌ በሚባለው ቢዛሞ ውስጥ በሚገኘው ቀበሌ ላይ በሺ የሚቆጠሩ አማሮች የታረዱት ባንድ ሳምንት ሳይሆን፣ ባንድ ቀን ሳይሆን፣ ባንድ ሰዓት ቢሆንም፣ ያሜሪቃ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣርያወች ለሆኑት ለ BBC እና CNN ግን ትልቅ ዜና አልነበረም፡፡
የጊዜው የኦነግ መሪ ጭራቅ አሕመድ ባመስት ዓመት የስልጣን ዘመኑ ባማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመው፣ ያለፉት የኦነግ መሪወች በመቶ ዓመት እንፈጽመዋለን ብለው ማስብ ቀርቶ የማያለሙትን ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ጭራቅ አሕመድ ባማራ ሕዝብ ላይ እስካሁን የፈጸመው ጭፍጨፋ ያሜሪቃን መንግሥት ያላረካው ይመስል የፕሪቶርያ ስምምነት (Pretoria Agreement) የሚባል አዲስ ያማራ ጭፍጨፋ ፕሮጀክት ነድፎ፣ በሥራ ላይ ማዋል ጀምሯል፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ዋና ዓላማ፣ ጭራቅ አሕመድ “ያማራን ልዩ ኃይል ለመበተንና ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት” በሚል ሰበብ ባማራ ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ይፋ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲከፍት ማድረግ ነው፡፡ የስምምነቱ ዋና ዐላማ ይሄውና ይሄው ብቻ መሆኑን ደግሞ ያሜሪቃ መንግሥት ያፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ (special envoy) የሆነው አቶ ሚካኢል መዶሻ (Mr. Michael Hammer) በቅርቡ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ በገዛራሱ አንደበት ተናግሯል፡፡
“The United States participated as an observer in the African Union lead talks in Pretoria … which produced the cessation of hostilities agreement on November 2nd. We are very proud to have supported that effort along with others and now we have seen the silencing of the guns … and now move to other issues of importance including insuring that Eritrean troops are completely removed from the region, and you deal with other Amhara special forces and FANNO groups that are active in the area.” (Michael A. Hammer, United States Special Envoy for the Horn of Africa).
“ባፍሪቃ ሕብረት መሪነት በፕሪቶርያ በትካሄደው ውይይት ላይ ያሜሪቃ መንግሥት በታዛቢነት ተካፍሏል፡፡ ውይይቱ በጠላትነት መተያየትንና ተኩስን በማስቆሙ ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል፡፡ የሚቀጥለው ደግሞ የኤርትራ ወታደሮችን ከበታው ሙሉ በሙሉ ማስወጣትና በቦታው የሚንቀሳቀሱትን ያማራ ልዩ ኃይሎችና ያማራ ፋኖ ልከ ማስገባት ነው” (ማይክል ሃመር፣ ያፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልክተኛ)
በማይክል ሃመር ንግግር ላይ፣ የግለሰቡን አጸያፊ አጭበርባሪነት ይልቁንም ደግሞ ሸፍጠኛነት በግልጽ የምታሳየው ቁልፏ ሐረግ (key phrase) በቦታው የሚንቀሳቀሱ (active in the area) የምትለው ሐረግ ናት፡፡ መሠሪው አቶ ማይክል መዶሻ ይህችን ውስጥ ወይራ ሐረግ የተጠቀመው ያማራ ልዩ ኃይልና ያማራ ፋኖ በቦታው ላይ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪወች ናቸው ለማለት ነው፡፡ ይህን ያለው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ፓርላማ በሽብርተኝነት ተፈርጆ የነበርው ወያኔ የፓርላማውን መቀመጫ (አዲሳባን) ተቆጣጥሮ ፓርላማውን ሊያፈርስ ሲል ፓርላማውን ከፍርሰት የታደጉት፣ በፓርላማው ክተት ተብለው የዘመቱት ያማራ ኃይሎች እንደነበሩ አውቆ አንዳላወቅ በመሆን ነው፡፡
ስለዚህም የፕሪቶርያው ውይይት (Pretoria talks) ብቸኛ ዓላማ ሽብርተኛውን ወያኔን ሕጋዊ አድርጎ ሕጋዊወቹን ያማራ ልዩ ኃይልና ያማራ ፋኖ ሽበርተኛ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ምክኒያት እውነትኛ ያማራ ሕዝብ ተውካዮች በውይይቱ ላይ እንዳይሳተፉና ያማራ ሕዝብ በጭራቅ አሕመድ ኦነጋዊ መንግሥት እንዲወከል የተደርገው ባሜሪቃ መንግሥት ከፍተኛ ጫና መሆኑ አያስገርምም፡፡ ጭራቅ አሕመድ አማራን የማጥፋት ይፋ ዘመቻውን የከፈተው ደግሞ ውይይቱ ተጠናቆ፣ ስምምነቱ ይተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ መሆኑ ሊያስገርም አይገባም፡፡ ጭራቅ አሕመድ ባማራ ሕዝብ ላይ የጥይት ዝናብ እያዘነበ ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ አቶ ሚካኢል መዶሻ ተኩስ ቁሟል (have seen the silencing of the guns) በማለት ባማራ ሕዝብ ላይ መሳቁና መሳለቁ ደግሞ፣ በሮማን ፕሮቻዝካ (Roman prochaska) ፀራማራ ቅንቅና ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተውን ያሜሪቃ መንግሥትን ያፍሪቃ ፖሊሲ ጠንቅቆ ለሚያቅ ምንም አያስደነቅም፡፡
የፕሪቶርያው ስምምነት ከተጠያቂነት ነጻ ያደረገው ጭራቅ አሕመድ፣ ባማራ ሕዝብ ላይ ከሚፈጽመው መጠነ ሰፊ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አልፎ፣ ያማራ ባለሐብቶችን፣ ልሂቆችን፣ ጋዜጠኞችን እና ተቆርቋሪወችን ባደባባይ እፍኖ በጅምላ አጉሯቸዋል፡፡ የትግራይ ልጆች በማንነታቸው ታሠሩ እያሉ ቀን ከሌት ያላዘኑ የነበሩት ምዕራባዊ ሚዲያወች (በተለይም ደግሞ BBC እና CNN)፣ ለትግራይ ሲል የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አስር ጊዜ ገደማ እንዲሰበሰብ ያደረገው ያሜሪቃ መንግሥት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉት Amnesty International እና Human Rights Watch ግን ያማራ ጉዳይ ሲሆን ድምጻቸውን አጥፍተው ዝም፣ ጭጭ፣ ፀጥ፣ ረጭ ብለዋል፡፡ ይህ ዝምታቸው ደግሞ የፕሪቶርያው ስምምነት አካል ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም፡፡
ያሜሪቃ መንግሥት ተመጻዳቂ ብቻ ሳይሆን ጭካኝም ነው፡፡ ለነገሩማ ይህ መንግሥት የተመሠረተው ባገሬ አሜሪቃውያን (Indigenous Americans) ላይ ከፍተኛ ጭካኔ በመፈጸም፣ አድጎና ተመንድጎ ልዕለኃያል ለመሆን የበቃው ደግሞ ባፍሪቃ አሜሪቃውያን (African Americans) ላይ ከፍተኛ ጭካኔ በመፈጸም ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ያሜሪቃ መንግሥት ኃያልነቱን ለመላው ዓለም ለማሳየትና ሶቬት ሕብረት እንዳትገዳደረው ለማስፈራራት ሲል ብቻ፣ ከሽንፈት አፋፍ ላይ የቆመውን የጃፓንን ሠራዊት እጅ መስጠት በጥቂት ቀኖች ለማሳጠር ጃፓንን በኑክሌር ቦንብ የቀጠቀጠ፣ በጥቅሙ ላይ ለሚመጣበት ምህረት የሌለው አረመኔ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ጨካኝ መንግሥት ነው፡፡
የነጻነት ተምሳሌት በመሆን ያፍሪቃውያን መኩርያ የነበረቸው ጦቢያ፣ ባሁኑ ጊዜ አሜሪቃ በሞግዚትነት የምታስተዳደራት ባፍሪቃ ውስጥ ብቸናዋ ያሜሪቃ ሙግዝት አገር (protectorate) በመሆን ያፍሪቃውያን ማፈሪያ ሁናለች፡፡ የጦቢያን ክልሎች ድንበር የሚወስነው ያሜሪቃ መንግሥት ነው፡፡ የትኛው ልዩ ኃይል እንዲበተንና የትኛው ልዩ ኃይል ይበልጥ እንዲጠናከር ቀጭን ትዕዛዝ የሚሰጠው ያሜሪቃ መንግሥት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የትኛው ሕዝብ ትጥቅ እንዲፈታና የትኛው ሕዝብ እስካፍንጫው እንዲታጠቅ የሚፈቅደው ያሜሪቃ መንግሥት ነው፡፡ የጭራቅ አሕመድ ያሜሪቃ ውሻነት እስከዚህ ድረስ ነው፡፡ በውሻነቱ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ ባማራ ሕዝብ ላይ የፍጸመውን ግፍ ቢፍጽምም አሜሪቃ ዝንቡን እሽ አትለውም፣ ውሻዋ ነውና፡፡
አሜሪቃን በተመለከት ዊገሮች እደለኞች ናቸው፣ አገራቸው ቻይና ያሜሪቃን ልዕለኃያልነት (sole superpower status) ለመንጠቅ እየተቃረበች ስለሆነች ብቻ፣ የዊገሮች የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ያሜሪቃ መንግሥት እጅጉን ያሳስበዋልና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪቃን በተመለከተ አማሮች ዕደለቢሶቸ ናቸው፣ አገራቸው ጦቢያ የምትመራው ያሜሪቃ ውሻ በሆነው በጭራቅ አሕመድ ስለሆነ ብቻ፣ ያማሮች የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ተከበሩ አልተከበሩ ላሜሪቃ መንግሥት ዴንታ አይሰጠውምና፡፡
ቻይና ያሜንቃን ልዕለኃያልነት መገዳደሯን እስከቀጠለች ድረስ፣ ያሜሪቃ መንግሥት የቻይናን መንግሥት የዊገሮችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በመርገጥ መክሰሱን ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጭራቅ አሕመድ ያሜሪቃ ውሻ መሆኑን እስከቀጠለ ድረስ፣ ባማራ ሕዝብ ላይ በይፋ የሚፈጽመውን ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከት ያሜሪቃ መንግሥት አይሰማም አይለማም፡፡
ስለ ዲሞክራሲና ስለ ሰብዓዊ መብት ከኔ ወዲያ ላሳር የሚለው ያሜሪቃ መንግሥት፣ ያሜሪቃ ውሻ በሆነ መንግሥት የሚፈጸምን የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ምንም አይሰማም፣ ምንም አያይም፣ ምንም አይናገርም፣ ምንም አያደርግም (hear nothing, see nothing, say nothing, do nothing)፡፡ ያሜሪቃ መንግሥት የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተመጻዳቂነት እስከዚህ ድረስ ነው – ወደር የለውም፡፡
መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com